1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ኤኮኖሚ በማገገም ሂደት?

ረቡዕ፣ ኅዳር 16 2002

2009 ዓ.ም. በፊናንሱ ቀውስ ሳቢያ ለዓለም ኤኮኖሚ ፈታኝ ወቅት ነበር። ይሁንና ችግሩን ለመቋቋም መንግሥታት ያፈሰሱት ገንዘብ ሁኔታውን ለማሻሻል ሳይበጅ አልቀረም። የኤኮኖሚው ትብብርና ልማት ድርጅት ኦኢሲዲ በሰሞኑ ዘገባው እንዳመለከተው የዓለም ኤኮኖሚ በመጪው ዓመት መልሶ ዕድገት የሚታይበት ነው።

https://p.dw.com/p/KgBY
ምስል dpa/DW

ድርጅቱ አውሮፓም የዚሁ ሂደት ተጠቃሚ ስትሆን በተለይም በውጭ ንግዷ ሻምፒዮን የምትሰኘው ጀርመን ከተቀሩት የአውሮፓ ሕብረት አገሮች በበለጠ ሁኔታ እንደምትራመድ ነው የተነበየው። እርግጥ ዕድገቱ ጭብጥ እንዲሆን አውሮፓውያን መንግሥታት የበጀት ኪሣራቸውን ማለዘብና ግብርን ከመቀነስ መቆጠብም ይኖርባቸዋል። ፓሪስ ላይ ተቀማጭ የሆነው የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ጠበብት ሰሞኑን ባለፉት ወራት ከተለመደው ይልቅ ጥሩ ዜና ይዘው መቅረባቸው በዚህ ዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ብርቱ የዕድገት ማቆልቆልን አስከትሎ በቆየባት በአውሮፓም ተሥፋን የሚያዳብር ነው። በድርጅቱ ዘገባ መሠረት በኢንዱስትሪ ልማት የገፉት ዓባል ሃገራቱ በሙሉ ከዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ሊላቀቁ ሳይቃረቡ የቀሩ አይመስልም። ከስብስቡ የኤኮኖሚ ጠበብት አንዱ ኤካርድ ቩርስል እንደሚሉት ለጊዜው የሚቀር ነገር ቢኖር የማገገሙ ሂደት ብዙም ፈጣን አለመሆኑ ነው።

“እኛ በወቅቱ የምንታዘበው ዕድገት ከሚፈለገው ሲነጻጸር ዝግ ያለ ነው። እንደቀድሞው ዓይነት እመርታ አይታየንም”

ጀርመንን እንደ ምሳሌ ከወሰድን የአገሪቱ ኤኮኖሚ በዓመቱ ሂደት 4,9 በመቶ ካቆለቆለ በኋላ በሶሥተኛው ሩብ ላይ 0,7 ከመቶ ዕድገት ታይቶበታል። ይህን ያረጋገጡት ሚዩኒክ ላይ ተቀማጭ የሆነው ኢፎ የተሰኘ ኢንስቲቲዩትና የጀርመን ሰንጠረዥ ቢሮ ናቸው። በነርሱ አባባል በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ የ 1,5 ከመቶ ዕድገት ይጠበቃል። ሆኖም ግን በኦ.ኢ.ሲ.ዲ. ዕምነት በመጪው ዓመት የሚጠበቀው ይህ ዕድገት በጀርመን የሥራ ገበያ ላይ መሻሻልን ለማስከተል የረባ አቅም የሚኖረው አይሆንም። እንደ ባለሙያው ይልቁንም፤

“የሥራ አጡ ቁጥር በጣሙን መጨመሩ የማይቀር ጉዳይ ነው። በጀርመን እስከ 2011 ዓ.ም. አጋማሽ ድረስ፣ ማለት ለተወሰነ ጊዜ ማደጉን ሊቀጥል ይችላል ብለን ነው የምናምነው”

