1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአየር ንብረት ተመልካች ጉባዔ አጋማሽ

ሰኞ፣ ኅዳር 27 2008

የፊታችን አርብ በይፋ ያበቃል ተብሎ የሚጠበቀው በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የተመድ የአየር ንብረት ተመልካች ጉባዔ ዛሬ ተጋምሷል። የ195 ሃገራት ልዑካን የተሳተፉበት ይህ ጉባኤ ይበልጥ ተጠናክሮ እና ድርድሩም ተጧጥፎ እንደሚቀጥል ይጠበቃል። የድርድሩን መድረክ የሀገራቱ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች ዛሬ ተረክበዋል።

https://p.dw.com/p/1HIr9
Frankreich Klimakonferenz COP21 in Paris
ምስል Reuters/S. Mahe

[No title]

የሚነሱት ነጥቦች በርካታ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን እውን እስኪሆኑም ብዙ ጊዜ ይጠይቃሉ።ያለፈውን ሳምንት የፓሪስ የአየር ንብረት ተመልካች ጉባዔ ድርድርን ለሚገመግም ባለፉት ቀናት በርካታ አወንታዊ ስምምነቶች ላይ ተደርሷል ማለት ይችላል። የጀርመን የግሪን ፒስ ተጠሪ ማርቲን ካይዘር ፤ «ዋናዎቹ ድርድሮች ግን ገና ናቸው» ይላሉ። ለውይይት የቀረቡት ከ2500 የሚበልጡ ጥያቄዎች ነበሩ ። አሁን ግን ወደ 567 ዝቅ ተደርገዋል። በርካታ የመፍትሄ ሃሳቦችም ተሰንዝረዋል። ይሁንና አሁንም ብዙ ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች አሉ። በተለይ ከደሴት ሀገራት የቀረቡትን ጥያቄዎች የአየር ንብረት ጥበቃ ተመራማሪ ሬጊነ ጉንተር ያወድሳሉ።« ተጎጂዎቹ ሀገራት መጥፊያችንን ለሚያረጋግጥልን ነገር ለምን ሲባል ተስማምተን እንፈርማለን ሲሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በማሰማት አስጠንቅቀዋል። እስካሁን እንዲህ በግልፅ ተነግሮ አያውቅም ፤ለነገሩ አስፈላጊም ነበር። »

Frankreich Klimakonferenz COP21 in Paris
ምስል Reuters/S. Mahe

በበለፀጉ እና በመበልጸግ ላይ ባሉ ሀገራት መካከል አሁንም የወጪው ጉዳይ ላይ ከስምምነት አልተደረሰም፤ የበለፀጉት ሀገራት በዓመት ከ 80-90 ቢሊዮን ዮሮ ለመለገስ ቃል ቢገቡም በመበልፀግ ላይ የሚገኙት ሀገራት አሀዙን በስጋት ነው የሚመለከቱት። በጉባኤው ላይ ራሳቸውን የድሀ አገሮች ተወካይ አድርገው ያቀረቡት የህንዱ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ሀብታም ሀገሮች ግዴታቸውን ከፍለው እንዲወጡ አሳስበዋል። ቻይናም ብትሆን ከነዚሁ ተርታ ትሰለፋለች። ፈጣን እንደገት በማስመዝገብ ላይ ያለችው ቻይና መጠነ ሰፊ በካይ ጋዝ በመልቀቅ ለአየር ብክለት አስተዋፅኦ ብታደርግም፣ተጠያቂዎቹ ምዕራባዊያን እንደሆኑ ናቸው ስትል ነው የምትከራከረው። በአንድ ነጥብ ላይ ቢያንስ የበለጸጉት ሀገራት ከጋራ ነጥብ የደረሱ ይመስላል። ይህም የሙቀት መጠን እንደታቀደው ከሁለት ዲግሪ ሳይሆን ከ 1,5 ዲግሪ እንዳይበልጥ ገደብ ለማስቀመጥ ነው። የፓሪሱ ጉባኤ ዋና ዓላማ ግን ሊማ ፔሩ ላይ የተወሰነውን የሙቀት መጠን ከሁለት ዲግሪ እንዳይበልጥ የሚለው ነው። ይሁንና እስካሁን ቃል የተገቡት ይህንን ቁጥር ቢያንስ በ50 በመቶ ጥሰዋል። ይህ ለቱቫሉ የፓሲፊክ ደሴት ጠቅላይ ሚኒስትር እኔሌ ስፖአንጋ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው።« ለውጡን እያየነው ስለሆነ ትልቅ ዋጋ መክፈል ጀምረናል። ከደሴቶቼ ሶሥቱ ያለምግብ፣ ያለ ንጹህ ውኃ ይገኛሉ። የግብርና ሰብሎች በሳይክሎን ፓም አውሎ ንፋስ ወድመዋል። ይኼ ማስጠንቀቂያ ነው ብለው አያምኑም? ማንኛውም የሙቀት መጠን መጨመር ትልቅ ቀውስ ነው የሚሆነው።»

BdW Global Ideas Bild der Woche KW 49/2015 Perito Moreno Eisberg
ምስል Getty Images/M. Tama

በዚህ አባባል የጀርመን የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ዮህን ፍላስባርትም ይስማማሉ። ስለ የሙቀት መጠን እቅዱ ሲያወሩ ትናንሽ ደሴቶችንም ከግንዛቤ በመክተት ነው።« ሊማ ላይ የዓለም የሙቀት መጠን ከሁለት ዲግሪ እንዳይበልጥ በሚለው ተስማምተናል። ዕውን ማድረግ የምንፈልገውም ይህንኑ ነው። ሆኖም ሁለት ዲግሪውም ቢሆን እነዚህን ሀገራትን ከከፍተኛ የተፈጥሮ አደጋ እንደማያድናቸው ነው። ከዚህ ጋር አንድ የተጣመረ ነገር ማስተዋል ይቻላል። እና ሁለቱን ዲግሪ በ 1,5 መተካቱ አሳማኝ አይደለም። ምክንያቱም ይህን ለማድረግ ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ያስፈልጋል። ይህንን ደግሞ ብዙዎች አልተቀበሉትም።» በዚሁ የአየር ንብረት ጉባዔ የመጀመሪያ የስብሰባ አጋማሽም ኢትዮጵያን ጨምሮ አስር የአፍሪቃ አገሮች 31 ሚሊዮን ሔክታር የተራቆተ መሬት መልሶ ለማልማት ቃል መግባታቸው ተሰምቷል።

ባርባር ቬዝል /ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