1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ዋንጫ መክፈቻ

ዓርብ፣ ሰኔ 1 2004

በፖላንድና በኡክራኒያ የጋራ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 14ኛው የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር አሁን በቅርቡ ተከፍቷል።

https://p.dw.com/p/15Ail
ምስል dapd

በፖላንድና በኡክራኒያ የጋራ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 14ኛው የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር አሁን በቅርቡ ተከፍቷል። ጨዋታውን ዋርሶው ላይ በደመቀ ስነ ስርዓት የከፈቱት ከአስተናጋጆቹ አንዷ ፖላንድና ግሪክ ሲሆኑ ግጥሚያውም ከጥቂት ደቂቃዎች ወዲህ እየተካሄደ ነው።

ፖላንድ በዋርሶው፣ ግዳንስክ፣ ብሬስላውና ፖዘን ስታዲዮሞችን በከፊል አዲስ ስታንጽና ያሉትንም ስታሻሽል ዘመናዊ አውራ ጎዳናን ጨምሮ ለዝግጅቱ 30 ሚሊያርድ ኤውሮ ገደማ ነው ያወጣችው። ታዲያ ስራው በጊዜው አልቆ ከዚህ መደረሱን አጠራጣሪ ያደረጉት ጥቂቶች አልነበሩም። አሁን በመጨረሻ ግን ዝግጅቱ በሚገባ ተጠናቆ ፖላንድ ለአኩሪ መስተንግዶ መብቃቷ ግልጽ ሲሆን ከአንግዲህ የሚቀረው የእግር ኳሱ ስኬት ብቻ ነው።

ከሰባኛዎቹ ዓመታት የነላቶ ታላቅ ዘመን በኋላ የነበሩትን ዓመታት በድክመት ያሳለፈችው ፖላንድ አሁን በዋርሶው ብሄራዊ ስታዲዮም ከግሪክ ጋር እየተጫወተች ሲሆን በተለይም በጀርመን ቡንደስሊጋ ውስጥ ቦሩሢያ ዶርትሙንድን ለተከታታይ ሻምፒዮንነት ባበቁት ሌቫንዶቭስኪን በመሳሰሉት ኮከቦቿ መጠናከሯ ነው የሚታመነው። ዕውነትም በብሄራዊው ቡድን ውስጥ የጨዋታ መግባባት ካልጎደለ የፖላንድ ዕድል የከፋ የሚሆን አይመስልም።

ROBERT LEWANDOWSKI
ምስል picture alliance/augenklick/firo Sportphoto

በምድብ-አንድ ውስጥ ከግሪክ ሌላ ከሩሢያና ከቼክ ሬፑብሊክ በአንድ የተደለደለችው ፖላንድ በመሠረቱ ከመጀመሪያዎቹ ሁለት አገሮች አንዱ በመሆን ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ ጥሩ ዕድል ነው ያላት። ካልሆነ በታላቅ ደስታና ኩራት ከፍ ያለ ውጤት የማየት ትልቅ ተሥፋ የጣለውን የአገሪቱን ሕዝብ በጣም የሚያሳዝን ነው የሚሆነው። በነገራችን ላይ የምድቡ ጠንካራ አገር ናት የተባለችው ሩሢያም ዛሬ ምሽቱን ብሬስላው ውስጥ ከቼክ ሬፑብሊክ ትጋጠማለች።

በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ፍጽሜ ውድድር ከአራቱ የመጀመሪያ ዙር ምድቦች የሞት-የሽረት ምድብ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ጀርመን የምትገኝበት ምድብ-ሁለት ነው። ጀርመን በነገው ዕለት መክፈቻ ግጥሚያዋን ኡክራኒያ-ቻርኪቭ ውስጥ ከፖርቱጋል ጋር ታካሂዳለች። በዚሁ ኔዘርላንድና ዴንማርክም አብረው በተሰለፉበት ምድብ እያንዳንዱ ግጥሚያ የፍጻሜን ያህል በመሆኑ ጨዋታው እጅግ የደመቀና ትግል የተመላበት እንደሚሆንም ነው የሚጠበቀው።