ማለት እስከ 9,7 ከመቶ ገደማ! ከዛሬው ሁለት ከመቶ ከፍ ያለ ይሆናል ማለት ነው። የሆነው ሆኖ በዚህ በጀርመን ብዙዎቹ የአገሪቱ ኩባንያዎች በቀውሱ ሂደት ሠራተኞቻቸውን ሳያባርሩ እስካሁን ይዘው ለማቆየት ችለዋል። ለዚህም በመንግሥት ድጎማ እየተደገፉ የሥራ ሰዓትን መቀነሱ ለምሳሌ ሠራተኞችን ለማቆየት አንዱ ዘዴ ነበር። የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅቱ በዚህ ረገድ የጀርመንን ኩባንያዎች ከፍ አድርጎ ነው ያወደሰው። ይሁንና እነርሱም ቢሆኑ በአስካሁኑ አካሄድ ሊቀጥሉበት የሚችሉ መሆናቸው ያጠራጥራል። ምናልባት በከፍተኛ ወጪ የተነሣ በሚቀጥሉት ወራት የተወሰኑ ሠራተኞችን ማሰናበታቸው እንደማይቀር ነው የሚታመነው። የፓሪሱ ድርጅት ይህንኑ በማጤን መንግሥት የጀመረውን የኤኮኖሚ ማነቃቂያ ዕቅድ ከግቡ እንዲያደርስ ይመክራል። በሌላ በኩል ግን የድርጅቱ ባለሙያ ዮርገን ኤልሜስኮቭ እንዳስገነዘቡት የተያዘው ዕቅድ ጊዜው ከበቃ በኋላ መንግሥታት ለኤኮኖሚው ዘርፍ ገንዘብ ማዝነባቸው ማባራቱ ግድ ነው።

እርግጥ ከኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅቱ ዓባል ሃገራት መካከል የመንግሥት በጀት ኪሣራቸውን እንዴት እንደሚያለዝቡ በወቅቱ ዕቅድ ያቀረቡት ግማሹ ብቻ መሆናቸው ለስጋት መንስዔ መሆኑ አልቀረም። በመሆኑም ድርጅቱ አንዳንድ የአውሮፓ መንግሥታትና ፖለቲከኞች የማስትሪሽቱን የበጀት ኪሣራ ውል አሳሪነት ለጊዜው ለማሸጋሸግ ወይም ለመለወጥ የሚያደርጉትን ሙከራ ተገቢ አድርጎ አላገኘውም። ሆኖም ማንኛውንም ውሉን የማዳከም ዕርምጃ አይቀበለውም። በማስትሪሽት ውል መሠረት የአውሮፓ ሕብረት አገሮች የብሄራዊ በጀታቸውን ኪሣራ በሶሥት ከመቶ መገደብ ይኖርባቸዋል። በፓሪሱ ድርጅት ባለሙያ በኤካርድ ቩርስል ዕምነት የወቅቱ ማነቃቂያ ፕሮግራም ጊዜ ሲያበቃ በረጅም ጊዜ ዕድገት ላይ ያተኮረ ዕቅድ መስፈኑ ግድ ነው የሚሆነው።

“ከዚያ በኋላ ረዘም አድርጎ ማሰቡ ግድ ይሆናል። ይህም ከ 2011 አንስቶ እስከወደፊቱ ማለት ነው። ምክንያቱም ከዚያ በኋላ የሚያስፈልገው በያመቱ ስር በሚሰድ መጠን የዕድገት ሃይልን እያጠናከሩ መሄድ ይሆናል”

የኦኢ.ሲ.ዲ. ዘገባ በተለይ ለጀርመን መንግሥት አስደሳች ላይሆን ይችላል። በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የሥር አጡ ቁጥር በሰፊው የሚጨምር መሆኑ ለመንግሥቱ ካዝና ይበልጥ መሟጠጥ ምክንያት የሚሆን ነው። መንግሥት ግብር ለመቀነስ ያለው ውጥን ተቀባይነት አለማግኘቱም ሌላው ተጨማሪ ግፊት ነው።

