1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ

ሰኞ፣ ግንቦት 27 2004

ፖላንድና ኡክራኒያ በጋራ የሚያስተናግዱት የዘንድሮው የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በፊታችን አርብ በደመቀ ስነ ስርዓት ይከፈታል።

https://p.dw.com/p/157ka

ላንድና ኡክራኒያ በጋራ የሚያስተናግዱት የዘንድሮው የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በፊታችን አርብ በደመቀ ስነ ስርዓት ይከፈታል። ውድድሩ በአራት ምድቦች ተከፍሎ የሚጀመር ሲሆን ከተከታዩ ሩብ ፍጻሜ ዙር ጀምሮ የሚካሄደው በጥሎ ማለፍ መልክ ነው። መክፈቻው ግጥሚያ በምድብ-አንድ በፖላንድና በግሪክ መካከል የሚካሄድ ሲሆን ፖላንድ እንደ አስተናጋጅ አገር በሕዝቧ ፊት ትልቅ ዕርምጃ የማድረግ ተሥፋ ጥላለች።

ፖላንድ ላቶንና ዥሙዳን በመሳሰሉት ድንቅ ተጫዋቾቿ ዘመን በጎርጎሮሳውያኑ 1972 እና 1982 በዓለም ዋንጫ ውድድር ሶሥተኛ በመሆን ግሩም ወጤት ካስመዘገበች ወዲህ ብዙ ጊዜ አልፏል። ቀደም ባሉት የዓለምና የአውሮፓ ዋንጫ ውድድሮች ገና በመጀመሪያው የምድብ ዙር ስንብት ማድረጓ ነው የሚታወሰው። ፖላንድ በምድብ-አንድ ውስጥ ከግሪክ፣ ከቼክ ሬፑብሊክና ከሩሢያ ጋር ስትመደብ በመሠረቱ ወደ ሩብ ፍጻሜው ከሚያልፉት ሁለት አገሮች አንዱ መሆኑ የሚከብዳት አይመስልም።

ለዚህም ተሥፋ የሚሰጠው አገሪቱ የጀርመኑን ቀደምት ክለብ ቦሩሢያ ዶርትሙንድን በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ ለሻምፒዮንነት ያበቁትን ሌቫንዶቭስኪን፣ ፒሽቼክንና ብላሽኮቭስኪን የመሳሰሉ ከዋክብት ማፍራቷ ነው። ብሄራዊው ቡድን ለረጅም ጊዜ እንዲህ ጠንካራ የሆኑ ተጫዋቾች አልነበሩትም። አሠልጣኙ ዝሙዳም በወቅቱ በነዚሁ ላይ ነው ትልቅ የስኬት ተሥፋ የጣለው። ለማንኛውም በምድቡ ውስጥ ሩሢያ ከሁሉም ጠንካራዋ እንደሆነች ይታመናል።

ምድብ-አንድ እንግዲህ በታዛቢዎች ግምት በንጽጽር ቀለል ያለው ሲሆን ምድብ-ሁለት በአንጻሩ እጅግ ጠንካራው ነው። የሁለት ጊዜዋ የአውሮፓ ሻምፒዮን ጀርመን፣ ፖርቱጋል፣ ኔዘርላንድና ዴንማርክ በአንድ ላይ ተመድበዋል። በዚህ ምድብ ውስጥ እያንዳንዱ ግጥሚያ የፍጻሜን ያህል የሚሆን ነው የሚመስለው። ዘንድሮ ከስፓኝ ጋር የዋንጫ ባለቤት ይሆናሉ ተብለው ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው ሶሥት ሃገራት መካከል ሁለቱ ጀርመንና ኔዘርላንድ በዚህ ምድብ ውስጥ መገኘታቸው የምድቡን ከባድነት ይበልጥ ጉልህ ያደርገዋል።

ያም ሆነ ይህ ለጀርመን ቡድን ቀደምቱ ተልዕኮው ዋንጫዋን ይዞ ወደ አገር መመለሱ ነው። ብሄራዊው ቡድን የመጨረሻ የአውሮፓ ዋንጫውን እንግሊዝ ውስጥ ካገኘ ወዲህ 16 ዓመታት ሲያልፉ አሠልጣኙ የአኺም ሉቭ አሁን ለጥቂት ሲያመልጥ የቆየው ድል መሳካት እንዳለበት ነው የሚያምነው። በነገራችን ላይ ጀርመን ባለፉት የአውሮፓና የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ለፍጻሜ ደርሳ ሁለቴም በስፓን መሸነፏ የሚታወስ ነው።

