1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ የአዲስ ግኝት ሽልማት

ረቡዕ፣ ሰኔ 11 2006

ዋና ጽ/ ቤቱ በሙዑንሸን፤ ደቡብ ጀርመን የሚገኘው፣ የአውሮፓ የአዲዲስ ግኝቶች የባለቤትነት መብት መዝጋቢና ዕውቅና ሰጪው መ/ቤት ከተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት በአንድ ዓመት ውስጥ፤ የፈጠራ ውጤት ባለቤትነት መብት ለማግኘት፣ 265,690 ማመልከቻዎች ናቸው የደረሱት።

https://p.dw.com/p/1CLbb
ምስል imago

ይሁንና፣ ትናንት በርሊን ላይ ለ 9ኛ ጊዜ በተካሄደ፣ 300 የሽልማት እጩዎች ዝርዝር ቀርቦ 15 ለፍጻሜ በተገኙበት «የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ «ኦስካር» ፣ ለዘንድሮዎቹ የፈጠራ ሥራ ውድድር አሸናፊዎች የተመደበውን ሽልማት ሰጥቷል። በዚህ የፈጠራ ሥራም ሆነ ግኝት ነክ የሽልማት አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የ 94 ዓመቱ ጀርመናዊ አዛውንት ፣ አርቱር ፊሸር (Artur Fischer) በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ግኝቶቻቸው ብዛት፤ ጥራትና ጠቀሜታ፤ የዕድሜ ዘመን ሥራዎቻቸው ተመዝነው ፤ ዐቢይ ግምት የተሰጠው በመሆኑ ለሽልማት በቅተዋል።

Bildergalerie Europäischer Erfinderpreis Artur Fischer
ምስል picture-alliance/dpa

እ ጎ አ ከ 2010 አንስቶ የአውሮፓ የፈጠራ ውጤቶች የባለቤትነት መብት መዝጋቢው ድርጅት ፕሬዚዳን ት ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት፤ ምስተር Benoit Battistelli ፤ ትናንት በርሊን ላይ በሽልማት አሰጣጡ ሥነ ሥርዓት ላይ፤ ስለአዛውንቱ የብዙ የፈጠራ ሥራዎች ባለቤት አርቱር ፊሸር ባሰሙት ንግግር ላይ፤ ----

«አርቱር ፊሸር ፤ እንደ አንድ የፈጠራ ሥራዎች ባለቤትና እንደ ተሣካለት የኢንዱስትሪ ተቋም መሪ፤ በጀርመንና፤ በአውሮፓ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሚደነቁ በመሆናቸው ፤ በክብር እ ንደሚቀመጥ ዓርማ የሚታዩ ናቸው። ለጀርመን የመካከለኛ ደረጃ ኢንዱስትሪዎች ፤ አርአያም ሆነ ምልክት፤ ከአርቱር ፊሸር የሚቀድም የለም። በሕይወት ዘመናቸው ያላንዳች ማወላወል፤ በዘዴ፣ የአእምሮአቸውን የፈጠራ ሀብት ፣ ከኢምንቱ ውጤት አንስቶ በሥነ ሥርዓት ፤ በአግባቡ ተግባራዊ ያደረጉ ናቸው። በመሆኑም፤ በሕይወet ዘመናቸው ላከናወኗቸው ገንቢ ተግባራት ሁሉ ማጠቃለያ የሆነውን የዘንድሮውን ፤ እ ጎ አ የ 2014 የአውሮፓውያን የግኝት ጉዳይ ሽልማት ሳበረክትላቸው እጅግ ደስ እያለኝ ነው።» ብለዋል።

Bildergalerie Europäischer Erfinderpreis Charles W. Hull
ምስል EPO

«የአውሮፓውያን የፈጠራ ውጤት ኦስካር» የተሰኘውን ማለትም ከፍተኛ የፈጠራ ውጤት ሽልማት የተቀበሉት አርቱር ፊሸር በበኩላቸው፣ «የማወቅ ጉጉት ያለበት የልጅነት መንፈስ በውስጣችን መኖር ይገባዋል። የሚፈልጉና የሚያገኙ ሰዎች ሊኖሩን ይገባል። ዐዋቂ ሰዎች፣ የፈጠራ ሐሳብ የሚመነጨው ከአእምሮ ነው ባዮች ናቸውና» ሲሉ ተናግረዋል።

ያሁኑ የ 94 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ አርቱር ፊሸር፤ እ ጎ አ ታኅሳስ 31 ቀን 1919 ዓ ም፤ በባደን ቩርተምበርግ ፌደራል ክፍለ ሀገር፣ ጥቁር ጫካ(Schwarzwald)በተሰኘው አውራጃ ተወለዱ። ከ 1100 በላይ የፈጠራና ግንባታ ነክ የባለቤትነት መብት ያስመዘገቡ ሲሆን ፤ በተለይ በዓለም ዙሪያ ላቅ ያለ ዕውቅና ያገኙት፣ እ ጎ አበ 1958 ሥራ ላይ ባዋሉት፤ ንዑስ ሆኖም እጅግ ተፈላጊው የምሥማር ፕላስቲክ ቅርቃር ነው። ግድግዳ ፣ ጣሪያም ሆነ ወለል ላይ፤ በአሸዋ እተመረገ ግድግዳ ወይም ጣውላ ላይ በመዶሻ የሚመታ ምሥማር ፣ ይልቁንም በጠብመንጃ መፍቻ እንዲጠብቅ ማድረግ የሚቻልበትን ብልሃት፤ ማለትም የፕላስቲክ ቅርቃር እንዲሠራ በማድረጋቸው ነው። ይህ በቤት ግንባታ ረገድ የሚውለው ሥነ ቴክኒክ ፣ በህክምናውም ዘርፍ፤ ለምሳሌ ያህል ፣ የአጥንት ሥብራት ለሚያጋጥማቸው ሰዎች ተመሳሳይ ዘዴ በመጠቀም በተሻለ ሁኔታ መርዳት መቻሉ ነው የሚነገረው።

