1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ልማት ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በሻንግሃይ

ረቡዕ፣ ግንቦት 8 1999

የአፍሪቃ ልማት ባንክ ሁለት ቀናት የሚፈጅ ዓመታዊ የቦርድ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት ሻንግሃይ ላይ ከፍቷል። ሻንግሃይ የስብሰባው ቦታ ሆና መመረጧ የቻይናና የአፍሪቃ ትብብር መጠናከር ውጤት መሆኑ ነው።

https://p.dw.com/p/E0cv
ምስል AP

ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂያባዎ የቻይና ፍላጎት የአፍሪቃን የተፈጥሮ ሃብት መበዝበዝ ነው ሲሉ ምዕራባውያን መንግሥታት የሚሰነዝሩትን ትችት እንደገና አስተባብለዋል። የባንኩም ተጠሪዎች አፍሪቃውያን ከእሢያና በተለይም ከቻይና የዕድገት ልምድ ብዙ ትምሕርት ሊቀስሙ እንደሚችሉ ነው የተናገሩት። የአፍሪቃ ልማት ባንክ በብድር አቅርቦት በመዋዕለ-ነዋይና በቴክኒካዊ ዕርዳታ አማካይነት ለክፍለ-ዓለሚቱ ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ከ 43 ዓመታት በፊት፤ በ 1964 ይቋቋማል።
በጅምሩ የባንኩን ውል 23 የአፍሪቃ ማዕካላዊ የገንዘብ ተቋማት አስተዳዳሪዎች ሲፈርሙ ባንኩ 65 ከመቶ በሚሆን የአፍሪቃ መንግሥታት ካፒታል ላይ ተመሥርቶ ነበር ሥራውን የጀመረው። የአፍሪቃ ልማት ባንክ ዛሬ 53 የአካባቢና 24 ከአካባቢው ውጭ የሆኑ ዓባል ሃገራት አሉት። ባንኩ በአስተዳዳሪዎች ቦርድ የሚመራ ሲሆን ለአምሥት ዓመታት የሚያገለግለውን ፕሬዚደንት የሚመርጠውም ይሄው አካል ነው። ከሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የቀድሞው የሩዋንዳ የገንዘብ ሚኒስትር ዶናልድ ካቤሩካ የባንኩ ፕሬዚደንት ሆነው ይገኛሉ።

የአፍሪቃ ልማት ባንክ ከተቋቋመ ጀምሮ አይቮሪ ኮስትን ለረጅም ጊዜያት የተግባር ማዕከሉ ሲያደርግ ምዕራብ አፍሪቃይቱን አገር ለሁለት በከፈለው የእርስበርስ ጦርነት የተነሣ መቀመጫውን በ 2003 ዓ.ም. ወደ ቱኒዝ ይቀይራል። ለነገሩ አይቮሪ ኮስት አሁን ባንኩ ወደ አቢጃን እንዲመለስ ትፈልጋለች። ይሁንና ፍላጎቷ መሟላቱን ለመናገር በወቅቱ ጥቂት አዳጋች ነው። ለማንኛውም ባንኩ ከተቆረቆረ አንስቶ እስካለፈው 2005 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ 55,2 ቢሊዮን ዶላር የፈጁ ከ 3,100 የሚበልጡ ፕሮዤዎችን ሲያራምድ ቆይቷል።
የአፍሪቃው የገንዘብ ተቋም 33 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ሲኖረው ባለፈው ዓመት የሰጠው ብድር 3,4 ቢሊዮን ገደማ ይጠጋ ነበር። አሕጉራዊው የፊናንስ ተቋም ብድር መስጠት ከጀመረ ከ 1967 ዓ.ም. ወዲህ የሰሜናዊው አፍሪቃ አገሮች 17 ቢሊዮን ዶላር አግኝተዋል። ይህም ከባንኩ ጠቅላላ ካፒታል ሲሦ ገደማ መሆኑ ነው። ቀደምቱ ተጠቃሚዎችም ሞሮኮና ቱኒዚያ ሆነው ይገኛሉ። ምዕራባዊው አፍሪቃ በናይጄሪያ ቀደምትነት ሩቡን ድርሻ ሲይዝ በሌሎች አካባቢዎች በዋነኝነት የባንኩን ብድር የሚያገኙት ኢትዮጵያን፤ ሞዛምቢክንና ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎን የመሳሰሉት ሃገራት ናችው።
የአፍሪቃ ልማት ባንክ ባለፈው ወር ደግሞ በአፍሪቃ ውስጥ ለሚካሄዱ ታላላቅ መዋቅራዊ ፕሮዤዎች፤ እነዚህም የኤነርጂን፣ የመንገድ ሥራንና ውሃን ይጠቀልላሉ የገንዘብ ምንጭ ለመፍጠር ከመዋዕለ-ነዋይ አቅራቢዎች ጋር ትብብር አስፍኗል።
Pan-African Infrastructure Development Fund የተሰኘው የውስጥና የግል የካፒታል ስብስብ በቀጥታ በመዋቅራዊ ፕሮዤዎች፤ በዚሁና በተያያዙ ዘርፎች ንብረት ባላቸውና በሚቆጣጠሩ ኩባንያዎች ዋስትናም ላይ ያተኩራል። ባንኩ ለዚሁ ተግባር 50 ሚሊዮን ዶላር ድርሻውን እንደሚወጣና ለአስተዳደር ተግባሩም ተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ዶላር እንደሚያቀርብ ነው የሚናገረው።