«እስካሁን በ 2008 እና በ 2010 ዋንጫው በጣም ለጥቂት ነበር ያመለጠን። እናም እርግጥ ይህን ለመለወጥ አሁን ተከታይ ዕርምጃ ማድረግ ይኖርብናል»

የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሺን ፕሬዚደንት ቮልፍጋንግ ኒርስባህ በበኩላቸው የምድቡን ጠንካራነት ግምት ውስጥ በማስገባት የዋንጫው ተልዕኮ በአጭሩ ሊቀጭ መቻሉንም ይናገራሉ።

«ሁሉም ነገር ሊያጋጥም ይችላል። በመጀመሪያው ዙር ልንወጣም እንችላለን። ግን ይህ የሚሆን አይመስለኝም። ይልቁንም የአውሮፓ ሻምፒዮን ልንሆን እንችላለን»

Flash-Galerie Teilnehmer der Fußball-Europameisterschaft 2012 Deutschland
ምስል picture alliance/Sven Simon

ይህን በጊዜው እንደርስበታለን፤ ጀርመንን ካነሣን አይቀር ሁለቱ ኮከብ አጥቂዎች ሚሮስላቭ ክሎዘና ሉካስ ፖዶልስኪ በትውልድ ፖላንዳዊ በመሆናቸው ልባቸው ሁለት ቦታ የሚመታ መሆኑ የማይቀር ነው። እነዚህ ተጫዋቾች በፖላንድ ተወልደው በዚህ በጀርመን ያደጉ ሲሆን ቢቀር በሁለቱ ሃገራት መካከል አገናኝ ድልድይ መሆኑ እንደሚሳካላቸው ተሥፋ እናደርጋለን። በተቀረ ሁለቱ ቡድኖች በውድድሩ ሂደት እርስበርስ ከተገናኙ አጋጣሚው ለክሎዘም ሆን ለፖዶልስኪ ቀላል አይሆንም። ግን እንደ ነገሩ ሊወጡት የሚችሉትም ነው።

ምድብ-ሶሥት ውስጥ የአውሮፓና የዓለም ሻምፒዮን ስፓኝ እንዲሁም ኢጣሊያ ወደ ፊት የመዝለቅ የላቀ ዕድል የሚሰጣቸው ቀደምቱ ሲሆኑ ክሮኤሺያና አየርላንድም ምናልባት ያልተጠበቀ ስኬት ሊያገኙ ይችላሉ። ለስፓኝ የሬያልና የባርሤሎና ከዋክብትም ሆነ ለኢጣሊያ ብሄራዊ ቡድን የምድቡ ውድድር ዝም ብሎ ቀላል ሽርሽር አይሆንም። በሌላ

በኩል የኢጣሊያ ብሄራዊ ቡድን በአውሮፓው ዋንጫ ውድድር ዋዜማ በውርርድ ማፊያዎች የጨዋታን ውጤት በሕገ-ወጥ መንገድ የመወሰን ድርጊት ተጫዋቾች በመጠርጠራቸው ውዥምብር ውስጥ ገብቶ ነው የከረመው።

ፖሊስ መረጃ ለማግኘት በብሄራዊው ቡድን ማሰልጠኛ ሰፈር ምርመራና ፍተሻ ሲያካሂድ የኢጣሊያ እግር ካስ ፌደሬሺን ተከላካዩን ዶሜኒኮ ክሪቺቶን በማጭበርበሩ ድርጊት በመጠርጠር ከቡድኑ እስከማስገድ ደርሷል። በፍተሻው በጠቅላላው 19 የአንደኛና የሁለተኛ ዲቪዚዮን ባልደረቦች ተይዘዋል። በላሢዮ ሮማና በሌቼ ግጥሚያ ብቻ ማፊያው ሁለት ሚሊዮን ኤውሮ ሲያገኝ ተጫዋቾቹን ለመግዛት 600 ሺህ ኤውሮ መውጣቱን ነው የፌደሬሺኑ መርማሪ ኮሚቴ ያስታወቀው። እንግዲህ የወቅቱ ውዥምብር በቡድኑ ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ እንደሚኖረው እያደር የምናየው ይሆናል።

ምድብ-አራት ውስጥ ሁለተኛዋ አስተናጋጅ ኡክራኒያ፣ ፈረንሣይ፣ እንግሊዝና ስዊድን በአንድ ተቀምጠዋል። በዚህ ምድብ ውስጥ እንግሊዝና ፈረንሣይ በመጀመሪያ የሚገናኙ ሲሆን እንበል በወረቀት ደረጃ ወደፊት የመዝለቅ የበለጠ ዕድል የሚሰጣቸውም ሁለቱ ናቸው። ሁለቱም በደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ወቅት የጎደፈ ዝናቸውን በማደስ ጠንካራ ግፊት ነው ወደ ውድድሩ የተጓዙት። ታዲያ ይሄው ይሳካላቸው ይሆን? ጠብቆ መታዘቡ ግድ ነው።

እንግዲህ የአራቱ አውሮፓ ሻምፒዮና ምድቦች ይዞታ በአጭሩ ይህን የመሰለ ሲሆን የአውሮፓው ዋንጫ ውድድር በኡክራኒያ የሰብዓዊ መብት ይዞታ የተነሣ ከጨዋታው ተሳትፎ የመቆጠብን ጥያቄና ክርክር አስነስቶ መቆየቱም ይታወቃል። ስለ ኡክራኒያ ከብርቱካናማው ዓብዮት ወዲህ ያለፉትን ሣምንታት ያህል በተለይም በምዕራቡ ዓለም ብዙ የተወራበት ጊዜ የለም። ለዚህም ምክንያት የሆነው በእሥራት ላይ የሚገኙት የቀድሞዋ የኡክራኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዩሊያ ቲሞሼንኮ የረሃብ አድማ ማድረጋቸውና አሳሳቢ የጤንነት ሁኔታ ላይ መውደቃቸው ነበር። ሆኖም አሁን በመጨረሻ እንደሚታየው ከውድድሩ የሚቀር የለም።

በእግር ኳሱ ዓለም ከአውሮፓ ባሻገር በአፍሪቃና በላቲን አሜሪካም የተለያዩ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ተካሂደዋል። በአፍሪቃው ማጣሪያ ትናንት ናይጄሪያ ናሚቢያን በዘገየ ሰዓት 1-0 በመርታት ጠቃሚ ነጥቦችን ስታድን በምድብ-አንድ ውስጥ ደቡብ አፍሪቃ ደግሞ በገዛ ሜዳዋ ከኢትዮጵያ 1-1 በሆነ ውጤት ተወስናለች። ከአሥሩ ምድቦች ውጤቶች የተቀሩትን ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ፤ አይቮሪ ኮስት ከታንዛኒያ 2-0፤ ሱዳን ከአፍሪቃ ሻምፒዮን ዛምቢያ እንዲሁ 2-0፤ ካሜሩን ከዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ 1-0፤ ዚምባብዌ ከጊኒ 0-1፤ እንዲሁም ሤኔጋል ከላይቤሪያ 3-1 ተለያይተዋል።

በደቡብ አሜሪካ ምድብ ውስጥ ደግሞ ትናንት አርጄንቲና ከኤኩዋዶር 4-0፤ ኡሩጉዋይ ከቬኔዙዌላ 1-1፤ ቦሊቪያ ከቺሌ 0-2፤ እንዲሁም ፔሩ ከኮሉምቢያ 0-1 ተለያይተዋል። ቀደም ሲል አርጄንቲና ቺሌን 4-1፤ ኡሩጉዋይ ቦሊቪያን 4-2፤ ኤኩዋዶር ከቬኔዙዌላ 2-0፤ ፓራጉዋይ ከኡሩጉዋይ 1-1 ተለያይተው ነበር። በወቅቱ ምድቡን አርጄንቲና በአሥር ነጥቦች የምትመራ ሲሆን ቺሌ በዘጠኝ ነጥቦች ሁለተኛ ናት፤ ኡሩጉዋይና ቬኔዜዌላ ደግሞ በእኩል ስምንት ነጥቦች ሶሥተኛና አራተኛ ሆነው ይከተላሉ። ከምድቡ ለዓለም ዋንጫው በቀጥታ የሚያልፉት አራት ሃገራት ሲሆኑ አምሥተኛው ከማዕከላዊና ሰሜን አሜሪካ አራተኛ ጋር በመጋጠም ወደፊት የመራምድ የመጨረሻ ዕድል አለው።

