1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃውያን ባርነትና ሰቆቃ በሊቢያ

ዓርብ፣ ኅዳር 22 2010

ሊቢያ ውስጥ ስደተኞች «የባርያ ፍንገላ» ይፈፀምባቸዋል በሚባልበት ባሁኑ ወቅት ዝምታ አይስፈልግም ሲሉ የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ኃላፊ ዦን ክላውድ ዩንከር ለዶይቸ ቬለ ተናገሩ። የመብት ተሟጋቾችና ለአፍሪቃውያን ተቆርቋሪ ተቋማት ኃላፊው ቀድሞውንም ቢሆን ሊቢያ ውስጥ ይከሰት የነበረውን ያውቃሉ ሲሉ ተችተዋል።

https://p.dw.com/p/2oX5j
Sklavenhandel mit Migranten in Libyen
ምስል Narciso Contreras, courtesy by Fondation Carmignac

የባርያ ፍንገላ በሊቢያ

በ21ኛው ክፍለ ዘመንም ሊቢያ ውስጥ የሰው ልጆች በባሪያ ፍንገላ ሲሰቃዩ የሚታይበት ቪዲዮ በመገናኛ ብዙኃን ከተሰራጨ ወዲህ ቁጣው ከየአቀጣጫው ተበራክቷል። ሞክታር ካማራ ጀርመን የሚገኘው የአፍሪቃውያን ማኅበረሰብ ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ ናቸው። ሊቢያ ውስጥ ስደተኞች በደልና ሰቆቃ እየደረሰባቸው ነው የሚለው ዜና መውጣቱን ተከትሎ ቅዳሜ ዕለት ለተቃውሞ በርሊን ወደሚገኝው የሊቢያ ኤምባሲ አቅንተው ነበር።

«ሊቢያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ለተንሰራፋው ለዚህ ሁሉ ቀውስ ሰበቡ የአውሮጳ ኅብረት ነው። የሊቢያ መንግሥት ከአውሮጳ ኅብረት ገንዘብ በገፍ ተልኮለታል፤ እናም ይህ የፋይናንስ ፈሰስ ሊቢያ ውስጥ አፍሪቃዉያን የሆኑ ሰዎችን ለባርነትና ለጭቆና የሚዳርጉ እና የሚገድሉ ሚሊሺያዎች እጅ ነው የገባው።»

በአርግጥ አፍሪቃውያኑ ፈላሲያን እንደቀድሞው በገፍ ወደ አውሮጳ መትመማቸው ቀንሶ ይሆንል፤ በግፍ የባርያ ፍንገላ ሰለባ መሆናቸው ግን መላ ዓለምን ጉድ አሰኘቷል። የአውሮጳ ኅብረት እና የአፍሪቃ ኅብረት ሃገራት መሪዎች በምዕራብ አፍሪቃዊቷ አይቮሪኮስት መዲና አቢጃን ሊመክሩ ስብሰባ የመቀመጣቸው አንዱ ዋነኛ አጀንዳም ይኸው ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ የሚደረገው አደገኛ ጉዞ ጉዳይ ነው። ከጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል፤ ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንትና ከሌሎች መሪዎች ጋር አቢጃን ተገናኝተው የነበሩት የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ኃላፊ ዦን ክላውድ ዩንከር ቀደም ሲል ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ «ከወደ አፍሪቃ የሰሙት መረጃ» እጅግ እንደሰቀጠጣቸው ገልጠዋል። 

«የተሻለ ሕይወት ፍለጋ በሚፈልጉ የሰው ልጆች ላይ ሊቢያ ውስጥ የሚፈፀመውን እያሰብኩ ተመችቶኝ ላንቀላፋ አልችልም። እነዚህ ሰዎች ሊቢያ ውስጥ ገሀነምን ነው ያገኙት።»

ኃላፊው «ይኾናል ተብሎ ሊታመን የማይችል» ያሉትን ችግር አውሮጳ በዝምታ ሊያለፍ አይገባም ሲሉም አክለዋል። ጀርመን የሚገኘው የአፍሪቃውያን ማኅበረሰብ ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ ሞክታር ካማር ግን የኮሚሽነሩ ንግግር የሚዋጥላቸው አይመስልም።

«ዩንከር ከማንም በተሻለ ያንን ያውቃሉ። የአውሮጳ ኅብረትም ሊቢያ ውስጥ እየሆነ ስላለው ጠንቅቆ ያውቃል። እንዲያም ሆኖ ግን ከሊቢያ መንግሥት ጋር ስምምነት አድርጎ እዚያው ሊቢያ ውስጥ ስደተኞች ማቆያ ስልትን ዘረጋ። ይኼ ለኔ ወንጀል ነው። እዚያ ሥርዓት አልበኝነት እንደነገሰ፤ መንግሥት መላ ሀገሪቱን መቆጣጠር እንደማይችል፤ ስደተኞች ቁም ስቅልና ግድያ እንደሚፈፀምብቸው እየታወቀ ነው ያ የሆነው።»

ዦን ክላውድ ዩንከር በበኩላቸው «ሊቢያ ውስጥ ያለውን ችግር እናወቃለን» ብለዋል። «ሊቢያ ከሌሎች ሃገራት የተለየች አይደልችም፤ ስለዚህም የሆነው ነገር ሊታሰብም ተቀባይነት ሊኖረው የማይችል ነው» ሲሉም አክለውል።

«የአውሮጳ ኅብረት ከሊቢያ ጋር ያደረጋቸውን ስምምነቶች በሞላ እንዲያቋርጥ እናሳስባለን፤ ማንቸውንም የፋይናንስ ርዳታዎች በሞላ እንዲሁ። ከዚያ በኋላም ሊቢያ ሰብአዊ መብቶችን ለመጠበቅ በርግጥም ተገቢው ቦታ ላይ ስለመሆኗ መጣራት አለበት። በሰው ልጅ ላይ ባርነት የተባለ ወንጀል ከሚፈፀምባት ሀገር ጋር የአውሮጳ ኅብረት መሥራቱ ሊሆን የማይችል ነው። የሕግ የበላይነት ዳግም እስኪሰፍን ድረስ በጋር መሥራቱ መቋረጥ አለበት።»
በሊቢያ ሕፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ስደተኞች አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ባለፈው የጎርጎሪዮሱ ዓመት ሾልኮ የወጣ ሰንድ በገፍ ወደ አውሮጳ የሚደረገውን ፍልሰት ለመግታት በሚል የአውሮጳ ኅብረት አምባገነኖቹን ጨምሮ ለስምንት የአፍሪቃ ሃገራት 40 ሚሊዮን ዩሮ ግድም ለመክፈል መስናዳቱ እጅግ አስተዛዝቦ ነበር። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