የአድዋ ድልን የሚዘክር ዩንቨርሲቲ
ዓርብ፣ የካቲት 10 2009
ኢትዮጵያ ከ 121 አመት በፊት በአድዋ ተራሮች ላይ የተጎናጸፈችዉን ድል ለመዘከርና ለትዉልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ የሚያስችል የፓን አፍሪካ ዩንቨርሲቲ ፤በአድዋ ሊገነባ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገልጿል።የአድዋ ድል የመላዉ ኢትዮጵያዉያንና የአፍሪካዉያን ብሎም የጥቁር ህዝቦች ድል በመሆኑ፤ይህንን ድል ለመዘከር እስካሁን ከተሰሩ ስራወች በተጨማሪ ዩንቨርሲቲ ለመገንባት እቅድ መያዙን ለዶቼ ቬለ የገለጹት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብና የአለም አቀፍና ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ናቸዉ።
እንደ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ፤የአድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲን ለማቋቋም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ያካተተ በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሟል በዩንቨርሲቲዉ የአድዋ ጦርነትንና የተገዉን ድል እንዲሁም በጦርነቱ የተሳተፉ ኢትዮጵያዉያን ታሪክ ላይ ምርምርና ጥናት የሚደረግበት ነዉ።ግንባታዉ መቼ እና በምን ሁኔታ ይከናወናል የሚለዉን ግን ጥናቱ ሲጠናቀቅና ወደ ስራ ሲገባ በባለሙያወችና በኮሚቴዉ የሚገለጽ መሆኑን አቶ ገዛኸኝ ገልጸዋል።
ጦርነቱ ከተካሄደባቸዉና ድል ከተገኘባቸዉ የአድዋ ተራሮች ባሻገር ከአድዋ ድል ጋር ተያያዥነት ያላቸዉ ታሪኮችና ቦታዎችን ለማስታወስ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች ይሰራሉ ተብሏል።ከነዚህም ዉስጥ ለጦርነቱ መነሻ የሆነዉን የዉጫሌ ዉል የተፈረመበትን ቦታ ለመዘከር መታሰቡን አቶ ገዛኸኝ ተናግረዋል።
የአድዋ ድል ሲታሰብ ቦታዎቹንና ታሪኮችን ከመዘከር ባለፈ ድሉን ያስገኙ ጀግኖችን በማክበርና እዉቅና በመስጠት እንዲሁም ለትዉልድ በማስተላለፍ ረገድስ ምን እየተሰራ ነዉ? ብለን
ላነሳንላቸዉ ጥያቄ ፤እስካሁን የተሰራዉ በቂ አለመሆኑን ገልጸዉ ወደፊት ግን ዩንቨርሲቲዉን ጨምሮ ሌሎች በሚሰሩ የመታሰቢያ ስራወች እንደየ ታሪክ ድርሻቸዉ ቦታ የሚሰጣቸዉ መሆኑን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በመጭዉ የካቲት 23 ለ121ና ጊዜ ይከበራል። በአሉ በዋናነት በአድዋ ተራሮች የሚከበር ሲሆን በመላዉ ኢትዮጵያም በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ ይዉላል ሲል የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር ገለፃ ያመለክታል።
ፀሐይ ጫኔ
አርያም ተክሌ