1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ኅብረት በአፍሪቃውያን ዕይታ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 17 2005

የአፍሪቃ ኅብረት ከዛሬ፤ ቅዳሜ ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓም አንስቶ እያከበረ የሚገኘውን የወርቅ ኢዮቤሊዩ በዓል በማስመልከት የተለያዩ የዶቸ ቬለ ሬዲዮ ጋዜጠኞች በተለያዩ የአፍሪቃ አገራት ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ግለሰቦችን አነጋግረዋል። «የአፍሪቃ ኅብረት ለእርስዎ ምን ትርጉም አለው?» አብይ ጥያቄያችን ነበር።

https://p.dw.com/p/18dx7
ምስል picture-alliance/dpa
Gründung der OAU 1963
ምስል picture-alliance/dpa
Afrikanische Union feiert 50. Jubiläum
ምስል picture-alliance/dpa

በመጀመሪያ የ33 ዓመቱ ደቡብ አፍሪቃዊ ግንበኛ፤ ኑሮው ጆሐንስበርግ ከተማ ውስጥ ነው። ዋሽንግተን ሮበርት ቺዋላ ይባላል። በግሉ የሚያስተዳድረው ድርጅት አለው። የአፍሪቃ ኅብረት አድናቂ እንደሆነ በመጥቀስ ድርጅቱ በየጊዜው የሚያሳየውን ለውጥ በእዚህ መልኩ ይገልፃል።

 «የአፍሪቃ ኅብረትን አደንቀዋለሁ። ድርጅቱ የቅኝ ግዛት ጭቆናን በሚገባ ተፋልሟል። ዘረኛ የአፓርታይድ ስርዓትንም ከደቡብ አፍሪቃ ገርስሷል። በአፓርታይድ ዘመን ስራ ማግኘት እንዲህ ቀላል አልነበረም። አንዳንድ መርገጥ የማትችላቸው መንገዶችም ነበሩ። የግል ቤትና መኪናማ ጭራሽ የማይታሰቡ ነበሩ። አሁን ሁሉም ነገር አለኝ። ልጆቼ ወዳፈቀዳቸው ትምህርት ቤት መሄድ ይችላሉ። የእራሴን ድርጅት አቋቁሜ ነጭ ሠራተኞችን ሳይቀር መቅጠር ችያለሁ።»

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጎማ የሠመመን መርፌ ወጊ ባለሙያ የሆነችው የ28 ዓመቷ ኤስተር ዛዋዲ ፓንጋ ኅብረቱ ለእሷ አንዳች ትርጉም  የማይሰጠው ለምን እንደሆነ እንዲህ ትገልፃለች።
 
 «የአፍሪቃ ኅብረት የጃጀ ድርጅት ነው። ለእኛ ለአፍሪቃውያን ምንም ፋይዳ የለውም። እንደ ማሊ ያሉ አገራትን ብቻ መመልከት በቂ ነው። እዚያ ከአፍሪቃ ኅብረት ይልቅ ፈረንሳይ ናት ጣልቃ የገባችው። እና እዚህ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ  ከአስር ዓመት በላይ በጦርነት ውስጥ ነው ያለነው። ወደ እዚህ ጦር መላክ የነበረበት የአፍሪቃ ኅብረት እንጂ የተባበሩት መንግስታት አልነበረም።  የአፍሪቃ ኅብረት እንደ አዲስ እንዲዋቀር እሻለሁ። ምክንያቱም  ድርጅቱ  የአፍሪቃውያንን ችግር ለመቅረፍ ምንም የረባ ነገር አያደርግም።»

አማዱ ሞሣ ኮሊባሊ እዛው ማሊ ባማኮ ከተማ ውስጥ  የሚገኘ አንድ የወጣቶች ድርጅት ሊቀመንበር ነው። የአፍሪቃ ኅብረት ወጣቶችን ችላ ብሎ ጭራሽ ዘንግቷቸዋል ባይ ነው።

