1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ-ቅርምት ጉባኤ 125ኛ አመት

ሰኞ፣ ኅዳር 14 2002

«ብዙ ጊዜ በታሪክ ለሚፈፀሙ በደሎች የገንዘብ ካሳ ይከፈላል።ለዚሕስ (ግፍ) ካሳ የማይከፈልበት ምን ምክንያት አለ። ባሁኑ ጊዜ በየሥፍራዉ የገንዘብ እጥረት መኖሩ ይገባኛል---

https://p.dw.com/p/Kdih
ቢስማርክ-የጉባኤዉ መሐንዲስ

23 11 09

ጀርመኖች የዳግም ዉሕደታቸዉን ቅድመ ብሥራት፣ ድፍን አለም የኮሚንዝምን ጅምር-ዉድቀትን ሃኛ አመት በርሊን ላይ ባከበረ በሳምንቱ፣የተባበሩት መነግስታት ድርጅት የችግር-ችጋር ጥናት ከሞት ለሚያታግለዉ አፍሪቃዊ የለጋሾን እርጥባን የጠየቀበት ጉባኤ ሮም ላይ የተሰየመ ዕለት፣በርሊን እየመከሩ፣በርሊን-እየተለያዩ ከበርሊን በሚነሳ እሳት በተደጋጋሚ እየተለላለቁት፣አዉሮጶች-የእልቂት ፍጅት-ምክንያትነት የነበረዉን ልዩነታቸዉን-የአብሮነታቸዉ ጌጥ፣የአንድነታቸዉ ፅናት መሆኑን አንድ መሪ በመምረጥ ዳግም ሊያስመሰክሩ-አራት ቀን ሲቀራቸዉ ፣ ብዙ ጊዜ የአለም ሒደት የተዘወረባት ያቺ ታሪካዊ ከተማ-አፍሪቃን ያቀራመተዉን ጉባኤ ያስተናገደችበት አንድ መቶ ሃያ-አምስተኛ አመት ተዘከረባት።በርሊን።ዝክሩ መነሻ፣ጉባኤ ዉጤቱ ማጣቃሻ የዛሬ አስተጋብቶ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።


አፄ-ምኒሊክ የመሩት ኢትዮጵያዊ ሐገር ነፃነቱን ለማስከበር የከፈለዉ መስዋዕትነት፥ በኢጣሊያ ቅኝ ገዢዎች ላይ የተቀዳጃዉ ድል ለኢትዮጵያዊዉ ክብር፣አኩሪ ታሪክነቱ፥ ለድፍን ጥቁር ሕዝብ የነፃነት-እኩልነቱ አብነት-አለኝታነቱ በርግጥ የዘመን ሒደት ሊሽረዉ አይችልም።

ከክዋሚ ንኩሩማ እስከ ጆሞ ኬንያታ፣ ከሴዳር ሴንጎር እስከ ጁሊየስ ኔሬሬ፣ ከሮበርት ሙጋቤ እስከ ኔልሰን ማንዴላ የመሩት አፍሪቃዊ በቅኝ ገዢ፣ ዘረኛ ገዢዎቹ ላይ ያመፀበት-ዘመን፣ የታገለበት ሥልት፣ የከፈለዉ መስዋእትነት የመለያየቱን ያክል-የየትግሉ ቆስቋሽ አብነት-የአድዋ ድል፥ ትግሉ ፀረ-ቅኝ አገዛዝ- አላማ-ግቡ ነፃነት-እኩልነት መሆኑ አያነጋግርም።

ቀዳማዊ ንጉስ ኡምቤርቶን ለቅኝ ገዢነት ያጃገነዉ፣ ንጉስ ቪክቶር ኢማኑኤል ሳልሳዊን ከነጀኔራሎቻቸዉ አድዋ ላይ በሟሸሸ የቅኝ ግዢነት እብሪት ያናወዛቸዉ ደግሞ በ1884 (ዘመኑ በመሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) በርሊን ላይ የተጀመረዉ ጉባኤ ዉጤት ነበር።የጉባኤዉ-እኩይ-ምክንያት-ዉጤት የሚታሰበዉ በጉባኤዉ መዘዝ ሕይወት፥ክብር ነፃነት ሐብቱን ያጣዉን አፍሪቃዊ በሚወክሉት አዲስ አበባ፥ናይሮቢ፥ አክራ ዳሬ-ሰላም ወይም ሌላ ከመሆን ይልቅ በርሊን መሆኑ ነዉ-የዛሬዉ ዚቅ።

ከሕዳር አስራ-አምስት 1884 እስከ እስከ የካቲት አጋማሽ 1985 የዘለቀዉ ጉባኤ ከተሰየመበት አዳራሽ አጠገብ-አንዲት የመታሰቢያ ሰሌዳ ቆማለች።በርሊን።ሰሌዳዉን ያቆመዉ የቶጎዉ ተወላጅ-ቪክቶር ድሲድሶኑ የያኔዉን ታሪክ አፍሪቃዉን የመዘንጋት የለባቸዉም-ባይ ነዉ።

«ሠሌዳዉ ለኔ በጣም አስፈላጊ ነዉ።ምክንያቱም የአፍሪቃን ታሪክ በሙሉ ሥለተከታተልኩት፥ ዛሬ እዚያ ያለዉን ችግር ያኔ ከተፈፀመዉ ጋር ማገናኘት ሥለምሻ ነዉ።ይሕ ሰሌዳ በቅኝ አገዛዝ ዘመን የተፈፀመዉ በደል እንዳይረሳ ማስታወሻ እንዲሆን እፈልጋለሁ።ለዚሕም ነዉ ያኔ አፍሪቃ በተቀራመቱባት ሥፍራ መቆም አለበት ብዬ ያሰብኩት።»

የፖርቱጋል፥ የቱርክና የስጳኝ ቅኝ ገዢዎች ክንድ እየዛለ፥ የብሪታንያና የፈረንሳይ እየፈረጠመ በነበረበት በአስራ-ዘጠነኛዉ መቶ-ክፍለ ዘነመን ነባሮቹ-ባዳዲሶቹ ብዙ እንዳይበለጡ ዘግይት ብለዉ ከጎለበቱት እንደ ጀርመንና ኢጣሊያ ከመሳሰሉት ጋር ማበሩን እንደ ጥሩ ብልሐት ነበር ያዩት።

ኢጣሊያ ከኦስትሪያ-ሐንጋሪ እና ከጀርመን ጋር -የጦር ቃል ኪዳን ስትፈራረም፥ የቤልጂጉ ንጉስ ሊዮፖልድ ሉዊስ ፊሊፕ ቪክቶር ዳግማዊ የዛሬዋን ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክን በ1878 እንደ የግል-ርሰተ ጉልታቸዉ መግዛት መጀመራቸዉ ብዙዎቹን ቅር አሰኝቶ ነበር።በተለይ ፈረንሳይ የሊዮፖልድን እርምጃ ደግፋለች መባሉ በጣሙን የፖርቱጋልና የብሪታንያን ቁጣ ቀስቅሶ ነበር።

ፖርቱጋሎች-ጉዳዩን ለማገድ ከጀርመኖች ጋር መተባበሩን ሲመርጡ፥ጀርመናዊዉ የታሪክ አዋቂ ዮአኺም ሴለር እንደሚሉት «ብረቱ» የሚል ቅፅል ለታከለላቸዉ ለጀርመኑ መራሔ መንግሥት ለኦቶ ፎን ቢስማርክ-ሾንሐዉሰርና ለወዳጆቻዉ ጥሩ አጋጣሚ ነበር።

«ኮንጎ በሊዮፖልድ ዳግማዊ እጅ መዉደቋና በዚያ በኩል የሚደረገዉ የሸቀጥ ዝዉዉር መታገዱ ለቢስማርክና ለሌሎቹ አሳሳቢ ነበር።የብዙዎቹ እምነት መርከቦች በኮንጎ ወንዝ በመነፃ መዘዋወር አለባቸዉ፥ሌሎች ሐያል መንግሥታትም ወደ ኮንጎ የመግባት መብታቸዉ መጠበቅ አለበት የሚል ነበር።»

የኮንጎ ድልብ ሐብት ሰበብ፥ የቅኝ ገዢዎቹ ልዩነት፥ የአዳዲሶቹ ሐይላት ጥያቄ፥ የእርስበራሳቸዉ መፈራራት-ምክንያት ከሁሉም በላይ አፍሪቃን የመቀራመቱ ፍላጎት መሠረት ሆኖ-ቢስማርክ ያን ጉባኤ ጠሩ።ሰወስት ወር በቆየዉ ጉባኤ አስራ-ሁለት የአዉሮጳ ሐገራት፥ቱርክና ዩናይትድ ስቴትስ ተካፋዮች ነበሩ።

ሐያሉ የአፍሪቃን ካርታ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጠዉ አፍሪቃን ሲቀራመቱ-ሴለር እንደሚሉት አንድም አፍሪቃዊ አልተወከለም ነበር።

«በግልፅ መታወቅ ያለበት አንድም አፍሪቃዊ (በዚያ ጉባኤ) እንዲገኝ አልተጋበዘም ነበር።»

ያኔ አይደለም ዛሬም የዚያን ዘመኑን ታሪክ የሚያስብ አፍሪቃዊ መሪ የለም-ካለም አይታወቅም።እንደ ጀርመንና ኢጣሊያ ያሉት ባነሱት ጥያቄ ብዙም ካልተደሰቱት አንዷ ብሪታንያ ከአፄ ዩሐንስ ጋር የሔዉሌት ስምምነት የተባለዉ ዉል አድዋ ላይ ተፈራርማ ነበር።ዉሉ ኢትዮጵያ የምፅዋን የመሳሰሉ ወደቦች ሪታንያ እዉቅና የሰጠችበት ነዉ።