እ ጎ አ በ 1960ኛዎቹ ዓመታት ፤ አርቱር ፊሸር፤ ከካሜራ ጋር የሚያያዝ ፣ በጨለማ፣ ቅጽበታዊ ብርሃን የሚፈነጥቅና ፎቶግራፍ ማንሳት የሚያስችል ማሣሪያ በማስተዋወቅም ይታወቃሉ። ሌላው፣ ለሆነ ዓይነት ግንባታ በፕላስቲክ ናሙና መሰል የተለያዩ መገጣጠሚያ ክፍሎችን ከመያዣው ጋር ሠርቶ በማስተዋወቅም ስማቸው ይጠራል።

Bildergalerie Europäischer Erfinderpreis Aquaporin
ምስል EPO

እ ጎ አ በ 1948 ዓ ም ንዑስ የኢንዱስትሪ ተቋም ሲገነቡ የቀጠሯቸው ሠራተኞች ከ 240 አይበልጡም ነበር። አሁን ግን በዓለም ዙሪያ 4,000 ገደማ ደርሰዋል። አሁን በየዕለቱ የሚመረተው የፕላስቲክ ቅርቃር መጠን 14 ሚሊዮን ሲሆን እስካሁን በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ይኸው የፕላስቲክ ቅርቃር ሥራ ላይ ውሏል።

የጀርመን የፍጆታ ተጠቃሚዎች ጥቅም ጉዳይ ተመላካች ሚንስትሩ ሃይኮ ማስ በተገኙበት በተካሄደው የሽልማት አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት፣

በህክምናው ዘርፍ፣ ለሳንባ ነቀርሳ ፤ ከ 40 ዓመት ወዲህ ይበልጥ ፍቱን የተባለ ክኒን ያቀረቡት ቤልጅጋዊው ከን አንድሪስና ፈረንሳዊው ባልደረባቸው Jerome Guillemont ፣

እንዲሁም ከ«አነስተኛና መለስተኛ ድርጅቶች፤ » ፒትር ሆልም የንሰንና ዳንኤለ ኬለር የተባሉ ደንማርካውያን ተመራማሪዎች፤ የኃይል ምንጭ ቆጣቢ በሆነ ዘዴ «አኳፖሪን » የተባለ ልዩ የውሃ ማጣሪያ ሠርተው በማቅረባቸው ለሽልማት በቅተዋል። ይኸው የውሃ ማጣሪያ ፤ ውሃን በሚገባ የሚያጣራ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ንፁህ የሚጠጣ ውሃ ላጡ 1,5 ቢሊዮን ሰዎች ሊታደግ ይችል ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል።ከብሪታንያ፣ ክሪስቶፈር ቱማዙ በሰው ዘረመል ፤ የዘር ኅዋሳት መሠረታዊ በሽታ አለ --የለም ፣ ቤተ ሙከራ (ላበራተሪ ) ሳያስፈልግ ባፋጣኝ ምርመራ ማወቅ የሚቻልበትን ብልሃት በማግኘታቸው ለሽልማት በቅተዋል። ይህም ማለት፤ ጣት በምታክል ከኮምፒዩተር መረጃ መሰብሰቢያ ም ሆነ ወደ ኮምፒዩተር መልሶ ማስገቢያ መሣሪያ፤ በዘርመል ላይ ሳንክ መኖር አለመኖሩን ማወቅ አያዳግትም ማለት ነው።

ከአውሮፓ፣ ውጭ በ 3 ማዕዘናዊ ምስል ማተሚያ ሥነ ቴክኒክ ፤ አአሜሪካዊው ተመራማሪ ቻርለስ ደብልዩ ሃል ሌላው ለዚሁ የአውሮፓ የፈጠራ ውጤቶች ባለቤትነት መብት ነክ መ/ቤት ተሸላሚነት በቅተዋል።

Bildergalerie Europäischer Erfinderpreis Koen Andries
ምስል EPO

አርቱር ፊሸር በ 94 ዓመታቸው ፤ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ተግባራዊ ላደረጉአቸው ግኝቶች ሽልማታቸውን፣ ዋና ጽ/ቤቱ በሙዑንሸን ደቡብ ጀርመን ከሚገኘው በአውሮፓው የፈጠራ ወጤቶች የባላቤትነት መብት መዝጋቢው መ/ቤት ፤ በርሊን ላይ በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ለማግኘት የበቁ ሲሆን፤ በራሳቸው ስም የሚጠራ የሽልማት ድርጅትም መኖሩ የታወቀ ነው። ይኸው «አርቱር ፊሸር ኤርፊንደርፕራይስ /ኢንቬንተር ፕራይዝ» ከባደንቩርተምበርግ ፌደራል ክፍለ ሀገር ሌላ የግል ድርጅት ጋር በጥምረት የተመሠረተ ነው። በ የ 2 ዓመት አንድ ጊዜ በሚዘጋጀው ሽልማት ለሕብረተሰብ ጠቀሜታ የሚሰጡ አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን ለሚያስተዋውቁ ፤ እንደየደረጃው ከአንደኛ እስከ 3ኛ ፣ ለአንደኛው 10,000 ለሁለተኛው 7,500፤ ለ3ኛው ደግሞ 5,000 ዩውሮ ይሰጣል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በምርምር ለሚወዳደሩና ውጤት ለሚያሳዩ ተማሪዎች ሌላ ሽልማት ይሰጣል።

ተክሌ የኋላ

ኂሩት መለሰ