«እኔ እራሴ ከአፍሪቃ ኅብረት እጠብቅ የነበረው  አንዳችም የተሟላ ነገር የለም። የአፍሪቃ ኅብረት ኅብረትነቱን ለማጠንከር አዲስ ገጽታን ሊላበስ ይገባል።  ለእዚያ ደግሞ ወጣቶች ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። በሁሉም የአፍሪቃ ክፍል ያሉ ወጣቶች ችግር ተመሳሳይ ነው። እርስ በእርስ  ልምድ ቢለዋወጡ ከእራሳቸው ተርፈው ለኅብረቱ እንኳ መፍትሄ ሊያበጁ በቻሉ  ነበር።»


አምባሳደር መንግስቴ ደስታ የአፍሪቃ ኅብረትን የተመለከተ አንድ መፅሐፍ በቅርቡ ለንባብ አብቅተዋል። ኅብረቱ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ይባል በነበረበት ወቅትም ሆነ አሁን በኅብረቱ ጥላ ስር የተሰጠውን ግብ በእርግጥም እያሳካ ነው ይላሉ።  አምባሳደሩ ነዋሪነታቸው የኅብረቱ መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ውስጥ ነው።  

«የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ቀዳማይ ግቡ መላ አፍሪቃን ከቅኝ አገዛዝና ዘረኛ የአፓርታይድ ጨቋኝ ስርዓት ማላቀቅ ነበር። ኅብረቱ ልክ እንደተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ሁሉ ሠላምና ደኅንነትን ለማስፈን የሚሰራ ምክር ቤት አቋቁሞዋል። እናም ይህ ድርጅት አፍሪቃ ውስጥ ሠላምና ደኅንነት ላይ የተጋረጡ መሰናክሎችን እየተጋፈጠ ይገኛል። እናም ከእዚህ አንፃር እንኳን እስካሁን በርካታ ተግባራትን ፈጽሟል።»

ሌላኛው ኢትዮጵያዊ የአፍሪቃ ኅብረት መስራች አባቶች ከሚባሉት አንዱ ዓፄ ኃይለሥላሴ ትኩረት ባላገኙበት የሚከበረው በዓል ትርጉም አይሰጠኝም ይላሉ።

የ58 ዓመቷ ናይጄሪያዊት ነዋሪነታቸው በናይጀሪያ ማዕከላይ ባውቺ ውስጥ ነው። ሀጂያ አያቱ የተባሉት እኚህ የቤት እመቤት የአፍሪቃ ኅብረትን በተመለከተ የተቀላቀለ ስሜት ነው ያላቸው። 


 «የአፍሪቃ ኅብረት አንዳችም ስኬታማ ተግባር አልፈፀመም ለማለት አይቻልም። በእርግጥ የመንቀሳቀስ ችግር አለ፤ ማለትም ቪዛ ለማግኘት አዳጋች ነው። ሌላኛው ችግር አፍሪቃ በእምቅ ሀብት የታደለች አህጉር ሆና ሳለ እኛ ከእዚያ ተጠቃሚ ለመሆን ያለመቻላችን ሁናቴ ነው።»

በምዕራብ አፍሪቃዊቱ ኒጀር ታሆዋ ውስጥ ነዋሪ የሆነው የ45 ዓመቱ ማሐሙድ አብዱል ከድር «ሙርያር ታላካ» ለተሰኘ ድርጅት በማገልገል ላይ ይገኛል። ድርጅቱ በአማርኛ «የተራ ዜጎች ድምፅ» ሲሰኝ፤ የአፍሪቃ ኅብረትን አጥብቆ ነው የሚተቸው።

 «ይህን ድርጅት ገና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለሁ አንስቶ ነው የማውቀው። ያኔ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ነበር የሚባለው። የድርጅቱ አቢይ ተግባር አባል አገራቱን የጋራ በሆነ ርዕዮተዓለም ማሰባሰብ ነበር። ያሳዝናል ያ ግን አልተሳካም። የገዛ ግቡን እንኳን ማሳካት ተስኖት ምኞቱን ውሃ የበላው ነው የሚመስለው።»

በምስራቅ አፍሪቃዊቱ ታንዛኒያ ኢሪንጋ ነዋሪ የሆነው የ47 ዓመቱ የድረገፅ አምደኛ የአፍሪቃ ኅብረት የቀድሞ ዓላማ አህጉሪቱን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ማውጣት እንደነበር መንቀስ ይፈልጋል። በእርግጥ ዛሬ ከኅብረቱ ሌላ ስራ  መጠበቁ አልቀረም።

«ድርጅቱ በተለያዩ መድረኮች ላይ የአህጉሪቱን ድምፅ ከመወከሉ አንፃር ካጤንነው  የ50 ዓመቱ የኢዮቤልዩ በዓል ለአህጉሪቱ ታላቅ ትርጓሜ ነው ያለው። በአሁኑ ወቅት የአፍሪቃ ኅብረት ዋነኛ ተግዳሮት አህጉሪቱን ከተፅዕኖ ለማላቀቅ ኢኮኖሚያዊና ርዕዮተዓለማዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሠጥቶ መንቀሳቀሱ ነው።»  

በኪነሕንፃና የቱሪዝም ዘርፍ የድርጅት ባለቤት የሆነው የ29 ዓመቱ የሳዖቶሜና ፕሪንሲፔ ነዋሪ ኤነርሊድ ፍራንሷ  የአፍሪቃ ኅብረት ግቡን አልመታም ሲል እንዲህ ያብራራል።

«የአፍሪቃ ኅብረት ማለት ለእኔ የተሰናከለ ፕሮዤ ማለት ነው። መስራት የነበረበት እንደ አውሮጳ ኅብረት ነበር ። የአውሮጳ ኅብረት በ20 ዓመት ጉዞው እኛ ዛሬ 50ኛ ዓመቱን ከምናከብርለት ድርጅት በላቀ ብዙ ነገሮችን አሳክቷል። በሁለቱ መካከል እጅግ የገዘፈ ልዩነት ነው ያለው። በአፍሪቃ ኅብረት አባል አገራት መካከል የጋራ የሆነ ኢኮኖሚያዊ መርኅ እንኳን የለም። »


በዚምባቡዌ ዋና ከተማ ሐራሬ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ሆኖ የሚያገለግለው የ44 ዓመቱ ትጄኔሳኒ ንቱንጋካዋ በአፍሪቃ ኅብረት ታላቅ ተስፋ ነው የሰነቀው።

Afrikanische Union feiert 50. Jubiläum
ምስል AFP/Getty Images

«የአፍሪቃ ኅብረት ለእኔ አዲስ የተሰፋ ስንቅ ሆኖ ነው የሚታየኝ። እዚህ ዚምባብዌ ውስጥ አገራችንን በብሔራዊ ደረጃ የሚያስተሳስር መንግሥት እንዲኖረን እገዛ አድርጎልናል። ከእዛ በተጨማሪ  ከኮንጎ ግጭት ባሻገር በዚምባብዌ፣ በተወሰነ መልኩ በሩዋንዳና ብሩንዲ ውስጥ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።  እንደ አንድ የዚምባብዌ ዜጋ የአፍሪቃ ኅብረት እንደ ሶማሊያ ባሉ ግጭት ባዳቀቃቸው ቦታዎች ውስጥ ስኬታማ ተግባር ሊያከናውን እንደሚችል አምናለሁ።»

የአፍሪቃ ኅብረት የግማሽ ምዕተዓመቱን ጉዞ በተመለከተ የተለያዩ አፍሪቃውያን የሰጡትን አስተያየት ነበር ያደመጣችሁት። እናንተስ ድርጅቱ በ50 ዓመት ጉዞው ያደረገውን ጉዞ እንዴት ትመለከቱታላችሁ? ተወያዩበት።

ማንተጋፍቶት ስለሺ