Kolonialismus Afrika Kongo Konferenz Berlin
ጉባኤዉምስል picture alliance/dpa

በርሊን ላይ ከነኢጣሊያና ጋር እተደራደረች-አድዋ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር የተዋዋለችዉ ብሪታንያ-የበርሊኑ ጉባኤ ባበቃ በወራት እድሜ ኢጣሊያ ምፅዋን ስትቆጣጠር-ለደካማዋ ኢትዮጵያ ወይም ለፈረመችዉ ዉል ፅናት አልተከራከረችም።በርግጥም ጥቅም፥ የሐይል ሚዛንን-አሰላለፍ እልፍ ሲልም የዘር-ወገን ቅርበት በሚዘዉረዉ የፖለቲካ ጨዋታ-ሐቅ-እዉነት፥ ሞራል-ሥነ ምግባር ቦታ አልነበረዉም።

የበርሊኑ ጉባኤ ልዩነት ድብልቅልቁ ወጥቶ አንደኛና ሁለተኛ በሚባሉት ጦርነቶች አለም እስክትነድ ድረስ የድፍን-አፍሪቃ ሕዝብ በቅኝ ገዢዎች ሐይላት ተጨፍጭፏል።ተረግጧል፥ ተገድሏል።ተዋርዷል-ለዛሬ ለተረፈ-የድንበር፥ የርስ በርስ ግጭትም ተዳርጓል።ከሕዳር አስራ-አምስት ጀምሮ በርሊን ዉስጥ በሚካሔደዉ ስብሰባ፥ ዉይይት ላይ ከሚካአሉት አፍሪቃዉያን አንዱ ስቬን ሜካሪደስ እንደሚለዉ በቅኝ አገዛዝ ዘመን በአፍሪቃዉያን ላይ ለተፈፀመዉ በደል-ካሳ የማይከፈልበት ምክንያት አይገባዉም።

«ብዙ ጊዜ በታሪክ ለሚፈፀሙ በደሎች የገንዘብ ካሳ ይከፈላል።ለዚሕስ (ግፍ) ካሳ የማይከፈልበት ምን ምክንያት አለ። ባሁኑ ጊዜ በየሥፍራዉ የገንዘብ እጥረት መኖሩ ይገባኛል።ይሁንና እዉነተኛ የምጣኔ ሐብት ትብብር ወይም ደግሞ የትምሕርት ማድረግ የሚገድ አይመስለኝም።የያኔዎቹ ቅኝ ገዢዎች ለአፍሪቃዉያንን ለማስተማርና ለማሰልጠን ወጪ የሚሆን የሆነ የገንዘብ ተቋም መመሥረት ይላሉ።»

ይችላሉ ግን-ለምን ያደርጉታል።ማንስ ጠይቋቸዉ።

አዉሮጶች የጠብ-ጦርነት ምክንያትን አስወግደዉ ዛሬ-አንድም ብዙም ሆነዉ አለምን መምራታቸዉ ብዙ አይገርምም።እስከ 1990ዎቹ ድረስ ሥለ-ድሕነት፥ በሽታ ረሐብ ሲነሳ አፍሪቃ፥ እስያ ደቡብ አሜሪካ እንደቅደም እኩል ተጠቃሾች ነበሩ።ዛሬ ግን ደቡብ-አሜሪካ-እስያዎች በረሐብ፥በሽታ ጦርነት የሚያልቅ ሕዝባቸዉን ቁጥር ቀንሰዉ ፖለቲካዊ መብት እኩልነታቸዉን እያስከበሩ ነዉ።የሰሜን-ኮሪያ የኑክሌር ዉዝግብ በድርድ ይፈታ ቢባል-ከስድስቱ ተደራዳሪዎቹ-አራቱ እስያዎች ናቸዉ።የሁንዱራስ ፖለቲከኞች ቢወዛገቡ-ሽምጋዮች ግንባር ቀደም ሸምጋዮች-እነ ብራዚል ናቸዉ።አፍሪቃ-ግን በነበረችበት ናት።
----------------------------------------------------
-----------------------------------------------------

በየአመቱ በሃያ-በሰላሳ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ የሚራብባት አፍሪቃ-የምግብ ምፅዋት ከመለመን አልፎ-ላለፈ በደል፥ ካሳ-የሚሟገት፥ ለዛሬ መብት-እኩልነት፥ለደፊት ብልፅግና የሚታትር-መሪ አላት ማለት በርግጥ ያሳስታል።የዚምባቡዌ፥ የኬንያ፥ የጊኒ፥ ሌላዉ ቀርቶ ነፃነትዋን አስከብራ በመኖርዋ የምትኮራዉ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ደም-አፋሳሽ ዉዝግብ ንትርካቸዉን መፍታት-አቅቷቸዉ የለንደን፥ ዋሽንግተን፥ ብራስልስን ዉሳኔ እየጠበቁ አፍሪቃ በባሪያ ፈንጋይ-ቅኝ ገዢዎች ተበድላለች-የሚሉበት ልቡና ከየት-ያመጣሉ-ነዉ ጥያቄዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ዶቬ ነጋሽ መሐመድ