1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ አንድነት የ50 ዓመት ጉዞ

ሰኞ፣ ግንቦት 12 2005

ሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2005 ዓ.ም. አምስት መዓልት ብቻ መቁጠር ይጠበቃል። ከእዚያም 50ኛ ዓመቱን ደፈነ ይባላል፤ የአፍሪቃ አንድነት። እጎአ 1963 ዓ ም፤ የቀን ቀመሩ በአጠቃላይ የጎርጎሮሳውያኑ ነው፤ ግንቦት 25። ነፃነቷን ከቅኝ ገዢዎች አስጠብቃ የቆየችው ኢትዮጵያ አፍሪቃውያን ወዳጆቿን እመዲናዋ ጠርታ ሽር ጉድ ይዛለች።

https://p.dw.com/p/18b77
Reproduction of a file photo dated 25 May 1963 shows the Ethiopian Emperor Haile Selassie (C) and Ghana's founder and first President Kwame Nkrumah (L) during the formation of the Organization of African Unity in Addis Ababa. Ghana, the first black African country to shake off the chains of British rule, celebrates the 50th anniversary of its independence 06 March 2007. AFP PHOTO (Photo credit should read STR/AFP/Getty Images)
Bildergalerie 50-jähriges Jubiläum der Afrikanischen Union AUምስል STR/AFP/Getty Images

ከ32 የአፍሪቃ አገራት የተውጣጡ ልዑካን አዲስ አበባ ከትመው ፊርማቸውን ያኖሩ ዘንድም በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ተጋብዘዋል። ንጉሠ ነገሥቱ በጉባኤው መክፈቻ ዕለት የሚከተለውን ታሪካዊ ንግግር አካሂደው ነበር።

«የተነሳሳንበትን ከፍተኛ ተግባር በመልካም አከናውነን ብንገኝ ስማችንና ግብራችን በታሪክ መልካም ስም ይኖረዋል። ተግባራችንን ሳንፈፅም ብንቀር ግን ይታዘንብናል። ስለእዚህ እምነታቸውን የጣሉብን ሕዝቦቻችን በሚመጡት ጊዜያቶች ውስጥ ከእኛ የሚጠብቁትን ሁሉ ለመፈፀም እንዲያበቃን ሁሉን የሚችለው ፈጣሪያችን ጥበብና አስተዋይነት እንዲሰጠን እናምነዋለን፣ እንለምነዋለን። »

በአፍሪቃ አንድነት ታሪክ እንደቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ሁሉ እቀዳሚው ተርታ ላይ ከሚሰለፉት ጥቂት፣ እውቅ ሰዎች መካከል የጋናው ፕሬዚዳንት ኩዋሜ ንኩሩማ ይገኙበታል። ንኩሩማ ከ1963ቱ የአዲስ አበባ ጉባኤ ቀደም ሲል፤ የካዛብላንካውን ቡድን ያስተባብሩ የነበሩ ሲሆን፤ የፓንአፍሪቃ አራማጆች አባት ተደርገውም ይቆጠራሉ።

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴምስል AP
የሴኔጋል ፕሬዚዳንትና ባለቅኔ ሊዮፖል ሴዳር ሴንጎር
የሴኔጋል ፕሬዚዳንትና ባለቅኔ ሊዮፖል ሴዳር ሴንጎርምስል picture-alliance/dpa
ለጥቁር የተከለከለ ቦታ ጆሐንስበርግ ደቡብ አፍቂቃ
ለጥቁር የተከለከለ ቦታ ጆሐንስበርግ ደቡብ አፍቂቃምስል Cover/Getty Images
የነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ
የነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላምስል F. Moalusi/AFP/Getty Images


ንኩሩማ በእዚያን ዘመን አፄ ኃይለስላሴ ከነበሩበት የሞንሮቪያው ቡድን ጋር በአስተሳሰብ ልዩነት ፍልሚያ ገጥመው የነበረ ቢሆንም ቅሉ፤ የአፍሪቃ አባቶች ያዘጋጁት ግብዣ ላይ ግን አልመጣም፥ ቀርቼያለሁ አላሉም። ለአፍሪቃ አንድነት መሰረቱን በኅብረት ለመጣል በአፍሪቃዊቷ መዲና፤ አዲስ አበባ ተገኝተው የሚከተለውን መልዕክት አስተላለፉ።