“በጀርመን የበጀት ኪሣራውና ይሄው ያስከተለው ዕዳ መቀነስ ይኖርበታል። በመሆኑም ከታቀደው የግብር ቅነሣ አንጻር ምን ዓይነት ተጻራሪ ወይም ማረጋጊያ ዕርምጃ እንደሚወሰድ በጉጉት ነው የምንጠብቀው”

የጀርመን መንግሥት ግብርን ለመቀነስ የያዘውን ዕቅድ ዕውን ለማድረግ ከፈለገ ይህ የሚሆነው በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የሰፈረው የዕዳ ገደብ ከተከበረ ብቻ ነው። የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅቱ ባለሙያዎች ግን ይህ መሳካቱን ይጠራጠራሉ። ለዚህም ምክንያቶቹ በአንድ በኩል የሥራ አጡ ቁጥር ከፍተኛነትና በሌላም ያረጀው የሕብረተሰቡ ክፍል እየጨመረ መሄድ ነው። እንግዲህ በአጠቃላይ ለሚቀጥለው ዓመት የተተነበየው የዕድገት አዝማሚያ ዘላቂነት እንዲያገኝ ከመንግሥታዊ ዕዳ ቅነሣ ጋር አብሮ መራመድ የሚኖርበት ይመስላል። ይህ ለመሆኑ ወይም ለመቻሉ ግን ዛሬ እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር በጣሙን የሚያዳግት ነው።

የጀርመንና የካታር የባቡር ሃዲድ ዝርጊያ ውል

ለጀርመን የግንቢያ ኩባንያዎች በሌላ በኩል በቀውጢው የኤኮኖሚ ቀውስ ዘመን ቢቀር በመጠኑ ያልተጠበቀ ሲሣይ መውረዱም አልቀረም። የጀርመን የምድር ባቡር ተቋም ዶቼ-ባንና ሌሎች የግንቢያ ኩባንያዎች ባለፈው ሣምንት ካታር ውስጥ የሕዝብና የጭነት ባቡር ሃዲድ መረብ ለመዘርጋት 17 ሚሊያርድ ኤውሮ የሚያወጣ ታላቅ ውል ተፈራርመዋል። ፕሮዤውን ታላቅ የሚያደርገው በተቀረው የአረቡ ዓለም ጭምር በመዛመት የረጅም ጊዜ የገቢ ምንጭ ሊሆን መቻሉም ነው። የባሕረ ሰላጤውን ኤሚር ግዛት የምድር ባቡር ልማት ኩባንያ ለመገንባት ባለፈው ዕሑድ በተፈረመው ታሪካዊ ግምት በተሰጠው ውል መሠረት ዶቼ-ባን 49 በመቶ፤ ካታሪ-ዲያር የተሰኘው የካታር መንግሥታዊ ኩባንያ ደግሞ 51 ከመቶ ድርሻ ይኖራቸዋል። ፕሮዠው በጀርመን የምድር ባቡር ኩባንያ ታሪክ ውስጥ ታላቁ ሲሆን በዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ለተጎዱት የአገሪቱ ኩባንያዎች ጠቀሜታው እጅግ ከፍተኛ ነው።

