1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ህብረት እና ድላሚኒ ዙማ

ቅዳሜ፣ ጥር 18 2005

ደቡብ አፍሪቃዊቱ ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበርነትን ሥልጣን ከተረከቡ ከአሥር ቀናት በፊት 100 ቀናት ሆናቸው። በዚሁ ሥልጣናቸው እሁድ በአዲስ አበባ የሚጀመረዉን የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመጀመሪያ ጊዜ ይመራሉ።

https://p.dw.com/p/17S6B
ምስል picture-alliance/dpa

የማሊ፡ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ፡ የጊኒ ቢሳው፡ የሱዳን እና የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ውዝግብ በእስካሁኑ የድላሚኒ የሥልጣን ዘመን ላይ ጥላ አጥሎበታል። የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪቃ የውጭ እና የሀገር አስተዳደር ሚንስትር ድላሚኒ ዙማ እአአ በ 2012 ዓም በተፎካካሪያቸው የቀድሞው የአፍሪቃ ህብረት ኮሚስዮን ፕሬዚደንት ዣን ፒንግን በጠባብ የድምፅ ብልጫ ቢያሸንፉም በህብረቱ ውስጥ ከፍተኛ አመለካከት አትርፈዋል።
የ 63 ዓመቷ ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ሰፊ ተሞክሮ እና ብቃት ያላቸው ፖለቲካኛ ሲሆኑ፡ በዲፕሎማሲ ክህሎታቸው በመጠቀም ለቀውሶች መፍትሔ ለማስገኘት ጥረት ያደርጋሉ። ይህንኑ ችሎታቸውንም በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ እና አሁን ደግሞ በማሊ ውዝግብ መፍትሔ በመሻቱ ጥረት ላይ አሳይተዋል ይላሉ የብሪታኒያው የጥናት ተቋም ቻተም ሀውስ የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮች አጥኚ አሌክስ ቫይንስ።
« የማሊን ውዝግብ በተመለከተ የአፍሪቃውያኑ የሰላም እና የፀጥታ መዋቅር እስከየት ድረስ ሊሄድ እንደሚችል መገንዘባቸው ሥልታዊ አርቆ አሳቢነታቸውን አሳይቶዋል። እንዲያውም፡ የአፍሪቃ ህብረትም ሆነ የተመድ የማሊን ውዝግብ ለማብቃቱ ተግባር አስፈላጊው የጦር ትጥቅ እንደሌላቸው ልዩ መልዕክተኞች በካይሮ ግልፅ ያደረጉበትን ሁኔታ ድላሚኒ ዙማ እና ተደራዳሪዎቻቸው በሚገባ ተረድተውታል። በዚህም የተነሳ ድላሚኒ ዙማ ሰሜናዊ ማሊን የተቆጣጠሩት ፅንፈኞቹ ሙሥሊሞች ወደ መዲናይቱ ባማኮ ለመገሥገሥ መወሰናቸው በታወቀ ጊዜ ፈረንሣይ በአንፃራቸው የጀመረችውን ዘመቻደግፈዋል። »
የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክን በተመለከተ የአፍሪቃ ህብረት በኃይል ተግባር ሥልጣን ለያዘ መንግሥት ዕውቅና እንደማይሰጥ ግልፅ አድርጓል። ከዚህ አልፎም ድላሚኒ ዙማ ደቡብ አፍሪቃ ወደዚችው ሀገር ጦር እንድትልክ ማግባባት መቻላቸው ይጠቀሳል።  
ያም ቢሆን ግን፡ ይላሉ የአፍሪቃ አጥኚ ፕሮፌሰር ኡልፍ ኤንግል የድላሚኒ ዙማ አመራር በመሠረቱ የኮሚሽኑን አሰራር አልለወጠም።
