1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአየር ንብረት ጉዳይ ጠበብት ጉባዔ በሐምበርግ፤

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 5 2003

ፀሐይ ትወጣለች ? ወይስ በደመና ተሸፍና ብርሃኗንና ሙቀቷን ትነፍጋለች? በሚቀጥሉት ቀናት ሰሞኑን እንዳሳለፍነው ነፋሻነቱ ይቀጥላል ወይስ ይገታል።

https://p.dw.com/p/RHhS
ነፋስ፣ በምድረበዳ የአሸዋ ክምር ሲንድ፣ምስል fotolia

እነዚህንና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ፤ የአየር ንብረት ጉዳይ ተከታታይ ባለሙያዎች አዘውትረው የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ናቸው።

በጀርመን ሀገር የአየር ር ጠባይን አስመልክተው ጥናታዊ ትንበያ በማቅረብ የሚያገለግሉ፤ 20 ገደማ የሚሆኑ የግል ድርጅቶች አሉ። ሁሉም በአጠቃላይ በዓመት የ 30 ሚሊዮን ዩውሮ ትርፍ ያገናሉ። ከዚህ አገልግሎት ጋር የተያያዘው ንግድም እየተስፋፋ በመሄድ ላይ ነው። በሰሜን ጀርመን በምትገው ግዙፏ የወደብ ከተማ ሀምበርግ፤ መጠን ያለፈ የአየር ጠባይን የሚዳስስ ዐቢይ ጉባዔ ተከፍቷል።

የጀርመን የአየርና የአየር ንብረት የመረጃ ልውውጥ ጉዳይ ተቋም ባዘጋጀው 6 ኛ ዐቢይ ጉባዔ፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የተውጣጡ ከ 1,600 የሚበልጡ የሳይንስ፤ በተለይም የአየር ንብረት ጉዳይ ጠበብት፤ ትናንት ጉባዔው ከተከፈተበት ዕለት አንስቶ እስከ ዓርብ ድረስ ከ 80 በላይ የጥናት ውጤቶችን በማቅረብ ሐሳብ ይለዋወጣሉ።

በጉባዔው ከሚመከርባቸው ዋና - ዋና ጉዳዮች አንዱ፤ የአየር ንብረት ለውጥ፣ በከተሞችና መዳረሻዎች ኑዋሪዎች ላይ ሊያስከትል የሚችለው የሳንክ ዓይነት አንደኛው ነው። ፀሐይ፤ ደመና ዝንብና ነፋስም በሰፊው ይመከርባቸዋል።

የጀርመን የአየር ጠባይ ምርምር ድርጅት ሊቀመንበር ሄልሙት ማየር እንደሚሉት ከሆነ፣ እ ጎ አ ከ 2040 ዓ ም በኋላ፤ ደቡብና ምዕራብ አውሮፓን እ ጎ አ በ2003 ዓ ም አጋጥሞ የነበረው ዓይነት ሐሩር ከሞላ ጎደል አዘውትሮ ሳያሠጋው አይቀርም። ያኔ አጋጥሞ ለነበረውና ወደፊት በተከታታይ መከሠቱ አይቀርም ለሚባልለት ሐሩር ፤ የመኻል አውሮፓ ከተሞች የተዘጋጁ አይደሉምና ምን ይውጣቸዋል? ሆኗል አሁን ፣ ጥያቄውም ሆነ ሥጋቱ! በሐምበርግ ፣ የአየር ንብረት መረጃ ማዕከል ኀላፊ ጊ ብራሰ እንደገለጹት ከሆነ ፣ በዓለም ዙሪያ፤ በአየር መቆሸሽ ሳቢያ 1,8 ሚሊዮን ህዝብ ህይወቱን ያጣል። ከእነዚህ መካካል 600,000 ው ቻይናውያን ናቸው። በጀርመን ሀገርም፤ አየር ጋር የሚቀላቀለው ያን ያህል በዓይን የማይታይ አቧራ መጠን እየጨመረ መሄድ፣ የኑዋሪዎቹን ዕድሜ በአማካዩ በአንድ ዓመት ሊያሣጥር እንደሚችል ነው የተገለጠው።

ባለፉት 50 ዓመታት ስለአየር ጠባይ የሚነገረው ትንበያ ፤ የጀርመን የአየር ጠባይ ተከታታይ መ/ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ፓውል ቤከር እንደሚሉት ከሆነ፣ እጅግ ተሻሽሏል። በ 1960ኛዎቹ ዓመታት የአንድን ቀን ማለትም የ 24 ሰዓቱን የአየር ጠባይ ከሞላ ጎደል በከፊል ነበረ በትክክል መተንበይም ሆነ አስቀድሞ ማሳወቅ የሚቻለው። በአሁኑ ጊዜ ግን የ 5 ቀናትን የአየር ጠባይ አስቀድሞ ከሞላ ጎደል በሚያስተማምን ሁኔታ መግለጽም ሆነ መተንበይ አያዳግትም።

