1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ መሪውን መረጠ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 10 2010

ጥልቅ መከፋፈል ገጥሞታል የሚባልለት የደቡብ አፍሪቃው የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ ድላሚኒ ዙማን ጥሎ ሲሪል ራማፎሳን መሪው አድርጎ መርጧል። የመሰንጠቅ አደጋ ተጋርጦበታል የሚባልለት ኤ.ኤንሲ ጃኮብ ዙማ እየመሩት አገሪቱን በአግባቡ መምራት ተስኖታል፣ ሙስና እና የዘር መድሎን ችላ ብሏል እየተባለ ይወቀሳል።

https://p.dw.com/p/2pesv
Südafrika Cyril Ramaphosa, neuer Präsident ANC
ምስል Reuters/S. Sibeko

ራማፎሳ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል

የምርጫ ሒደቱን ያስተናበሩት ወ/ሮ "ሦስት የተበላሹ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች እና አራት የድምፅ ተዓቅቦዎች አሉ። ጓዲት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ 2,261  ድምፆች ጓድ ራማፎሳ ደግሞ 2,446 ድምፆች አግኝተዋል። በዚህም መሠረት ጓድ ሲሪል ራማፎሳን የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ አዲስ ፕሬዝዳንት አድርገን አፅድቀናል።" ሲሉ ተደመጡ። ደስታ እና ጭፈራ ተከተለ። ኩነቱን በዝምታ የሚከታተሉም አልጠፉም። 
የደቡብ አፍሪቃው ገዢ ፓርቲ የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ አባላት እና ደጋፊዎች እንዲህ እየጨፈሩ አዲስ መሪ መረጡ። የደቡብ አፍሪቃው ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ያሸነፉት የአለቃቸው የፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ የቀድሞ ባለቤት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማን ነው። 

የ65 ዓመቱ ጎልማሳ የሠራተኞች ማኅበር መሪ እና ከናጠጡ የደቡብ አፍሪቃ ባለሐብቶች መካከል አንዱ ናቸው። የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ መሪ በመሆናቸው በሙስና ቅሌት የሚታሙትን እና መንግሥታቸው የአገሪቱን የኤኮኖሚ እድገት አቀዛቅዟል እየተባሉ የሚተቹትን ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማን ይተካሉ። በቀረቡባቸው ለቁጥር የሚያታክቱ የሙስና ክሶች ምናልባት ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ይችላሉ የሚባልላቸው ዙማ የፓርቲ መሪነታቸውን ቢያስረክቡም እስከ መጪው ምርጫ ግን በሥልጣን ይቆያሉ።
ላለፉት ሦስት ዓመታት የዙማ ምክትል ሆነው ያገለገሉት ራማፎሳ ታዲያ ዙማን መሞገት ተስኗቸዋል እየተባሉ የሚወቀሱ ፖለቲከኛ ናቸው። ላለፉት 23 ዓመታት ደቡብ አፍሪቃን የመራው ፓርቲ በሕዝባዊ ድጋፍ እጦት ምክንያት ከሁለት ዓመታት በኋላ በሚደረገው ምርጫ ሁነኛ ፈተና ይጠብቀዋል። ራማፎሳ ሊመሩት በትረ-ሥልጣኑን የተቀበሉት ፓርቲም ቢሆን በቀድሞ ግርማ ሞገሱ አይገኝም።  ደቡብ አፍሪቃዊው ተባባሪ ፕሮፌሰር  ምቅፃቢሲ ንዳላጫና ጭርሱን የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ የፖለቲካ ፍልስፍና ስለመስራቱ እርግጠኛ አይደሉም።  

Südafrika ANC Parteitag Nkosazana Dlamini-Zuma
ምስል picture-alliance/Zumapress/D. Naicker

"የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ ካለፈው ታሪኩ ፋታ ያሻዋል። ባለፉት አስር ዓመታት 15 በመቶ ድጋፋቸውን አጥተዋል። በጎርጎሮሳዊው 2004 ዓ.ም. 69 በመቶ የነበረ ሲሆን ባለፈው ዓመት ግን ወደ 54 በመቶ ዝቅ ብሏል። ይህ ደግሞ የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ ፖለቲካ እየሠራ አለመሆኑን ይጠቁማል።"
የቀድሞ ባለቤታቸው ድጋፍ የነበራቸው ድላሚኒ ዙማ ቢመረጡ በአገሪቱ የሰፈነውን የዘር ጥላቻ ሊታገሉ ቃል-ገብተው ምረጡኝ ሲሉ ሰንብተዋል። ሙስናን መታገል እና በአንድ ወቅት ከፈጣኖቹ ጎራ ተመድቦ የነበረውን የደቡብ አፍሪቃ ኤኮኖሚ ማነቃቃት ደግሞ የሲሪል ራማፎሳ ቃል ኪዳኖች ናቸው። በአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ 54ኛ ጉባኤ የታደሙ 4,700 በላይ የፓርቲው ልዑካንም ቢሆኑ ስለ ፓርቲያቸው ያላቸው ተስፋ ተቃራኒ ነው። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ተሳታፊ  "ሲሪል ራማፎሳ በማሸነፋቸው ደስታ ተሰምቶኛል። አገሪቱን ወደ ሚቀጥለው ደረጃ ከፍ ያደርጓታል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ለውጥ ይኖራል። በደቡብ አፍሪቃ ለውጥ እናያለን።" ሲሉ ተስፋቸውን ተናግረዋል። በሌላ ወገን በዚያው አዳራሽ ውስጥ "ማን አሸነፈ ማን ተሸነፈ የሚለው ጉዳይ ለውጥ አያመጣም። ዙማ በስልጣን ከቆዩ ሁሉም ነገር ያው ነው። አብዛኞቹ በሙስና የተጨማለቁ በመሆናቸው የሚቀየር ነገር አይኖርም።" የሚሉም ነበሩበት። 

Südafrika Jacob Zuma Winnie Madikizela-Mandela Cyril Ramaphosa ANC
ምስል picture alliance/AP Photo/T. Hadebe

አዲሱ መሪ በርከት ያሉ ፈተናዎች ከፊታቸው ተደቅነዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ ጃኮብ ዙማ ለቀረቡባቸው የሙስና ክሶች ፍርድ ቤት የመቆማቸው ነገር ይሆናል። ይኸን ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ የቀድሞ ታጋዮች፣ የሲቪክ ማኅበረሰቡን ጨምሮ መላ ደቡብ አፍሪቃውያን በዓይነ-ቁራኛ ይከታተሉታል። 

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