1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ የስደተኞች አቀባበል መርህ

ረቡዕ፣ መስከረም 29 2006

ባለፈው ሐሙስ በኢጣልያዋ የላምፔዱዛ ደሴት አቅራቢያ ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ ሰጥማ ከሰወስት መቶ በላይ ሰዎች መሞታቸዉ የአውሮፓ ፖለቲከኞችን፥ የመብት ተሟጋቾችና የሐይማኖት መሪዎችን ዛሬም እያነጋገረ ነዉ።

https://p.dw.com/p/19x2f
ምስል Reuters

የኢጣሊያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ኤንሪኮ ሌታ እና አዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳት ሆዜ ማኑኤል ባሮሶ ዛሬ ላምፔዱዛን ሲጎበኙ ከመብት ተሟጋቾች ከፍተኛ ተቃዉሞ ገጥሟቸዋል።ያም ሆኖ ሁለቱ ፖለቲከኞች የሟቾቹን አስከሬን ተሠናብተዋል።የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በበኩላቸዉ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጳጳሳትን ለማነጋገር አቅደዋል።ትናንት ላክስምበርግ የተሰበሰቡት የአውሮፓ ህብረት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትኩረት ሰጥተው ከተነጋገሩበት ጉዳይ አንዱ የላምፔዱዛው አደጋ ነበር።ሚንስትሮቹ ተመሳሳይ አደጋ እንዳይደገም ሥለሚደረገዉ ጥንቃቄ መክረዋል። ይሁንና ሚኒስትሮቹ የሚሹት መፍትሔ ብዙ ወጪ የማያወጡበትን ነዉ። ባለፈው ሳምንት ላምፔዱዛ አቅራቢያ የደረሰው አደጋ እንዳይደገም ከአውሮፓ ህብረት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ምን ይጠበቃል? ስብሰባው ከመጀመሩ አስቀድሞ ለአውሮፓ ህብረት የጀርመን ተጠሪ የቀረበላቸው ጥያቄ ነበር። «የመጨረሻ ውሳኔ አይጠበቅም» የሚል ነበር መልሳቸው። በኢጣልያ አሳሳቢነት ችግሩ በንግግራቸው አጀንዳ ተይዞ ሚኒስትሮቹ ትናንት ማምሻውን በጉዳዩ ላይ ሃሳብ ተለዋውጠዋል፤ ተከራክረዋል። የኢጣልያ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አንጀሊኖ አልፋኖ የሰዎችን ህይወት

Friedrich EU Inennminister Treffen in Luxembourg 08.10.2013
ምስል picture-alliance/dpa

ለመታደግ አውሮፓ የእርዳታ እጁን ይዘርጋልን በማለት ተማፅነዋል። የአውሮፓ ህብረት የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሲሲሊያ ማልምስቶርምም አባል ሃገራት ከለላ እና ድጋፍ የሚያሻቸውን ሰዎች እንዲቀበሉ አሳስበዋል። የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሃንስ ፔተር ፍሪድሪሽ ግን ሰዎች ወደ አውሮፓ ድንበር ድርሽ እንዳይሉ በምህፃሩ FRONTEX የሚባለውን የአውሮፓ ድንበር አስተዳደር መስሪያ ቤት አሁን ማጠናከር ይገባናል የሚል አስተያየት ነበር የሰጡት። እነዚህን የመሳሰሉ የተለያዩ አስተያየቶች ቢቀርቡም የተላለፈ ውሳኔ ግን የለም። በሜዴትራንያን ባህር ስደተኞችን ያሳፈሩ ጀልባዎች አደጋ የደረሰባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው። ባለፉት 10 ዓመታት በአደገኛው የባህር ጉዞ አውሮፓ ለመድረስ ሲሞክሩ በረሃብ በውሃ ጥም በመስጠም እና በመቃጠል የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 20 ሺህ ይጠጋል። መሰል አደጋዎች በደረሱ ቁጥር ከአውሮፓ መዲናዎች ተደጋጋሚ ጥሪዎች ይሰማሉ። ሁሌም እንደሚሆነው የአውሮፓ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮችም ለወደፊቱ አደጋ እንዳይደርስ ለማድረግ ቃል ይገባሉ፤ ሆኖም አሳዛኝ አደጋዎች ተደጋግመው መድረሳቸው አልቀረም። ታዲያ ችግሩ ምን ይሆን ለሚለው ጥያቄ ማንፍሬድ ቬበር በአውሮፓ ፓርላማ የሃገር ውስጥ ፖለቲካ ጉዳዮች አዋቂ ችግሩን ከግንዛቤ ጉድለት ጋር ያያዙታል።