የፖርቱጋሉ አሠልጣኝ ፓውሎ ቤንቶ በዚሁ ከባድ ምድብ ውስጥ ከጀርመን ጋር የሚደረገው መክፈቻ ግጥሚያ እጅግ ጠቃሚ ቢሆንም ቡድናቸው በመላው የምድብ ተጋጣሚዎቹ ላይ ማተኮር እንደሚገባው ነው ያስገነዘቡት።

«ከጀርመን ጋር የምናካሂደው ግጥሚያ የመጀመሪያው በመሆኑ እጅግ ጠቃሚ ነው። ግን በዚህ ግጥሚያ ላይ ብቻ በማተኮር የተቀሩትን ዴንማርክንና ኔዘርላንድን ችላ ልንል አንችልም። እርግጥ ነው፤ የጀርመን ቡድን ምን ዓይነት ጥንካሬና ባሕርይ እንዳለው እናውቃለን። እናም ተጫዋቾቻችንን ለዚሁ ለማዘጋጀትና ጥሩውን የስኬት መንገድ ለማግኘት ነው የምንፈልገው»

Mannschaftsbild Nationalmannschaft Deutschland EM 2012 Trainingslager
ምስል picture alliance / dpa

ምናልባትም የጨዋታውን ውጤት የሚወስነው የጎል ዕድልን በአግባብ መጠቀሙ ሊሆን ይችላል። በዚህ ረገድ ከልምድ ከተነሣን ጀርመን የተሻለው ዕድል ይኖራታል። ግን ክሪስቲያኖ ሮናልዶን የመሰለ ታላቅ ኮከብ ያላት ፖርቱጋልም በቀላሉ የምትታይ አትሆንም። የጀርመኑ ብሄራዊ ቡድን አምበል ፊሊፕ ላምም ቢሆን የሮናልዶ ጥንካሬ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ነው ያመለከተው።

«ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉት ድንቅ ተጫዋቾች አንዱ መሆኑ ይታወቃል። በፍጥነት ማታለል ጥንካሬው ሲሆን ቀልጣፋና በሁለት እግሩም መጫወት የሚችል ነው። ከዚሁ ሌላ ጥሩ ቅጣት ምት መምታት ይችላል። እናም እንደ ቡድን ይህን መከላከል ግድ ነው»

Bildergalerie Stars der EM 2012
ምስል picture-alliance/dpa

በእርግጥም ሮናልዶ ዘንድሮ በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ለሬያል ማድሪድ እንደተጫወተው ጥንካሬውን ከጠበቀ ለጀርመን አደገኛ ሊሆን የሚችል ነው። በተለይም ሌላው የፖርቱጋል ኮከብ ናኒ ከአካል ጉዳቱ አገግሞ በመመለሱ ቡድኑን በሚገባ እንደሚያጠናክር አንድና ሁለት የለውም። በረኛው ኤዱዋርዶ ካርቫሎም ቢሆን ቡድኑ በነገው ግጥሚያ ጠንካራ ሆኖ እንደሚቀርብ ነው የተናገረው።

«እጅግ ጠንካራ ግጥሚያ ነው የሚሆነው። ጀርመን በጣም ጥሩ ቡድን ነው ያላት። ግን እኛም የራሳችን መሣሪያ አለን። በጊዜው ጠንክረን እንደምንቀርብ አምናለሁ። በጨዋታው እንደምናሸንፍም ተሥፋ እናደርጋለን። ምክንያቱም ጨዋታው የመጀመሪያው በመሆኑ እጅግ ጠቃሚ ነው»

በሌላ በኩል የሶሥት ጊዜዋ የአውሮፓ ዋንጫ ባለቤት ጀርመንም ቢሆን ወደ ውድድሩ ያመራችው ከ 16 ዓመታት ወዲህ እንደገና በድል ወደ አገር ለመመለስ ቁርጠኛ በመሆን ነው። ቡድኑ መጨረሻው አይታወቅ እንጂ ቢቀር እስከግማሽ ፍጻሜው መግፋቱን ብዙ የሚጠራጠር የለም። ለማንኛውም የምድብ-ሶሥትና አራት መክፈቻ ግጥሚያዎች ደግሞ በፊታችን ዕሑድ ሰኞ ይካሄዳሉ።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሰ