1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ

ዓርብ፣ ሰኔ 29 2004

ከጀቡቲ በስተቀር እንግሊዝኛ ተናጋሪ የሚባሉት የምሥራቅ አፍሪቃ ሐገራት ምናልባት ሠልፋቸዉን ከምዕራቦቹ ሳያደርጉ አይቀርም። ግጭትን በተመለከተ ጉባኤዉ ከዚሕ ቀደም የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉ ይወስናል ተብሎ ነዉ የሚጠበቀዉ

https://p.dw.com/p/15Sva
18ኛዉ ጉባኤምስል picture-alliance/dpa


አስራ-ዘጠኛዉ የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች መደበኛ ጉባኤ በመጪዉ ሳምንት አዲስ አበባ ዉስጥ ይደረጋል።ሊሉንግዌ-ማላዊ ሊደረግ የነበረዉ ጉባኤ ወደ አዲስ አበባ የዞረዉ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እንዲታሰሩ የበየነባቸዉ የሰሜን ሱዳኑ ፕሬዝዳት ዑመር ሐሰን አል-በሽር በጉባኤዉ እንዳይገኙ ማላዊ በማገዷ ነዉ።ጉባኤዉ ከመሰብሰቢያ ሥፍራ በስተቀር በሚወያይባቸዉ ርዕሶች ላይ ያደረገዉ ለዉጥ የለም።የማሊ፥ የሱዳኖች፥ የሶማሊያና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንግ ግጭትና ዉዝግብ የጉባኤተኞችን ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮች ናቸዉ።ከሁሉም በላይ ግን የሕብረቱን ኮሚሽን ፕሬዝዳት መምረጡ ታዛቢዎች እንደሚሉት ብዙ ሳያከራክር አይቀርም።

መሪዎቹ ለዋና የመነጋገሪያ ርዕሥነት የመረጡት የአፍሪቃን-የንግድ ትሥሥር ማጠናከር የሚል ነዉ።እንዲያዉ ከፖለቲካ ዉዝግቡ፥ ከጦርነት፥ ግጭት ትርምሱ፥ ፋታ፥ ከተለመደና ካለዉ እዉነት ገለል-ቀለል ለማለት፥ አለያም እንደ ሌላዉ ዓለም ወግ፥ ከሌላዉ ለመመሳሰል ወይም ለማስመሰል፥ ካልሆነ በቀር አፍሪቃን ከተጣባት የእልቂት ፍጅት፥ የስደት-መከራ ዑደት እንደማያማልጡ እነሱም አፍሪቃን የሚያዉቀዉም አላጡትም።

ማሊ እየተተራመሰች፥ ሱዳኖች ሁለት ተሰንጥቀዉም እየተፋጁ፥ ሶማሌዎች እየተላለቁ፥ ከዩጋንዳ እስከ ብሩንዲ፥ ከኢትዮጵያ እስከ ኬንያ ፥ ጅቡቲ በሶማሌዎች እልቂት መሐል እየዳከሩ የሌጎስ ነዳጅ ባማኮ፥ የኬንያ ሻይ ቅጠል መቃዲሾ፥ የኢትዮጵያ አትክልት ጁባ፥ የሱዳን ጥጥ፥ ካምፓላ ሥለሚሸጥ-ሥለሚለወጥበት ደንብ መሪዎቹ አፍ-ከልብ ሆነዉ ይነጋገራሉ ብሎ ማሰብ ሲበዛ ከባድ ነዉ።

እንዲያዉም ርዕሠ-መንበሩን ፕሪቶሪያ ያደረገዉ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም (ISS-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) እንደሚለዉ የጉባኤዉ ትልቅ ርዕሥ መሪዎቹ እንዳሉት ንግድ አይደለም።ብዙዎች እንደሚጠብቁት ከባማኮ-እስከ ሞቃዲሾ የሚደርሰዉ ቀዉስም አይደለም።የሕብረቱን ኮሚሽን ፕሬዝዳት መምረጥ እንጂ።

ባለፈዉ ጥር በሥልጣን ላይ ካሉት ከዦን ፒንግና ፒንግን ለመተካት ካመለከቱት ከደቡብ አፍሪቃዊቷ ፖለቲከኛ ከንኮሳዛና ድላሚኒ-ዙማ መሐል አንዱን ለመምረጥ ለሁለት ተገምሰዉ በይደር ነበር የተዉት።የመሪዎቹን አለመስማማት አንዳዶች የእንግሊዝኛና የፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሐገራት ልዩነት ይሉታል።የአይ፣ኤስ፣ ኤሱ አጥኚ ዶክተር ጅዴ ማርትየንስ ኦኬኬ ግን ይሕን መላምት አሳሳች ይሉታል።