የአፍሪቃ የልማት ባንክ ከሁለት ሣምንት በፊት ለማዳጋስካር የኒኬል ማዕድን ፕሮዤ 150 ሚሊዮን ዶላር ሲያቀርብ በኡጋንዳም ሊታነጽ ለታሰበ የሃይል ማመንጫ ጣቢያ 110 ሚሊዮን ለመስጠት ወስኗል። የኡጋንዳው ፕሮዤ የአገሪቱን የኤነርጂ እጥረት ለመቋቋም የተወጠነ 250 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ሊያመነጭ የሚችል ነው።

ዛሬ ሻንግሃይ ላይ ወደተከፈተው ዓመታዊ የቦርድ ስብሰባ እንመለስና በጉባዔው ላይ ዓበይት የንግግር ርዕስ ሆነው የተመረጡት በዓለም ኤኮኖሚ ላይ የእሢያና በተለይም የቻይና ሚና፤ እንዲሁም የአፍሪቃና የቻይና የልማት ሽርክና ናቸው። 53 የአፍሪቃ ሃገራትን የጠቀለለውን የልማት ባንክ የሚመሩት ዶናልድ ካቤሩካ በሻንግሃዩ ስብሰባ ከእሢያ ከዕርዳታ ጥገኝነትና ከፊናንስ ቀውስ የማገገም ልምድ አሕጉራቸው ብዙ መማር እንደምትችል ተናግረዋል። የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ዛሬ በአማካይ 5,5 ከመቶ ዓመታቲ ዕድገት ማድረጉ ቢነገርም ገና በሁለት እግሩ ለመቆም የቻለ አይደለም። ሁኔታውን ለመለወጥ ገና ብዙ ጥረት ይጠይቃል።

ካቤሩካ የቻይናን መንግሥት ከአፍሪቃ ጋር ለሚያደርገው ትብብር አወድሰዋል። በሌላ በኩል ምዕራቡ ዓለም፤ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት ቻይና የነዳጅ ዘይትና ሌሎች ጥሬ ሃብቶች ለመበበዝበዝ እንጂ በአፍሪቃ ሰብዓዊ መብት ለመከበሩም ሆነ በጎ አስተዳደር ለመስፈኑ ደንታ የላትም ሲሉ ይወቅሳሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂያባዎ ግን በሻንግሃዩ ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት የቻይና ዓላማ ጨርሶ ይህ አይደለም። አገራቸው ዕድገትን ለማራመድ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ስረዛ ማድረጓን ሲያስገነዝቡ በአፍሪቃ የሚገኙ የቻይና ኩባንያዎች መንገድ ዝርጊያንና ጤና ጥበቃን በመሳሰሉ ዘርፎች ለሕዝብ የሚጠቅሙ ፕሮዤዎችን እንዲያራምዱ ጥሪ ሰንዝረዋል።

