1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአየር ንብረት ለዉጥ ጉባኤ በቦን

ማክሰኞ፣ ግንቦት 25 2007

ዓለም የአየር ንብረት ለዉጥን አስመልክቶ መነጋገር ከጀመረ ሁለት አስርት ዓመታት አልፈዋል። የሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ተፅዕኖ እንዳስከተለዉ የሚገመተዉ የአየር ጠባይ ለዉጥ ተባብሶ ሳይንቲስቶቹ የሚገምቱት ሁሉ እንዳይደርስ ተግባራዊ ርምጃዎችን ለመዉሰድ ለመስማማት አሁንም እየተሰበሰ መነጋገሩን ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/1Faoj
UN-Klimakonferenz in Bonn
ምስል AFP/Getty Images/P. Stollarz

ከትናንት ጀምሮ እዚህ ቦን ከተማ የተመድ የአየር ንብረት ለዉጥን የሚመለከተዉ ጉባኤ ተጀምሯል። ተሰብሳቢዎቹ በመጪዉ ታኅሳስ ወር ፓሪስ ላይ ለሚካሄደዉ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለዉሳኔና ስምምነት የሚበጁ የሚሏቸዉን የመፍትሄ ሃሳቦች ያፈልቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። ብዙዎች ግን ከዚህ ስብሰባ ብዙም አይጠብቁም። ያዉ የተለመደዉ የመድረክ ንግግር፤ የጥናት ወረቀቶችና የተመራማሪዎች ድምጽ ተሰምቶ የሚያነሷቸዉ ነጥቦች መወያያ ሆነዉ እንደተከፈተ ሁሉ ይዘጋል ባዮች ናቸዉ።

ቀጣይዋ የተመድ የአየር ንብረት ለዉጥ ጉባኤ አስተናጋጅዋ የፈረንሳይ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር አነጋገርም ይህንን አጉልቶ ያመላከተ ነዉ። ሴጎሌኔ ሶጎሌኔ ሮያል ከቦኑ ጉባኤ ቀደም ብለዉ ለጋዜጠኞች እንደገለፁት የተመድ የሚያካሂዳቸዉና ያካሄዳቸዉ ጉባኤዎችና ድርድሮች በአሁኑ ወቅት ዓለም የተጋፈጠዉን የአየር ንብረት ለዉጥ ለመቀልበስ የሚያስችል ዉጤት ለማስገኘት በቂ አይደለም። እሳቸዉ እንደሚሉት ሁሉም በየግሉ ስለችግሩም ሆነ መፍትሄዉ ሲያወራ ይደመጣል፤ ሆኖም ግን ምንም ችግር እንደሌለ ብጤ መፍትሄዉን ተስማምቶ ለመወሰን ሂደቱ እየተጓተተ ነዉ። አክለዉም በጉባኤዉና አስቸኳይ በሆነዉ የአየር ንብረት ይዞታ መካከል ያለዉ ርቀትም በገሀድ ለሚታየዉ ችግር መባባስና የአየር ጠባይ ለዉጥ ሰለባ የሆኑ ሃገራትን ጉዳት መጥናት ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል። የተሰማቸዉን ፊትለፊት በመናገር የሚታወቁት የፈረንሳይዋ ሚኒስትር ሮያል እንደዉም ባለፉት ጉባኤዎች ስኬት ማየት ያልተቻለዉ በተደራዳሪዎቹ ድክመት መሆኑን ተናግረዋል።

UN-Klimakonferenz in Bonn
ምስል AFP/Getty Images/P. Stollarz

እዚህ በጀርመኗ ቦን ከተማ የመንግሥታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለዉጥ ተከታታይ ዘርፍ በሚያስተናግደዉ ጉባኤ 190 ሃገራት ተሳታፊ ናቸዉ። ከዚህ ጉባኤ እጅግም ትልቅ ዉጤት አልተጠበቀም። በዋናነት ግን አሁንም የበካይ ጋዞችን ልቀት በመቀነስ የመሬት ሙቀት ከሁለት ዲግሪ እንዳይበልጥ ሊያግባቡ የሚችሉ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማንሳት ይፈለጋል። እስከዛሬ በጉዳዩ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች የተነሱና በጉባኤዉ የተያዙት ሃሳቦች በተለይ ተግባራዊ ለማድረግ አቅምና ኃላፊነቱ ያላቸዉን ፖለቲከኞች ፈቃድኝነት የሚሹ ናቸዉ። የጀርመንየአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ሚንስትር ባርባራ ሄንድሪክስምበጉባዔው መክፈቻ ላይ ይህንኑ ነዉ ያመለከቱት።