Italien EU Flüchtlinge Barroso und Letta auf Lampedusa Ankunft
ምስል picture-alliance/dpa

«በአውሮፓ ግንዛቤ የማስጨበጥ ባህል ያስፈልገናል። በሜዲቴራንያን ባህር ላይ ችግር የሚገጥማቸው መርከቦች የሚታደጋቸው ማጣታቸው እና የኢጣሊያ ሕግ እርዳታ የሚሰጡትን መቅጣቱ ሊሆን የሚችል አይደለም።»

Italien Lampedusa Schiffsunglück
ምስል picture alliance/AP Photo

እጎአ በ2002 የቀድሞው የኢጣልያ መሪ የሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ መንግሥት ያወጣው ሕግ ባህር ላይ ለአደጋ የተጋለጡ ስደተኞችን በመርዳት ወደ ኢጣልያ ምድር የሚያስገቡ መርከበኞችም ሆኑ አሣ አጥማጆች ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ በማሻገር ተጠያቂ ያደርጋል። ተጨማሪ ወጪ የሚያስከትሉትን ስደተኞች ላለመቀበል የሚፈልጉ ሃገራት ስደተኞችን በጥሩ ሁኔታ አይቀበሉም። የግሪክ የስደተኞች መጠለያዎችን መጥቀስ ይቻላል ሰብዓዊነት በጎደለው የግሪክ የስደተኞች ማጎሪያ ካምፖች አያያዝ ሰበብ የጀርመን ፍርድ ቤት ከግሪክ የሚመጡ ስደተኖች ወደ ግሪክ ተመልሰው እንዳይላኩ ከልክሏል። በጀርመን ግፊት በጸደቀው በደብሊኑ ስምምነት መሠረት አንድ ስደተኛ ተገን መጠየቅ የሚችለው መጀመሪያ በገባበት የአውሮፓ ሃገር ነው። ለምሳሌ መጀመሪያ ከገባ በኋላ ወደ ጀርመን ቢመጣ ወደ ግሪክ ተጠርዞ ይላካል። በዩጎዝላቪያው ጦርነት ወቅት ጀርመን ከአካባቢው በርካታ ስደተኖችን በተቀበለችበት ወቅት ሌሎች ጎረቤት ሃገራት ስደተኞችን እንዲከፋፈሉ የተደረገው ሙከራ ፈቃደኛ ባለመገኘቱ አልተሳካም። አሁንም ወደ አውሮፓ በብዛት የሚጎርፉትን ስደተኞች ሌሎቹም የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት እንዲቀበሉና የገንዘብ እርዳታ እንዲደረግላቸው ግሪክ ስፓኝና ኢጣልያ የሚያቀርቡት ጥሪ ከብዙዎቹ በኩል ሰሚ አላገኘም። የአውሮፓ ሃገራት ስለ ስደተኞች አያያዝ ደንብ ማውጣታቸው ድንበር ጠባቂው ፍሮንቴክስ ሕገ ወጥ ድንበር አሻጋሪዎችን ቢያድንም ወይም የአውሮፓ ህብረት ኮሚስዮን ከሰሜን አፍሪቃ ሃገራት ጋር የድንበር ቁጥጥር ላይ ቢደራደርም እና ለአባል ሃገራት ኮታ ቢያስቀምጥም ይህ መፍትሄ አይሆንም ይላሉ የስደተኞች ጉዳይ ተመራማሪና የአውሮፓ ህብረት አማካሪ ቤርንድ ሌበር «ሁሌም ወደ አውሮፓ መግባት የሚፈልጉት በኮታ ከሚፈቀደው በላይ ብዙዎች ናቸው። ያም ማለት በዚህ ዓይነት መንገድ ሕገ ወጥ ስደት የሚያስከትለውን ችግር ማስቆም አይቻልም።»

ባለፈው ሐሙስ የደረሰውን መሰል አደጋ ማስቀረት የሚቻለው የአውሮፓ ድንበሮች ክፍት ከሆኑ ብቻ ነው። ይህ ግን ገቢራዊ ሊሆን አይችልም እንደ ሌበር።

ሒሩት መለሠ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