የአፍሪቃ ልማት ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ሻንግሃይ ላይ መካሄዱ ለሁለቱ ወገን ትብብር ታላቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው በጀኔቫ የዓለምአቀፍ ጥናት ኢንስቲቲቱት መምሕር የሆኑት የፕሮፌሰር ላንሢን-ሢያንግም ዕምነት ነው። “እንደማስበው የአፍሪቃ ልማት ባንክ ከአፍሪቃ ውጭ ሲሰበሰብ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። መጀመሪያ በስፓኝ ነበር፤ አሁን ደግሞ በሻንግሃይ! ይህ ስብሰባ ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም የአፍሪቃ መንግሥታት በቻይና የልማት ዘይቤ ላይ ማተኮራቸውና ከቻይና ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለጋራ የኤኮኖሚ ጥቅም ማጠናከር መፈለጋቸው ነው”

የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ኮሚሢዮን ሥራ አስፈጻሚ አካል ጸሐፊ አብዱሊዬ ጃኔህም እንደተናገሩት የባንኩ ዓመታዊ ጉባዔ በሻንግሃይ መካሄዱ ለአፍሪቃና ለእሢያ ግንኙነት ጥንካሬ ምሥክር ነው። የስብሰባውን አጀንዳም ለጊዜው ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው ብለውታል። እርግጥ ምዕራቡ ዓለም ግን ጉዳዩን እንዲህ አይመለከትም።

ለማንኛውም ፕሮፌሰር ላንሢን-ሢያንግ ከአውሮፓም ሆነ ከአሜሪካ በአፍሪቃና በቻይና ትብብር ላይ የሚሰነዘረው አስተያየት ወይም ትችት አይጥማቸውም። የቅኝ ገዢዎች አስተሳሰብ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። “አውሮፓውያን አፍሪቃ ጓሮዋችን ናት ብለው ነው የሚያስቡት። ማለት የቀድሞ ቅኝ ገዢ ሃይላት ናቸው። ታዲያ ቻይና ወደዚህ ጓሯቸው በመዝለቋ መጨነቃቸው አልቀረም። እና ከዚህ የተነሣ ትችት መሰንዘራቸው ብዙም አያስደንቅም። ግን ትችቱ ክብደት የሚሰጠው አይደለም። አንዳንዴ እንዲያውም የቻይናን ዓላማ ኔኦ-ኮሎኒያሊዝም፤ የዕጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ይሉታል። ይህ ትክክለኛ ሊሆን አይችልም”

የጄኔቫው ዓለምአቀፍ ኢንስቲቲዩት ባልደረባ በአንጻሩ ቻይና በአፍሪቃ የያዘችው ትብብር ቀና ለመሆኑ አይጠራጠሩም። ላንሢን-ሢያንግ በጎ አስተዳደር በአፍሪቃ እንዳይሰፍን ቤይጂንግ መሰናክል ሆናለች የሚለውን አባባልም አይቀበሉትም። “ቻይና በጎ አስተዳደር እንዳይሰፍን ታደርጋለች ብዬ አላምንም። በሌሎች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት ለረጅም ጊዜ ጸንቶ የቆየ የቻይና ፖሊሲ ነው። ግን ቤይጂንግ የአፍሪቃን የኤኮኖሚ ዕድገት ከልብ ትፈልገዋለች። ለዚህም ነው ሰፊ የዕዳ ስረዛ ያደረገችው። በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የልማት ዕርዳታም ትሰጣለች። አሜሪካ ግን በአፍሪቃ አንድም ነገር አላደረገችም። ቻይና ቢቀር የተወሰነ ሥራ ሠርታለች”