« በያዝነው ምዕተ ዓመት ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ያካባቢ ጥበቃን የማይጎዳ የዓለም የምጣኔ ሀብት ያስፈልገናል። የዓለም የሙቀት መጠን ከሁለት ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንዳይበልጥ ለማድረግ የምናሳየው የጋራ ጥረታችን አበረታቺ እና ትክክለኛው ምልክት ነው። ዘላቂ የሆነ ስምምነት ለመድረስ ከፈለግን ይህን የአየር ሙቀትን የመገደቡ ሀሳብ በየብሔራዊ ዓላማችን ላይ ማካተት ይኖርብናል ብዬ አስባለሁ። »

ትናንት ለተሳታፊዎቹ ከጉባኤዉ አዎንታዊ ዉጤት እንደሚጠብቁ የጠቆሙት የፈረንሳይ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎሮን ፋቢዮስ በዚህ ስብሰባና ዉይይታቸዉ የሚደርሱባቸዉ ስምምነቶችም የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤትን ይሁንታ መጠበቅ እንደሌለባቸዉ በግልፅ መቀመጥ እንደሚኖርበት አሳስበዋል። ተደራዳሪዎቹ የእሳቸዉን እቅድ የሚከተሉ ከሆነም የበካይ ጋዞችን መጠን ለመቀነስ ያስችላል ሕጋዊ ማሰሪያ ያለዉ ዓለም አቀፍ ስምምነት የሚባለዉ ቀርቶ እያንዳንዱ ሀገር የበኩሉን ለማድረግ ሊቀበለዉ የሚችል መግባቢያ ላይ እንዲደረስ እንደሚሹ ነዉ የተነገረዉ። በአንፃሩ 28 አባላት ያሉት የአዉሮጳ ኅብረትና በዓለም ሙቀት መጨመር የዉቅያኖስ ዉኃ ከፍታ የሚያሰጋቸዉ የትናንሽ ደሴት ሃገራት ሕጋዉ ማሠሪያ ያለዉ ዓለም አቀፍ ስምምነት ለዚህ ችግር መፍትሄ ነዉ ያምናሉ። የፈንሳዩ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይህን ያሉበትን ምክንያት ለስብሰባዉ ተሳታፊዎች ሲያስረዱም ምንም እንኳን ሕጋዊ ተጠያቂነት ያለዉ ስምምነት እንዲደረስ የሚፈልጉት በርካቶች ቢሆኑም፤ ያ ስምምነት ወደዋሽንግተን ሲሻገር የሪፐብሊካንን ተቃዉሞ መቋቋም እንደማይችል ነዉ የገለፁት። ይህም ቢሆን ግን በስብሰባዉ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር አዎንታዊ ዉጤት እንደሚጠብቁ ነዉ ያመለከቱት፤

UN-Klimakonferenz in Bonn
የፈረንሳይ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርምስል AFP/Getty Images/P. Stollarz

«እኛ እንዲሆን የምንፈልገዉ አንድ ዉል ቢኖር በርካታ ሃገራት በምክር ቤታቸዉ ሊያጸድቁ መዉሰድ ይኖርባቸዋል። አንዳንድ ሃገራት አሉ ለምሳሌ ዩናይትድ ስቴትስ ፤ የምክር ቤቱን አብዛኛ መቀመጫ ሪፐብሊካን ስለያዙ ፖለቲካዉ ይብስ ዉስብስብ ያለ ነዉ። ምንም እንኳን በዚህ ላይ ዉሱን ስልጣን ያላቸዉ ፕሬዝደንት ኦባማ ጉዳዩን ወደፊት ለማራመድ ቢፈልጉም እነሱ እንዲህ ያለ ዉል አንፈልግም ሊሉ ይችላሉ። ስለዚህ በቦኑ ዉይይታችን እንዲህ ያለዉን ችግር ለመወጣት ለሁሉም ሊስማማ የሚችል ዉል ልናፈላልግ እንችላለን ብዩ አስባለሁ።»