« በመጀመሪያ ደረጃ ከርሳቸው በፊት የነበሩት ዣን ፒንግ የተተከተሉት አሰራር ከሞላ ጎደል አሁንም እንደቀጠለ ነው። ለዚህም የአፍሪቃ ህብረት መዋቅር ተጠያቂ ነው። ብዙው ከርሳቸው የመወሰን መብት ውጭ ነው። ህብረቱ በአንድ የተወሰነ ሕግ መሠረት ነው የሚሰራው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፡ የአፍሪቃ ህብረት ተቋማዊ አሰራር በጣም እየተጠናከረ በመሄዱ ህብረቱ ይጠቀምባቸው የነበሩ አንዳንዶቹ ሥልቶች ተሽረዋል። ከዚህ በተረፈ ግን ድላሚኒ ዙማ ለየት ያለ አቀራረብ አስተዋውቀዋል። »
ኤንግል አክለው እንዳስረዱት፡ ድላሚኒ ዙማ የኃይል ርምጃ እና የውዝግቦች ሰለባ ለሆኑ ሴቶች እና ሕፃናት ልዩ ትኩረት ሰጥተዋል።
እርግጥ፡ የፖለቲካ ተንታኝ ድላሚኒ ዙማ እስካሁን ያከናወኑትን ስራ ቢያሞግሡም፡ በተለይ ለሰላም እና የፀጥታ ጉዳዮች ጠንካራ ትኩረት የሰጡበት አሰራራቸው የውዝግቦችን መንሥዔ የመታገሉ ተግባር ችላ እንዲባል አድርጎታል በሚል ህብረቱን የሚመለከቱ የሰላም እና የፀጥታ ጉዳዮች አማካሪ መሐሪ ማሩ አስጠንቅቀዋል።
እንዲያም ቢሆን ግን፡ የድላሚኒ ዙማ የመጀመሪያዊቹ ሦስት ወራት ተኩል የሥልጣን ጊዜ ምንም እንኳን ለዚሁ ሥልጣን የተመረጡበት ድርጊት አዳጋች ቢሆንም፡ የተሳካ እንደነበር አሌክስ ቫይንስ አስታውቀዋል።
« በተለምዶው አሰራር  የአፍሪቃ ህብረት ሊቀ መንበርነት ሥልጣን ደቡብ አፍሪቃ፡ ናይጀሪያ፡ አልጀሪያ፡ ግብፅን ከመሳሰሉ ትላልቆቹ መንግሥታት ለመጣ ግለሰብ ስለማይሰጥ በዙማ ምርጫ ወቅት አንዳንዶች ቁትብነትን አሳይተው ነበር። ይህ አሰራር በዙማ ምርጫ አክትሞዋል። እና አሁን ህብረቱን በባለሙያነት የመምራት ችሎታ እንዳላቸው እና የደቡብ አፍሪቃን አጀንዳ እንደማይከተሉ፡ እንዲሁም፡ ይህንኑ ችሎታቸውንም የአፍሪቃ ህብረትን ለመጥቀም እና አህጉሩ የሚገጥሙትን ፈተና ለመወጣቱ ተግባር እንደሚያውሉት እያሳዩ ነው ያለው። »
በአህጉሩ በወቅቱ ለሚታዩት ቀውሶች መፍትሔ ከማፈላለጉ ጎን ድላሚኒ ዙማ በእንግሊዝኛ እና በፈረንሣይኛ ቋንቋ ተናጋሪ አፍሪቃውያት ሀገራት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት መያዛቸውን በፕሪቶርያ የሚገኘው የደቡብ አፍሪቃውያን ዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ኃላፊ ጃኪ ሲልየ አመልክተዋል።
« ድላሚኒ ዙማን ያጋጠማቸው ትልቁ ተግዳሮት አንድ ዓመት ሙሉ በነዚህ ሁለት ቡድኖች ገላጋይ ሀሳብ ላይ አለመድረስ የተነሳ እክል ገጥሞት የነበረውን ድርጅት መምራቱ ነበር። ልዩነቱ የተፈጠረው አንዳንዶች እንደሚሉት ፈረንሣይኛ ተናጋሪ ሀገሮች ዙማ እንዳይመረጡ በምርጫው ዘመቻ ወቅት ተቃውሞ ባሰሙበት ጊዜ ነበር። ባጠቃላይ ግን እስካሁን ያሳዩት አአራር ጥሩ ነው። በጣም ችሎታ ያላቸው ግለሰብ ናቸው። »
እንግዲህ ይህን ልዩነት ማጥበብ መቻል አለመቻላቸው በአሁኑ የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ይታያል።

ሳራ ሽቴፈን/አርያም ተክሌ
መሥፍን መኮንን

Afrikanische Union Gebäude in Addis Abeba
ምስል DW /Maya Dreyer
Gipfel Afrikanische Union Addis Abeba
ምስል dapd
Nkosazana Dlamini-Zuma
ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማምስል picture-alliance/dpa