በእርግጥም ቻይና በአፍሪቃ የራሷን የጥሬ ሃብት ጥም ለመወጣት ስትል በያዘችው የጠበቀ ትብብር የቀድሞዉ ቅኝ ገዢዎች በዘመናት ያልሰሩትን ተግባር ነው ያከናወነችው። በአፍሪቃ በመዋቅራዊው ግንባታ፤ በመንገድ ይሁን በድልድዮችና ሃዲዶች ማነጽ፤ ሌሎች ሌሎች ተግባራትም የቻይና ሥራ ዛሬ ጎልቶ የማይታይበት ቦታ አይገኝም። ምዕራቡ ዓለም በቻይና ላይ የሚሰነዝረው ወቀሣ እንግዲህ ለአፍሪቃ ልማት ወይም የሰብዓዊ መብት ከበሬታ ከመቆርቆር ይልቅ የተነጠቅሁ ቁጭት ነው የሚመስለው። ለአፍሪቃውያን የልማት ባንኩ ፕሬዚደንት ዶናልድ ካቤሩካ በትክክል እንዳሉት ከተመጽዋችነትና ከጥገኝነት ለመላቀቅ የእሢያ ልምድ እጅግ ጠቃሚ ነው። የተገኘውን ትምሕርት በሥራ ላይ ለማዋል መጣር ይኖርበታል።

ሆኖም ይህ ፍሬ ሊሰጥ የሚችለው ደግሞ የአፍሪቃ መንግሥታት ከቻይና ጋር ያላቸውን ትስስር በሚገባ ሊጠቀሙበት ሲበቁ ነው። ከጥገኝነት የሚያላቅቃቸውን ዕውቀትንና የቴክኖሎጂ ጥበብን ለመውረስ፣ በቅንጦት ሕንጻዎች ፈንታ ለልማት የሚበጁ መዋቅራዊ ግንባታዎችን ለማራመድ፣ የግሉን የንግድ ዘርፍ ለማስፋፋትና መሃከለኛ የሕብረተሰብ ክፍልን ለማሳደግ ቁርጠኛ ሆኖ መነሣት ይጠበቅባቸዋል። እነርሱ ያልጠየቁትን ቻይና ልትሰጣችው አትችልም። ይህ ግንዛቤ ዛሬ በብዙዎቹ የአፍሪቃ አገሮች ገና በሚገባ የሰረጸ አይደለም። የሚፈለገውን የዕድገት ፈለግ ተከትለው ጭብጥ ዕርምጃ ሲወስዱ የሚታዩት መንግሥታት በእጣት የሚቆጠሩ ናቸው።

የማዳጋስካር ፕሬዚደንት ማርክ ራቫሎማናና በአግባብ እንደተናገሩት አፍሪቃ ላይ ተደቅኖ የሚገኘው ታላቁ ፈተና የአመራር እጦት ነው። በመሠረቱ ዛሬ በቂ ቁሣቁሳዊ፣ የገንዘብና የቴክኖሎጂ ብቃት በሰፈነባት ዓለም ድህነት የትናንት እንጂ የዛሬ ታሪክ መሆን አልነበረበትም። ግን ሃቁ አፍሪቃ በአብዛኛው ከተመጽዋችነትና ከአምባገነንነት፤ ይሄው ከፈጠረው በሙስና ከጨቀየ አገዛዝ አለመላቀቋ ነው። ይህ የአፍሪቃ ልማት ባንክ በሁለት ቀናት ስብሰባው የሚለውጠው ነገርም አይሆንም። ዓመታዊው ስብሰባ ነገ ሲጠናቀቅ ግን ቢቀር ስለመጪው ዕቅዱ ጥቂት መስማታችን የማይቀር ነው።