ከዚህ በመነሳትም አንዳንዶች ግምታቸዉን እየሰነዘሩ ነዉ። ምናልባትም ከፓሪሱ ጉባኤ በመፍትሄነት ሊወጣ የሚችለዉ እቅድ አንዳንዶቹ ስምምነቶች በሕግ ታስረዉ በተለይ የበካይ ጋዞች ቅነሳዉ ግብ በእያንዳንዱ ሀገር እንዲወሰን የሚፈቅድ ሊሆን ይችላል የሚል። በኢንዱስትሪ የበለፀጉት ሃገራት በየጊዜዉ የየራሳቸዉን የብከላ መጠን ለመቀነስ በዚህ ነጥብ ከፍ አደርጋለሁ ሲሉ ይደመጣል። በዚህ ረገድ ሁሉም ባይሆኑም አንዳንድ የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ጥረት በምሳሌነት ይጠቀሳል።

የአየር ንብረት ለዉጥን ለመግታት ያስችላሉ የሚባሉ የተለያዩ ሃሳቦች በየጊዜዉ ይነሳሉ። የካርቦን ንግድ የሚባለዉ አንዱ ነዉ። ከቅሪተ አፅም በተፈጥሮ ሂደት እንደሚገኝ የሚታወቀዉ የነዳጅ ዘይት በዉስጡ ያካተተዉ ካርቦን ከባቢ አየርን አምቆ በማሞቅ ተጠያቂ ነዉ። እንደሳይንሱ የካርቦንን የአየር ዉስጥ ክምችት ለመቀነስ ደግሞ ዛፎች ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። የካርቦን ንግዱ ታዲያ ለከባቢ አየር መበከል እንብዛም አስተዋፅኦ የሌላቸዉ ድሀ ሃገራት ዛፍ በመትከል ዛፎቹ ለምግብ መሥሪያቸዉ ካርቦኑን እንዲመጡ፤ በኢንዱስትሪ የበለፀጉት ሃገራት ደግሞ ምድራቸዉን በደን እየሸፈኑ ብክለቱን ለመቀነስ ለሚጥሩ ሃገራት የገንዘብ ድጎማ እንዲያደርጉ ያደራድራል። ትናንት የቦኑ ጉባኤ ሲጀመርም በነዳጅ ዘይት ሻጭ ኩባንያዎች ይህን የሚያበረታታ ደብዳቤ ለአስተባባሪዎቹ ተልk/ል። ደብዳቤዉን የላኩት ስድስት የአዉሮጳ የነዳጅ ዘይትና ጋዝ ኩባንያዎች ናቸዉ፤ ሮያል ደች ሼል፤ BP፤ ኤኒ፤ ቶታል፤ ስታት ኦይል እና የBG ቡድን በመባል የሚታወቁት እነዚህ ነዳጅ ዘይት ሻጭ ኩባንያዎች ለቀጣዩ የአየር ንብረት ጉባኤ ሊቀመንበርና ለተመድ የአየር ንብረት ለዉጥ ተመልካች ዘርፍ ኃላፊ ክርስቲና ፊጎርስ በላኩት ደብዳቤ የካርቦን ንግዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም ሃገራት ተግባራዊ እንዲሆንና ቁጥጥርም እንዲረግበት ጠይቀዋል። ኩባንያዎቹ እንደሚሉትም እያንዳንዱ ሀገር የሚኖረዉን የካርቦን ልቀት መጠን እንዲወሰንና ከዚያ ባለፈ ቁጥርም ሊከፍል የሚገባዉ ዋጋ እንዲጨምር የሚደነግግ ሕግ እንዲኖር አሳስበዋ። የተፈጥሮ አካባቢን ከሚበክሉ ነገሮች ዋነኛዉን ንግድ የሚያካሂዱት እነዚህ ኩባንያዎች ያቀረቡት ሃሳብ መጥፎ የሚባል ባይሆንም ተግባራዊነቱ ግን ማጠያየቁ አልቀረም። ኩባንያዎቹ ግን ይህን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ለመነጋገር ከተመድና ከሚመለከታቸዉ ዓለም አቀፍ አካላት ጋ በቀጥታ መነጋገር እንፈልጋለን እያሉ ነዉ። ጥያቄያቸዉ ተቀባይነት ካገኘም ሌላዉ ወገን ሂደቱን የሚሰማዉ ይሆናል።

