1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ሣምንት በጀርመን

ረቡዕ፣ ግንቦት 15 2004

በዚህ በጀርመን በፍራንክፉርት ከተማ ካለፈው ሰኞ አንስቶ እስከፊታችን አርብ የሚዘልቅ «የአፍሪቃ የቢዝነስ ሣምንት» የሚል ስያሜ የተሰጠው የመድረክ ስብሰባ እየተካሄደ ነው።

https://p.dw.com/p/150EY

በዚህ በጀርመን በፍራንክፉርት ከተማ ካለፈው ሰኞ አንስቶ እስከፊታችን አርብ የሚዘልቅ «የአፍሪቃ የቢዝነስ ሣምንት» የሚል ስያሜ የተሰጠው የመድረክ ስብሰባ እየተካሄደ ነው። በዚሁ መድረክ ላይ የአፍሪቃና የአውሮፓ የኤኮኖሚ ዘርፍ ተጠሪዎችና ባለሙያዎች ተሰብስበው ሲወያዩ ይሰነብታሉ።

አፍሪቃ ዛሬ በተለይም በተፈጥሮ ሃብቷ የተነሣ ከመቼውም በላይ የዓለም ማተኮሪያ ሆና ነው የምትገኘው። ክፍለ-ዓለሚቱ ባለፈው አሠርተ-ዓመት በተፋጠነና ጠንከር ባለ ሁኔታ የኤኮኖሚ ዕድገት እያደረገች መምጣቷም በየጊዜው ይነገራል። ይህ ሁሉ ደግሞ አውሮፓውያን ኩባንያዎች የወደፊቷ ጠቃሚ ገበያ መባል በጀመረችው ክፍለ-ዓለም መዋዕለ-ነዋይ እንዲያደርጉ ለማደፋፈር መንስዔ መሆኑ አልቀረም።

በዓለምአቀፍ ደረጃ ተሰሚነት ያለው የጀርመን የኩባንያዎች አማካሪ ድርጅት ሮናልድ በርገር በቅርቡ ባወጣው አዲስ የጥናት ወጤቱ እንደሚለው የአፍሪቃ የኤኮኖሚ አቅም ዛሬ ቻይናና ሕንድ ከሃያ ዓመታት በፊት ከነበሩበት የሚመሳሰል ነው። ከዚሁ ባሻገር ትልቅ የፍጆት ገበያን የሚከፍት መካከለኛ የሕብረተሰብ መደብ እያደገ መሆኑና ለዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ልዩ ዕድል እንደከፈተም ነው ከጥናቱ አጠናቃሪዎች አንዱ ክሪስቲያን ቬሰልስ የሚናገሩት።

«የአፍሪቃ ሃቅ ዛሬ ምዕራቡ ዓለም በከፊልም ቢሆን እስካሁን ካለው ግንዛቤ ብዙ ርቆ የተራመደ ሆኖ ይገኛል። ይህም የሆነው አፍሪቃ የራሷን ዕጣ በራሷ ዕጅ በማስገባት በተለያዩ ዘርፎች አስደናቂ ዕርምጃ በማድረጓ ነው። የጥሬ ሃብቱ ዘርፍ ወደፊት የዕድገቱ አንድ ክፍል ብቻ እንደሚሆን በግልጽ ይታያል። እርግጥ ጥሬው ሃብት ታላቅ ሚና ኖሮት ነው የሚቀጥለው። ግን ትርጉሙን በተለይም ክፍጆት ምርቱ ኢንዱስትሪ፣ ከፊናንሱ ዘርፍ፣ ከመኖሪያ ቤቶች ግንባታና ከመዋቅራዊ ፕሮዤዎች ዕድገት ጋር በንጽጽር ማየት ያስፈልጋል»

በሌላ በኩል ዛሬ ብዙ በአድናቆት የሚወራለት የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ዕድገት በብዙ ተመራማሪዎች ዘንድ ሲበዛ አጠያያቂ ነው። ከነዚሁ መካከል አንዱ በሰሜናዊው ጀርመን የሃምቡርግ የአፍሪቃ ልማት ምርምር ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ሮበርት ካፐል የክፍለዓለሚቱን ወቅታዊና የወደፊት ሁኔታ አጋኖ ግምት ከመስጠት መቆጠብ እንዲኖር ነው የሚያሳስቡት። ተመራማሪው የሮናልድ በርገርን ጥናት ውጤት የሚመለከቱት የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶችን ወደ አፍሪቃ ለመሳብ የተወጠነ አድርገው ነው።

Arnulf Christa und Jaiye Doherty auf der Africa Business Week Frankfurt
ምስል DW

አፍሪቃ በዓለም ገበያ ላይ የረባ ድርሻና በኢንዱስትሪ ረገድም አንዳች ሚና እንደሌላት ነው የሚያመለክቱት። ለግንዛቤ ያህል በዓለምአቀፍ ደረጃ የአፍሪቃ የውጭ ንግድ ድርሻ በ 0,5 ከመቶ ብቻ የተወሰነ ነው። ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር የምታደርገውን የውጭ ንግድም እንደ ምሳሌ ብንወስድ የአፍሪቃ ድርሻ እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ሁለት በመቶ የተወሰነ ነው። ለዚያውም የጀርመን ኩባንያዎች ከሣሃራ በስተደቡብ መዋዕለ-ነዋይ የሚያደርጉትም ከሞላ ጎደል በደቡብ አፍሪቃ ብቻ ሆኖ ይገኛል።

የአፍሪቃ ኤኮኖሚ እንግዲህ በተጨባጭ ሲታይ ዛሬም በኢንዱስትሪና በእርሻ ልማት ዘርፍ የሚደረግ ጠንካራ ዕርምጃ ይጎለዋል። ባለፉት ዓመታት ተገኘ የሚባለው ከፍተኛ ዕድገት አሁንም እንደቀድሞው በጥሬ ሃብት ላይ የተመሠረተ ነው። አፍሪቃ የራሷን ፍጆታ ለመሸፈን እንኳ አምራች ኢንዱስትሪ ለማነጽ አልቻለችም። ይህን የዓለም ባንክ ጥናትም ያረጋግጣል። እርግጥ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ዕድገት እየታየበት መሆኑ አንዱ ሃቅ ነው።

ነገር ግን የሚያሳዝን ሆኖ ሕብረተሰቡ የዕድገቱ ተጠቃሚ ወይም ተካፋይ ሊሆን አልቻለም። ሃቁ እንዲያውም ድህነት በክፍለ-ዓለሚቱ እየጨመረ መሄዱ ነው። ዛሬ ሚሊያርድ ገደማ ከሚጠጋው ከአንዲት ዶላር ባነሰች የዕለት ገቢ ኑሮውን የሚገፋው አብዛኛው የዓለም ሕዝብ በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም እንደሚገኝ ይታወቃል። ከዚህ አንጻር በአፍሪቃ መዋዕለ-ነዋይ ማድረግ የሚፈልግ በተመሳሳይ ጊዜ የልማት ዕርዳታ መስጠቱም አይቀርለትም።

በፍራንክረርቱ ሣምንት የጀርመን ኩባንያዎች በአፍሪቃ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? ምን ዕድልስ አላቸው? እነዚህ ጥያቄዎችና የዕውቀት ሽግግር ጉዳይ በሰፊው ውይይት የተያዘባቸው ነጥቦች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ የበለጸጉት መንግሥታት የጥሬ ሃብት ፍላጎት እጅጉን እያደገ ሲሄድ የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት በሚጨምርባት በአፍሪቃም ለምሳሌ የኤነርጂ ዕጥረት ብርቱ ችግር በመሆን ላይ ነው። ይሄም እርግጥ መዋዕለ-ነዋይንና ለመዋቅራዊ ግንባታ የውጭ ኩባንያዎችን ተሳትፎም ይበልጥ አስፈላጊ የሚያደርግ ነገር ሆኖ ይገኛል።

የጀርመን ኤኮኖሚ ዘርፍ ጥራትና ብቃት እንዲሁም አስተማማኝነት መለያው ሲሆን ከዚህ ደግሞ የአፍሪቃ ሃገራት በጣሙን ሊጠቀሙ ይችላሉ። ስለዚህም የጀርመን ኩባንያዎች ተፈላጊነት በአፍሪቃ በዚህ በበርሊን የሩዋንዳ አምባሳደር ክሪስቲን እንኩልኪንካ እንደሚናገሩት እጅግ ከፍተኛ ነው። እርግጥ እስካሁን በሰፊው ወደ ክፍለ-ዓለሚቱ አይሻገሩ እንጂ!

«ከጀርመኖች የምንፈልገው እስካሁን ካለው የበለጠ ነው። የጀርመን የኤኮኖሚ ዘርፍ አፍሪቃ ውስጥ ገና በሰፊው ተሰማርቷል ብዬ አላስብም። ስለዚህም ጠንካራ ተሳትፎውን ማየት ነው የምንሻው»

Portrait Alt-Bundespräsident Horst Köhler
ምስል AP

የጀርመን ኩባንያዎች እስካሁን ወደ አፍሪቃ በመሻገሩ ረገድ ቁጥብነት ማሳየታቸው በተለይም በብዙዎቹ በአፍሪቃ መንግሥታት የጎደፈ ዝና የተነሣ ነው። መንግሥትና የአስተዳደር ተቋማቱ በሙስና የተዘፈቁ መሆናቸውና ሕጋዊ ዋስትና አለመኖሩ ሲታሰብ ለመሆኑማንስ ነው በዚህ ሁኔታ ለመነገድ የሚፈልገው? እርግጥ የቀድሞው የጀርመን ፕሬዚደንት ሆርስት ኮህለር እንደሚሉት የአፍሪቃን ክፍለ-ዓለም በጥቅሉ እንዲህ መመልከት የሚቻልበት ጊዜም አልፏል።

«አፍሪቃውያን ዛሬ ሁኔታቸውን መለወጡ የራሳቸው ጉዳይ መሆኑን ተገንዝበዋል። በፖለቲካ ረገድ የዴሞክራሲው ሂደት መረጋጋት እየታየበት ሲሆን የመንግሥት አመራሩም ሁኔታ እየተሻሻለ ነው። እርግጥ ሙስና እንደ ካንሰር ሆኖ ባለበት ቀጥሏል። ሆኖም ግን ሙስና ለአፍሪቃና ለሕዝቧ ጎጂ የመሆኑ ንቃተ-ህሊና በክፍለ-ዓለሚቱም እያደገ ነው። በሁለተኛ ደረጃም የአፍሪቃዊው ዜጋ ንቃት እየጨመረ ነው የመጣው። ሌሎቹ ማለትም ሃብታሞቹ መንግሥታት አፍሪቃን እንደሚፈልጉ ዛሬ ጠንቅቆ ያውቃል»

ምክንያቱም አፍሪቃ ያላት ጸጋ ሌላው በግድ የሚያስፈልገው መሆኑ ነው። ቻይና ይህን ገና ቀደም ሲል ተገንዝባ በክፍለ-ዓለሚቱ በገፍ መዋዕለ-ነዋይ በማድረግ ላይ ትገናለች። በሌላ በኩል እርግጥ በአፍሪቃውያን ዘንድም ለቀሪው ዓለም የተፈጥሮ ጸጋ በማስረከብ እንደተወሰኑ መቀጠሉ እንደማይጠቅም ግንዛቤው እየጨመረ መሄዱ አልቀረም።

«ጥሬ ሃብትን ወደ ምርት መለወጡ፤ ማለት አንድን ያለቀ ምርት አፍሪቃ ውስጥ በራስ ሰርቶ ማውጣቱ ነው ዋጋ ያለው ነገር። እንዚህ ሃገራት ደግሞ ይህ ያስፈልጋቸዋል። ለወጣቱ ትውልድ የሥራ መስኮችን መክፈት መቻል አለባቸው። ለዚህ እያደገ ለሚሄደው ራስን የመቻል ሂደት ደግሞ የጀርመን የማቀናበር ብቃት፣ የኢንጂነር ጥበብ፣ የመንግድ ሥራና ሌላም ብዙ ነገር ጥሩ ዝና ነው ያለው። እናም ትልቅ ዕድል ይኖረዋል»

የጀርመን መዋዕለ-ነዋይ ለሁለቱም ወገን ጠቃሚ እንደሆነ ነው ሆርስት ኮህለር የሚናገሩት። የቀድሞው የጀርመን ፕሬዚደንት በቅርቡ አንድ የጀርመንና የአፍሪቃ ኩባንያዎች የሚገናኙበት ስብሰባን አዘጋጅተው ነበር። በዚህ ደረጃ በሚደረግ ንግግር ጥሩ የንግድ ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚቻል ነው የሚምኑት። በንግግሩ ላይ የጀርመን ኩባንያዎች ቅድመ-ግዴታዎች በሙሉ እንዲሟሉ እንደሚፈልጉና በዚሁ የተነሣም ቁጥብ እንደሆኑ ነው ከአፍሪቃውያኑ በኩል የተነገረው። በዚህ ደግሞ ብዙ ዕድል ሳያመልጣቸው አልቀረም።

Deutschland Entwicklingsminister Dirk Niebel bei Deutsche Welle in Bonn
ምስል DW

በስንጠረዦች ላይ ካተኮሩ አፍሪቃ በረጅም ጊዜ ከሌሎች የዓለም አካባቢዎች ይበልጥ የኤኮኖሚ ዕድገት ዕድል ያለባት አካባቢ ናት። በዓመት በሰባት ከመቶ እንደምታድግ የሚገመት ሲሆን እርግጥ ጀርመን የዚህ ሂደት ተጠቃሚ ለመሆን የአገሪቱ ፌደራላዊ የኤኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዲርክ ኒብል እንደሚሉት አፍሪቃን በእኩልነት መቀበል መቻል አለባት።

«አፍሪቃ ወጣትና ከዓለም በጥሩ ሁኔታ የተሳሰረ ለፍጆታ ዝግጁ የሆነ ሕዝብ ያላትገበያ እየሆነች ነው። አፍሪቃ ቀውስ አይጣት እንጂ የቀውስ ክፍለ-ዓለም ብቻም አይደለችም። በሸሪክነት ከተቀበልናት ብዙ ዕድል ያለባት ክፍለ-ዓለም ናት። አፍሪቃ ዛሬ ከኢንዱስትሪው ዓለም የልማት ዕርዳታ የሚወረወርላት አካባቢ አይደለችም። የለም፤ ሸሪካችን ናት»

የሆነው ሆኖ የጀርመን ኩባንያዎች ከሣሃራ በስተደቡብ አፍሪቃ በአብዛኛው መዋዕለ-ነዋይ ሲያደርጉ የቆዩት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ነው። ዛሬ በደቡብ አፍሪቃ 600 ገደማ የሚጠጉ የጀርመን ኩባንያዎች ሰፍረው ይገኛሉ። እንዚህም ከ 90 ሺህ የሚበልጡ ሠራተኞችን ቀጥረው የሚያስተዳድሩ ሲሆን ከሞላ-ጎደል ሁሉም የጀርመን ታላላቅና መካከለኛ ኩባንያዎች በኬፕታውን ውክልና አላቸው። የጀርመን ኩባንያዎች ሕልውና ደቡብ አፍሪቃ ከውጭ ሣይሆን ክውስጥ ማደግ እንድትችል ጠቃሚ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።

ለዚህም በኩባንያዎች ውስጥ የሚሰጥ የሙያ ሥልጠናና የቴክኖሎጂ ሽግግር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ አልቀረም። ይሄው ከውጭ የሚደረግ የኤኮኖሚ ድጋፍና የልማት ትብብር መተሳሰር ደግሞ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሚኒስትር ዲርክ ኒብል እንደሚናገሩት ከጀርመን መንግሥት የአፍሪቃ ፖሊሲ ጋር የሚጣጣም ነው። በሚኒስትሩ አባባል አፍሪቃውያን ዛሬ የሚፈልጉትንና የማይፈልጉትን ራሳቸው ከሚወስኑበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ከሆነ ይህ ጥቅምን ለማስከበር የሚበጅ ነገር ነው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