Leichtathletik WM Daegu 2011 Mo Farah
ምስል ap

አትሌቲክስ

ሰንበቱን በአሜሪካ በኦይገን-ኦሬገን በተካሄደ የዳያመንድ ሊግ ውድድር ጥሩነሽ ዲባባ የአሥር ሺህ ሜትር አሸናፊ በመሆን የለንደን ኦሎምፒክ ተቃርቦ ሳለ በግሩም ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ አስመስክራለች። በመቶ፣ ሁለት መቶና አራት መቶ ሜትር ሩጫ የአሜሪካ አትሌቶች በወንዶችና በሴቶችም አይለው ሲታዩ በስምንት መቶ ሜትር የሱዳኑ አቡባከር ካኪ ኢትዮጵያዊውን የአዳራሽ ውስጥ የዓለም ሻምፒዮን መሐመድ አማንን ለጥቂት ቀድሞ አሸንፏል። በማይል ሩጫ ኬንያዊው አስቤል ኪፕሮፕ ሲያሸንፍ ሩጫውን በሁለተኝነት የፈጸመው መኮንን ገ/መድህን ነው።

በአምሥት ሺህ ሜትር ደግሞ ድሉ ከሶማሊያ የመነጨው የብሪታኒያ አትሌት የሞ ፋራህ ነበር። በዚሁ ሩጫ ኬንያዊው ኢሢያህ ኮች ሁለተኛ ሲወጣ አሜሪካዊው ኒክ ሩፕ ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል። በሴቶች ሶሥት ሺህ ሜትር የሞሮኮዋ ማሪየም ሤልሱሊ ስታሸንፍ ከንያዊቱ ሤሊይ ኪፕየጎ ሩጫውን በሁለተኝነት ፈጽማለች። በአሥር ሺህ ሜትር ከጥሩነሽ ዲባባ ድል በተጨማሪ በላይነሽ ኦልጂራም ሶሥተኛ በመውጣት ግሩም ወጤት አስመዝግባለች። በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክልም እንዲሁ ሶፊያ አሰፋና ሕይወት አያሌው ሁለተኛና ሶሥተኛ ሆነዋል። አንደኛ የወጣችው ኬንያዊቱ ሚልካህ ቼይዋ ነበረች።

Tennis Australian Open Djokovic Nadal
ምስል dapd

ቴኒስ

በፓሪሱ ዓለምአቀፍ የቴኒስ ውድድር በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ በወንዶችና በሴቶች ቀደምቱ ከሆኑት ተጫዋቾች መካከል የሰርቢያው ኖቫክ ጆኮቪች ወደ ሩብ ፍጻሜው ዙር መሻገሩ እንደምንም ሲሳካለት የቤላሩሷ ቪክቶሪያ አዛሬንካ በአንጻሩ ቀድሞ መሰናበቱ ግድ ሆኖባታል። ጆኮቪች በፓሪስ-ኦፕን ለአራተኛ ጊዜ በተከታታይ ባለድል ለመሆን ያለውን ዕድል የጠበቀው የኢጣሊያ ተጋጣሚውን አንድሬያስ ሤፒን በአምሥት ምድብ ጨዋታ በማሸነፍ ነው።

ጆኮቪች በመጀመሪያው ምድብ ሲሸነፍ ያልተጠበቀ የውድቀት አደጋ ለአጭር ጊዜም ቢሆን አንዣቦበት ነበር። ቪክቶሪያ አዛሬንካ በአንጻሩ በስሎቫኳ በዶሚኒካ ቺቡልኮቫ በሁለት ምድብ ጨዋታ ተሸንፋ በአራተኛው ዙር ከውድድሩ ስንብት አድርጋለች። ከዚሁ ሌላ የስዊዙ ሮጀር ፌደረር የቤልጂግ ተጋጣሚውን ዴቪድ ጋፊንን በማሸነፍ በአጭር ከመቅረት ማምለጡ ተሳክቶለታል። በተቀረ ጀርመናዊቱ አንጌሊክ ኬርበር የክሮኤሺያ ተጋጣሚዋን ፔትራ ማርቲችን ስታሸንፍ ኢጣሊያዊቱ ሣራ ኤራኒም ሩሢያዊቱን ስቬትላና ኩዝኔትሶቫን በለየለት ሁኔታ 6-0,7-5 ረትታለች።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