1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃውያን ወጣቶች የፖለቲካ ፍላጎት

ሐሙስ፣ መጋቢት 19 2005

በሰሜን አፍሪቃ የቀድሞዎቹን መንግሥታት ከሥልጣን ያስወገዱት በተለይ ወጣቶች ነበሩ። ከሰሀራ በስተደቡብ በሚገኙት አፍሪቃውያት ሀገራት ግን ምንም እንኳን እጅግ የከፋ ድህነት ቢኖርም እና በብሩሕ የወደፊት ዕድል እጦት ምክንያት በወጣቶች ዘንድ ተስፋ የመቁረጡ ሁኔታ እጅግ ቢስፋፋም፡ እስካሁን ትልቅ ተቃውሞ አልተካሄደም።

https://p.dw.com/p/186Ud
ምስል privat
Mkhuleko Hlengwa
ምስል DW

የሀያ አምስት ዓመቱ ሚክሁሌኮ ሂሎንግዋ ኬፕታውን በሚገኘው በደቡብ አፍሪቃ ምክር ቤት የኢንካታ ነፃነት ፓርቲ ተወካይ እንደራሴ ነው። በምክር ቤቱ ከተወከሉት አራት መቶ እንደራሴዎች መካከል በዕድሜ ትንሹ የሆነው ወጣት ሂንግዋ ወጣት ደቡብ አፍሪቃውያን የሀገራቸውን መንግሥት ተግባር በሚገባ በመከታተል፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በኃላፊነት መጠየቅ መቻል እንደሚገባቸው አመልክቶዋል። በወቅቱ ሂንግዋ በሀገሩ በሴቶች ላይ ለሚፈፀመው ወሲባዊ የኃይል ተግባር ትልቅ ትኩረት በመስጠት በዚህ አንፃር ርምጃ እንዲወሰድ ጥረት ጀምሮዋል።
ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በ 2012 ዓም ሴቶች ላይ 64,000 ጊዜ ወሲባዊ ጥቃት ተፈፅሞዋል በሚል ክሶች እንደቀረቡለት ቢያመለክትም፡ የመብት ተሟጋቾች ይኸው ቁጥር ከዚህ በጉልህ እንደሚበልጥ ነው ያስታወቁት። ትምህርትን ማስፋፋት እና ስራ አጥነትን መቀነስ የሚሉት ጉዳዮችም ለእንደራሴው ሂንግዋ ዋነኛ አጀንዳዎ ሲሆኑ፡ ከሰሀራ በስተደቡብ ባሉት አፍሪቃውያት ሀገራት የሚኖሩት ብዙዎቹ ወጣቶች ካለ ስራ ከቆዩ፡ በሰሜን አፍሪቃ የታየውን ዓይነት ዓመፅ መጀመራቸው እንደማይቀር ነው ሂንግዋ ያስጠነቀቀው።

« ጎረቤታችን ዚምባብዌ ለምሳሌ የሰብዓዊ መብት የተረገጠባት ሀገር ናት። ሀገሪቱ ክሽፈት ደርሶባታል። ደቡብ አፍሪቃም ተመሳሳይ አካሄድ ነው የምትከተለው፤ ምክንያቱም፡ ከብዙ ጊዜ ጀምራ ለወጣቶቹ ችግሮች እና አስተሳሰብ ትኩረት አልሰጠችምና። »
ወጣቱ እንደራሴ ሂንግዋ እንዳሳሰበው፡ መንግሥት የትምህርቱን፤ የጤና ጥበቃውን፡ እንዲሁም፡ የስፖርቱን ዘርፎችና የትርፍ ጊዚያት እንቅስቃሴዎችን ለማስፋፋት ርምጃ ሊወስድ ይገባዋል። የዩጋንዳው ተወላጅ ዩሱፍ ኪራንዳም ይህንኑ የሂንግዋን አስተሳሰብ ይጋራል።
በካምፓላ በሚገኘው እና ዴሞክራሲያዊ ሂደት ለማጠናከር በሚንቀሳቀሰው የጀርመናውያኑ ኮንራድ አድናወር ተቋም ውስጥ የሚሰራው ኪራንዳ ስራ አትነት በሀገሩ ትልቁ ችግር መሆኑን እና ወጣቶች ብሩሕ የወደፊት ዕድል እንደሌላቸው እና የዩጋንዳ መንግሥትም ይህን ሁኔታ ለመቀየር አንዳችም ርምጃ እንዳልወሰደ ገልጾዋል።
« ወጣቱ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በተስፋፋው ሙስና ተንገሽግሾዋል። ወጣቱ ራሱን እንዲችል ለተነደፉ መርሀግብሮች መዋል ያለበት ገንዘብ ሲጠፋ እና አላግባብ ሲውል ይታያል። ግን የሕዝብን ገንዘብ የሚሰርቁትን በኃላፊነት ለመጠየቅ፡ እና ገንዘቡን መልሶ ለማግኘት መንግሥት እስካሁን የወሰደው ይህ ነው የሚባል ርምጃ የለም። ስለሆነም ተስፋ መቁረጡ ከፍተኟ ነው። ስራ የለም፡ ሁኔታው ተበላሽቶዋል። ይህንንም ሁኔታ ለማሻሻል ምንም እየተሰራ አይደለም። »
ዩጋንዳዊው ኪሩንዳ እንዳስታወቀው፡ የአፍሪቃ ወጣቶች ስለወደፊቱ የአህጉሩ ዕጣ ፈንታ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ የሀገራቸው ጉዳይም ላይ አብረው መወሰን መፈለጋቸውን አንጋፋ ፖለቲከኞች ብዙም አይረዱላቸውም። አንጋፋ መሪ ከሚባሉት መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞው የጋና ርዕሰ ብሔር ጆን ኩፎር ይኸው የኪሩንዳ አባባል የተሳሳተ ነው ይላሉ። ለርሳቸው አፍሪቃ በሀገር አመራር ላይ የወጣቶችዋን ተፅዕኖ ከፍ በማድረጉ ጥሩ ጎዳና ላይ ናት።
« ወደጋና ምክር ቤት ብትመጣ፡ ከ 275 እንደራሴዎች መካከል ከ 50 ከመቶ የሚበልጡት ከ 40 እና ከ 45 ዓመት በታች ናቸው። ስለዚህ ወጣቶች ሥልጣን ለመያዝ እና ተፅዕኖ ለማሳረፍ ዕድሉ አላቸው። አፍሪቃ ፈጣን ለውጥ በማሳየት ላይ ነች። ራሷን ክፍት እያደረገች ነው። »

 

Yusuf Kiranda
ዩሱፍ ኪራንዳምስል DW

ቶማስ መሽ/አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