በሰሜን ጀርመን በኪል ከተማ የሚኖሩት የአየር ንብረት ጉዳይ ሊቅ ሞጂብ ላቲፍ ፣ የዓለም ን የአየር ንብረት መዛባት ለማስተካከል፤ የአቶም የኃይል ምንጭና የነዳጅ ዘይት አጠቃቀምን ማስወገድ ፣ የግድ ነው ይላሉ ። የአቶም ኃይል ምንጭ ፤ የአየር ንብረትን ይዞታ መዛባት ለማስወገድ ይበጃል መባሉ አጉል ፈሊጥ መሆኑን፤ አሁን፣ መላው ዓለም የሚመሠክረው ነው፤ በፍጹም ሊሆን አይችልም ተብሎ የታሰበውን ፤ የፉኩሺማው አደጋ አክሽፎታልና በማለትም ነው ሞጂብ ላቲፍ ያስገነዘቡት። የጀርመን የአንደኛው መሥመር የቴሌቭዥን አገልግሎት የአየር ንብረት ጉዳይ ባለሙያ እስቬን ፕሎዖገር፤ ከአቶም አጠቃቀም መውጣት ያስፈልጋል። የኢ,ር ንብረት መዛባት፤ የኃይል ምንጭ አጠቃቀም ለውጥን አስፈላጊነት የግድ ይላል የሚያሳዝነው ግን ስለወጥ አስፋላጊነት ለማሰብ ፤ በጃፓን የደረሰው ዓይነት ጥፋት እስኪከሠት መጠበቅ የሰዎች ባህርይ መሆኑ ነው። የአቶም የኃይል ማመንጫ አውታር አደጋ እንዳለበት አሁን አይደለም የሚታወቀው። ከዚህ ጥፋት ትምህርት እንደሚቀሠም ተስፋ ያደረጉት ፕሎዖገር፤ «አስተሰባባችን ዓለም አቀፍነት ይኑረው ተግባራችን ሀገራዊ ሊሆን ይችላል » ነው ያሉት።

መጪው ዘመን ፤ በታዳሽ የኃይል ምንጮች ላይ የሚያተኩር ነው የሚሆነው። በጀርመን በመላ፣ በሚተከሉ ትልልቅ ዓምዶች ላይ የሚያፏጩ ፉሪቶች ፣ ኤልክትሪክ ነው የሚያመነጩት። Clean Energy የተሰኘ ኩባንያ ያላቸው ቶማስ ፒልግራም፤ በነፋስና በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የራሳቸው አውታሮች አሏቸው። ስለዚህ ቶማስን የመሳሰሉ ሰዎች፣ በቀጣዮጩ ቀናት የነፋሱ ኃይል የቱን ያህል ጥንካሬ አለው? የፀሐይዋ ብርሃንና ሙቀትስ እስከምን ድረስ ነው? ለሚሉ ጥያቄዎች ትክክለኛውን ምላሽ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

«ለእኛ ፤ እጅግ ጠቃሚና ተፈላጊም ነው። እናም የትኛውን ዓይነት የኃይል ማመንጫ በምን ያህል መጠን መጠቀቀም እንደምንችል ማቀድ እንችላለን። ከሚያስፈልገን በላይ የኃይል ምንጭ ያለን መሆን አለመሆኑን ስለምናውቅ፤ ብዙ ስናገኝ ለገበያ እናቀርባለን። እጥረትም ካለበት ከገበያ መግዛት ይኖርብናል ማለት ነው። »

የጀርመን መንግሥት የሳይንስ ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ዲርክ ሜስነር በበኩላቸው፤ ፌደራሉ መንግሥት ፣ በቅርቡ ሳይንሳዊ መረጃ ያቀረበውን ቡድን መግለጫ ትልቅ ግምት የሰጠው ከመሆኑም ባሻገር፤ ከነዳጅ ዘይትና ከአቶም ኃይል ምንጭ በመራቅ፣ ወደፊት፤ በታዳሽ የኃይል ምንጭ ላይ እንደሚያተኩር፤ ዓለምም ፤ ኤኮኖሚዋም በአረንጓዴ ላይ ይመሠረታል የሚል አመለካከት እንዳለው አስረድተዋል።

«ከድፍድፍ ነዳጅ ዘይት የኃይል ምንጭ መውጣት አለብን፤ ሌላ አማራጭ የለንም። የኑክልየር ኃይል ምንጭ እጅግ አደገኛ ነው። ያም ሆኖ አንዱን ችግር ለማስወገድ ራስን አስገድዶ መፍትኄ መሻት ሌላ ችግር ሊያስከትል ይችላል።»

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