«ልዩነትን የአንግሎ ፎንና የፍራንኮፎን ተናጋሪ ሐገራት ልዩነት አድርጎ መናገር አሳሳች ነዉ።ዦን ፒንግን ከሚደግፉት ሐገራት የተወሰኑት ፈረንሳይኛ ተናጋሪ አይደሉም።ለምሳሌ የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ (ኤኮዋስ) አባል መንግሥታት ዦን ፒንግ ይቀጥሉ በሚለዉ ሐሳብ ይስማማሉ።ይሕ ናጄሪያን የመሳሰሉ የአካባቢዉ ጠንካራ መንግሥታትን ያካትታል።»

ናይጀሪያ ደግሞ እንግሊዘኛ ተናጋሪ ሐገር ናት።ልዩነቱ ባለፈዉ ጥር፥-አሁንም መኖሩን ኦኬኬ አሳምሮ ይሉታል።ምክንያቱ ግን ጥቅም-እንጂ ቋንቋ አይደለም።

«በየአካባቢዉ ባሉ ጠንካራ መንግሥታት መካከል ያለ ግጭት ነዉ።የጥቅም ግጭት።

ሰሜን አፍሪቃዎች ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ካስገደሉ በኋላ አድፍጠዉ ማየቱን የመረጡ መስለዋል። ምሥራቆች ግን በደቡብ አፍሪቃና በናጄሪያ-መሪነት ደቡብ እና ምዕራቦች ከሚሻኮቱበት መድረክ ዋና ተዋኝ ናቸዉ።ምክንያትም አላቸዉ።ያዉ ግን ጥቅም።

«በሳዴክ አባላትና በምሥራቅ አፍሪቃ መንግሥታት መካካልም ዉጥረት አለ።መገንዘብ ያለብን አሁን ባለዉ አሠራር መሠረት ማዳም ዙማ የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ከሆኑ የምክትል ሊቀመንበርነቱን ሥልጣን የያዙት የምሥራቅ አፍሪቃዊቱ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሐገር የኬንያ ዲፕሎማት ሥልጣናቸዉን እንደያዙ አይቀጥሉም።»

ከጀቡቲ በስተቀር እንግሊዝኛ ተናጋሪ የሚባሉት የምሥራቅ አፍሪቃ ሐገራት ዉክልናቸዉን ላለማጣት ምናልባት ሠልፋቸዉን ከምዕራቦቹ ሳያደርጉ አይቀርም ነዉ-ግምቱ።ግጭትን በተመለከተ ጉባኤዉ ከዚሕ ቀደም የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉ ይወስናል ተብሎ ነዉ የሚጠበቀዉ።የማሊን ጉዳይ ግን ኦኤኬ አጓጊ ይሉታል።

«የማሊን የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክን የሶማሊያና የሌሎችም ግጭት ያለባቸዉን አካባቢዎች ችግር ለማስወገድ በሒደት ላይ ያለ ጥረት አለ።በአፍሪቃ ሕብረት፥ አንዳድ አካባቢ ደግሞ በኤኮዋስ የሚመሩ ጣልቃ ገብነት እርምጃዎችም አሉ።አጓጊ የሚሆነዉ ግን የሕብረቱ የሠላምና የፀጥታ ኮሚሽን የማሊን ቀዉስ ለማስወገድ ኤኮዋስ ከሚወስደዉ እርምጃ የተለየ እርምጃ እንዲወሰድ ከወሰነ ነዉ።»

የማሊን ቀዉስ ለማስወገድ ኤኮዋስ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ብሔራዊ የአንድነት መንገሥት መመሠረት አለበት የሚል አቋም ነበረዉ።የቲምቡክቱ ታሪካዊ ቅርሶች መፍረሳቸዉ ከተሰማ ወዲሕ ግን ጣልቃ ገብ ጦር ለማዝመት መዘጋጀቱን አስታዉቋል።

Nkosazana Dlamini Zuma
ድላሚኒ-ዙማምስል picture-alliance/ dpa
Gipfel Afrikanische Union Addis Abeba
ፒንግምስል Reuters

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