የአረቡ ዓለም ሼይኮች በምዕራቡ ዓለም የክፉ ጊዜ መድህን ከሆኑ ሰንበት ብለዋል። ዛሬ ዳይምለርን በመሰለው ታላቅ የአውቶሞቢል ኩባንያ፣ በክሬዲት-ስዊስ ባንክና ሌሎችም የካፒታል ባለድርሻዎች ናቸው። የወቅቱን የምድር ባቡር ውል በተመለከተ የካታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼይክ-ሃማድ-አል-ታኒ እንዳሉት የድርሻው ይዞታ በረጅም ጊዜ የሚታይ ነው። የምንዛሪ ዋጋ ከወደቀ ካታር ድርሻዋን ከፍ ታድጋለች። በስዊሱ ባንክ ውስጥም የሆነው ይሄው ነው። ካታር በረጅም ጊዜ ባላት የልማት ዕቅድ በራሷ የአየር ማረፊያና የወደብ ግንቢያዎች ላይም ሰፊ መዋዕለ ነዋይ ታፈሳለች። እስካሁን በኤሚሯ ግዛት በሰፊው የሚጎለው ፈጣን የሰውና የዕቃ ማመላለሻ የባቡር ሃዲድ መረብ ነው። የዚህ ማመላለሻ ዘዴ አለመኖር እያደር ችግር ማስከተሉም እየጎላ መሄዱ አልቀረም። የግልና የጭነት ተሽከርካሪዎች መበራከት የመንገድ መጨናነቅንና የአየር ብክለትን ነው ያስከተለው። ይህ ደግሞ የተፋጠነ መፍትሄን የሚጠይቅ ጉዳይ ሆኗል።

ካታርን ወደፊት ከጎረቤቷ ከባሕሬይን ጋር ሊያገናኝ የታቀደው ዘመናዊ የምድር ባቡር በሰዓት 350 ኪሎሜትር የሚገሰግስ ይሆናል። ከዚሁ ሌላ በባሕር ላይ 45 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው ድልድል ሊታነጽ ሲወጠን የዋና ከተማይቱን የዶሃን አየር ጣቢያ ከማዕከሉ በሃዲድ ለማገናኘት ነው የታሰበው። የባሕረ-ሰላጤው ሃብታም አገሮች ለዚህ እርግጥ ፍላጎቱ ብቻ ሣይሆን የገንዘቡም አቅም አላቸው። ካታር በረጅም ጊዜ ርቃ ለማሰቧና አማራጭ የዕድገት መንገድ ለመሻቷ ዋናው ምክንያት የዛሬው ሃብት ምንጭ ነዳጅ ዘይት በሚቀጥሉት አሠርተ-ዓመታት እየተሟጠጠ የሚሄድ መሆኑ ነው። ካታርና መሰሎቿ እንግዲህ በዱባይ የኢንዱስትሪ አማካሪ የሆኑት ብሪታ ሃድለር እንደሚሉት የራሳቸውን የፊናንስ ኢንዱስትሪ ለመገንባትና የዓለም የምርት መተላለፊያ ለመሆን የሚያበቃ ብቃትን ለማስፈን ተነስተዋል።

“አካባቢው እዚህ ለተለያዩት የዓለም ክፍላት መተላለፊያ በር ነው። የንግድ ሰዎች ከዓለም ዙሪያ ይጎርፉበታል”

ዱባይ ውስጥ ባለፈው መስከረም በዓለም ላይ ከሁሉም ዘመናዊ የሆነው የምድር ውስጥ ባቡር መስመር መከፈቱ ይታወቃል። ታላቅ አየር ጣቢያም በመታነጽ ላይ ነው። እነዚህ ፕሮዤዎች እንዲሁ ለኩራትና ለመታየት የተወጠኑ አይደሉም። የአየር ጣቢያው ፕሮዤ ሃላፊ ሼይክ-አሕመድ-አል-ማክቱም እንደሚያስረዱት በአገልግሎቱ ዘርፍ ኢንዱስትሪ ላይ የተያዘው የግንቢያ መስፋፋት ትልቅ የገቢ ምንጭ በመሆኑ ነው። እርግጥ ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በባሕረ-ሰላጤው አገሮች ላይም ተጽዕኖ ሳያደርግ አልቀረም። ከባድ የገንዘብ ኪሣራን አድርሷል። ይሁንና የተንበረከከለት የለም። ይህ ደግሞ የነዚህ ከነዳጅ ዘይት ጥገኝነት ለመላቀቅ የተነሱት ትናንሽ መንግሥታት መለያ እየሆነ በመሄድ ላይ ነው። በዚህ ሂደት የጀርመን የምድር ባቡር ኩባንያም የረጅም ጊዜ ተጠቃሚ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም።

MM/DW