UN-Klimakonferenz in Bonn
ከጉባኡዉ ተሳታፊዎች በከፊልምስል AFP/Getty Images/P. Stollarz

በተቃራኒዉ ግን የበካይ ጋዞች በከባቢ አየር ዉስጥ መከማቸቱ ከዚህ ቀደም በበረሃነት በሚታወቁ አካባቢዎች የዝናቡ መጠን እንዲጨምር አድርጓል የሚሉ ጥናቶች እየወጡ ነዉ። እዚህ ጉባኤ ላይ የቀረበ አንድ ጥናት በጎርጎሪዮሳዊዉ 1970ዎችና 1980ዎቹ በድርቅ ምክንያት 100,000 ሰዎች ያለቁበት የአፍሪቃዉ የሳህል ግዛት አካባቢ በአየር ንብረት መዛባት ተጠቃሚ መሆኑን አመልክቷል። በብሪታንያዊ ሪዲንግ ዩኒቨርሲቲ የብሄራዊ የከባቢ አየር ሳይንስ ማዕከል ፕሮፌሰር የሆኑት ራዉን ሱቶን እንደሚሉት ለሌሎች ከፍተኛ ጉዳት እንዳስከተለ የሚታየዉ የበካይ ጋዞች ክምችት ከሴኔጋል እስከ ሱዳን ባሉ የደቡብ ሳህል አካባቢዎች የልምላሜ ምክንያት ሆኗል። ጥናታቸዉ በከባቢ አየር የበካይ ጋዞች ክምችት ርጥበትን በማስከትል ዝናብን እንደሚያበዛ ቢያመላክትም በሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት በዚሁ ምክንያት የመጣዉ የዝናብ እጥረትና ድርቅ አሳሳቢ መሆኑንም ማመላከቱ አልቀረም። እነዚህ አደገኛ ጋዞች ያስከትላሉ የሚባለዉን የከባቢ አየር ሙቀት መጨመር ችግር መሆኑን ለሚከራከሩ ወገኖች ሌላ ፈተና ሆኖ ቀርቧል። ያም ቢሆን የፈረንሳዩ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስብሰባዉ መንፈስ አዎንታዊ ነዉ ይላሉ፤

«የስብሰባው መንፈሥ አዎንታዊ ነው። እያንዳንዱ ተወካይ ስምምነት እንዲኖር የሚፈልግ ይመስለናል። ይህ በራሱ አዎንታዊ ነው። ይሁንና፣ ጥያቄዎቹ በጣም በጣም የተወሳሰቡ ናቸው፣ መገንዘብ ያለባችሁ ስምምነቱን መድረስ ያለባቸው 196 ቡድኖች መሆናቸውን እና በ196 ፓርቲዎች መካከል ገላጋይ ሀሳብ የመድረሱ ሂደትም ቀላል አለመሆኑን ነው። »

እርግጥም በዚህ ጉዳይ ላይ ከስምምነት የመድረሻዉ መንገድ አጭር ይሆናል ብሎ መገመት ቢያንስ አሁን ሲታይ የሚቻል አይመስልም። ስብሰባዉም ድርድሩም ቀጥሏል። ይህኛዉ ለ11ቀናት ይዘልቃል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