«ግርማዊነትዎ፥ ክቡር ፕሬዚዳንት፣ ክቡራን ተሳታፊዎች፣ ወንድሞችና ወዳጆች፤ ዛሬ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ከ32 አገራት ያላነሱ ተወካዮች ተገናኝተናል። የቁጥራችን መጨመር ሕዝባችን ለነፃነቱ ያሳየው ፅናትና ጥብቅ ትስስር ማረጋገጫ ነው። አህጉራችንን ለማዋሃድ መላው የአህጉሪቱ ነዋሪ በእዚህ ጉባኤ ላይ የኅብረታችንን መሰረት እንድናኖር ሃላፊነቱን ጥሎብናል።»


ከ32ቱ አገራት የተውጣጡት የአፍሪቃ ልዑካን አዲስ አበባ ውስጥ ፊርማቸውን አኖሩና የኅብረቱ መንደርደሪያ የሆነው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት OAU ለዓለም ይፋ ሆነ። የአፍሪቃ አንድነት እውን ከመሆኑ ጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ ግን ካዛብላንካና ሞንሮቪያ የተሰኙ ሁለት ቡድናት ተከስተው በየፊናቸው ለአፍሪቃ ይጨነቁ፣ ይጠበቡ፣ ብሎም ይጨቃጨቁም ነበር።

የካዛብላንካው ቡድን አራማጅ ጋና ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣችበት ዕለት አንስቶ አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት ኩዋሜ ንኩሩማህ ነበሩ። ቡድኑ በመላው ዓለም የሚገኙ አፍሪቃውያን እንዲተባበሩ የሚያጠይቀው የፓንአፍሪቃ ፅንሰ ሀሳብ በዋናነት ይቀነቀንበታል። የቡድኑ ዋነኛ ዓላማ መላ አፍሪቃን በፌዴሬሽን ማስተሳሰር የሚለው ነጥብ ነበር። አፍሪቃን ከቅኝ ግዛት ጭቆና ለማላቀቅ የተባበረ የአፍሪቃ ጦር መመስረት ያስፈልጋል ሲልም በወቅቱ ሞግቷል። ተቀናቃኙን ቡድን የኢምፔሪያሊዝም ጥገኞች ሲል በጥርጣሬ ይመለከት ነበር። ጋናን ጨምሮ አልጀሪያ፣ ጊኒ፣ ሞሮኮ፣ ግብፅ፣ ማሊ እና ሊቢያ የካዛብላንካው ቡድን አባላት ሆነው በታሪክ ተመዝግበዋል።


ሌላኛው የሞንሮቪያው ቡድን በመባል ይታወቃል። የለም አፍሪቃ ወደ ኅብረት መምጣት ያለባት እንዲህ በጥድፊያ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ትብብርን መሰረት ባደረገ ሂደት ነው ሲል አጥብቆ ተከራክሯል። ኢትዮጵያ፣ ሴኔጋል፣ ናይጀሪያ፣ ላይቤሪያ እና በአፍሪቃ የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች አባላቱ ሆነው ተመዝግበዋል። ቡድኑን ከቅኝ ግዛት ዘመን መልስ የመጀመሪያው የሴኔጋል ፕሬዚዳንትና ባለቅኔ ሊዮፖል ሴዳር ሴንጎር ያራምዱት ነበር። ቡድኑ የአፍሪቃ ጦር መመስረት የሚለውን የእነኩዋሜ ንኩሩማህ ሀሳብ በጥርጣሬ ብቻ ሳይሆን በስጋት ነበር የተመለከተው። የጋራ ጦር ከተመሰረተ የፓንአፍሪቃ አራማጆቹ እንኩዋሜ ንኩሩማህ ከስልጣናችን ያስወግዱናል ሲል ሰግቶ እንደነበረም በታሪክ ሰፍሮ ይገኛል።

ይህ በሁለቱ ቡድናት መካከል በ1960ዎቹ መንደርደሪያ ላይ የተጀመረው ንትርክ በ1963 አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ጉባኤ ቡድናቱ ወደ አንድ አቋም በመጡበት ሁናቴ ሊረግብ ችሏል። ይሁንና ልዩነቱ መልኩን ቀይሮም ቢሆን ዛሬም ድረስ በኅብረቱ እውን ሆኖ ይስተዋላል። ይህንና ሌሎች ነጥቦችን በማንሳት በተለይ የአፍሪቃ አንድነትን አቅመቢስነት የሚተቹ አካላት አንድነቱንም ኅብረቱንም በጥቅል «ጥርስ አልባ አንበሳ» ሲሉት ይደመጣል። አምባሳደር መንግስቴ ደስታ የአፍሪቃ አንድነት ሲመሰረት ጀማሪ ዲፕሎማት ነበሩ፤ አንድነቱ ላይ የተሰነዘረውን ትችት አይቀበሉም።

«የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ጥርስ አልባ ነበር የሚባለውን ፈፅሞ አልስማማበትም። ጠንካራ ጥርስ ነበረው። ሲመሰረት ቀዳሚ ዓላማው ምን ነበር የሚለውን ነቅሶ ማውጣት ያስፈልጋል። ዓላማው መላው አፍሪቃን ከቅኝ አገዛዝ፣ ከዘረኝነትና ከአፓርታይድ ስርዓት ማላቀቅ ነበር። »


በእርግጥም አፍሪቃ ዙር አዙር ካልሆነው የባዕዳን ቅኝ አገዛዝና ዘረኛ የአፓርታይድ ስርዓት ነፃ ወጥታለች። የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የመግባቢያ ሠነድ በ1963 አዲስ አበባ ላይ ከተፈረመ በኋላ ድርጅቱ በቀዳሚነት የተንቀሳቀሰው በቅኝ ግዛት ይማቅቁ የነበሩ አፍሪቃዊያት አገራት ለነፃነት የሚያደርጉትን ፍልሚያ መደገፍ ነበር። የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የመጀመሪያው ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ዓፄ ኃይለሥላሴም የመግባቢያ ሠነዱ በተፈረመበት ወቅት ይህንኑ በአንክሮ ገልፀው ነበር።

«በሮዴሺያ፣ በአንጎላ፣ በደቡብ አፍሪቃ፣ በሞዛምቢክ፣ በሌሎችም አገሮች የሚኖሩት ወንድሞቻችን ሙሉ ርዳታ እንድንሰጣቸው በመጮህ ላይ ይገኛሉ። ይህ ልመናቸው ሊታለፍ ከቶ አይገባም።»

ከዓጼ ኃይለስላሴ ንግግር በኋላ አፍሪቃውያንን ከቅኝ አገዛዝ እንዲላቀቁ የመርዳቱ ሂደት ወዲያው ነበር ወደተግባር የዋለው። ለአብነት ያህል ምንጊዜም የአፍሪቃ የነፃነት ዓርማ ተደርገው የሚወሰዱት የደቡብ አፍሪቃው የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ኢትዮጵያ ገብተው አዲስ አበባ፣ ኮልፌ የሚገኘው ማሰልጠኛ ውስጥ የቡጢና የትጥቅ ትግል ልምምድ ማድረግ ችለዋል። ናሚቢያና ደቡብ አፍሪቃን ከአናሳ ነጮች የጭቆና አገዛዝ ነፃ ለማውጣት በሚል በአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ስር «ነፃ አውጭ ኮሚቴ» የተሰኘ ቡድን ተቋቁሞም ታንዛንያ ውስጥ ስራውን የጀመረው አንድነቱ በተመሰረተበት ዓመት ነበር። በሂደት ደቡብ አፍሪቃን ጨምሮ መላ የአፍሪቃ አገራት ከቅኝ አገዛዝ ቀንበርና ከአፓርታይድ፥ ዘረኛ ጭቆና ለመላቀቅም በቅተዋል።


«በእኛ ስምና ለእኛ ሲሉ ህይወታቸውን የሰጡት አፍሪቃውያን በተሰበሰቡበት ስፍራ ሁሉ ስማቸው ህያው ሆኖ ይኖራል፤ ሀውልትም ሊቆምላቸው ይገባል።»

ዛሬ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ምንም እንኳን በተግባር ትችት ባይለየውም ወደኅብረት ግን ማቅናት ችሏል። ኅብረቱ ከ10 ዓመታት በኋላ በቻይና መንግስት የተገነባለት አዲስ ዘመናዊ ሕንፃ ቅጥር ውስጥ የካዛብላንካው ቡድን አራማጅ የኩዋሜ ንኩሩማህን ሀውልት ለመታሠበያ አቁሞዋል። በአንፃሩ ለአፍሪቃ ነጻነትና አንድነት ታላቅ ገድል የፈፀሙት የዓፄ ኃይለሥላሴ ሀውልት በቅፅሩ ያለመኖሩ ጉዳይ በርካታ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን ሳይስቆጭ አላለፈም።

«ለአፍሪቃ ነጻነት የረዱትንም ሁሉ ልንረሳቸው አይገባም። »

የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት በረዥሙ ጉዞው የተለያዩ አካባቢያዊ የንግድ ማኅበረሰቦችን ማቋቋሙ እንደ አንድ እመርታ ይቆጠርለታል። ሆኖም የምስራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብን ጨምሮ ኢኮዋስ፣ ሳዴክ ኮሜሳና የማግሬብ ኅብረት የተሰኙት የአካባቢ የኢኮኖሚ ትብብር ድርጅቶች በአፍሪቃ ኅብረት ጥላ ስር ያላቸው የቀረጥና ግብር አሰባሰብ ስርዓት የአንዱ አካባቢ ማኅበረሰብ ከሌላኛው ጋር በቀላሉ የንግድ ልውውጥ እንዲያደርግ የተለሳለሰ መንገድ አላበጀም። አንዳንድ ተንታኞች አፍሪቃዊ አገር በኅብረቱ ጥላ ስር ከሚገኝ ሌላ አገር ጋር የንግድ ልውውጥ ከማድረግ ይልቅ ከአውሮጳ ኅብረት ጋር የሚያደርገው የንግድ ሽርክና ይቀለዋል ሲሉ ይተቻሉ። የፌዴራል ጀርመን መንግስት የአፍሪቃ ልዑክ ኤ ኮቻንኬ ኅብረቱ በተለያየ መስክ የአውሮጳ ድጋፍ እንደሚደረግለት ጠቅሰዋል።

«ቀደም ሲል እንደገለፅኩት አፍሪቃውያንን በመልካም አስተዳደር፣ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ፣ እንዲሁም ሌላኛው በጣም ጠቃሚ በሆነው የመሠረተ ልማት አውታሮችን የማጠናከር ጉዳይ መርዳታችንን መቀጠል እንፈልጋለን። በተጨማሪም በአፍሪቃ ኅብረት ውስጥ የሚጠቃለለው የፓንአፍሪቃ ምክር ቤትም ከእኛ ድጋፍ ይደረግለታል። እዚያ የምናከናውናቸው ነገሮች አሉ። እናም እንደ አፍሪቃ ኅብረት ያለ ተቋም በውጭ እና አፍሪቃ ውስጥ ባለው የፀጥታ መርኅ ወደፊት ግጭቶችን ለመከላከልና በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚችል ይሆናል ብለን እናምናለን። »

የጋናው ፕሬዚዳንት ኩዋሜ ንኩሩማ
የጋናው ፕሬዚዳንት ኩዋሜ ንኩሩማምስል Getty Images
የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ከምስረታው 3 ዓመታት በኋላ
የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ከምስረታው 3 ዓመታት በኋላምስል AFP/Getty Images
የአፍሪቃ ኅብረት ሠላም አስከባሪ ጦር
የአፍሪቃ ኅብረት ሠላም አስከባሪ ጦርምስል M. Longari/AFP/Getty Images
ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ የኅብረቱ ሊቀመንበር
ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ የኅብረቱ ሊቀመንበርምስል picture-alliance/dpa


የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ወደኅብረትነት የተቀየረው ሐምሌ 9 ቀን 2002 ዓም ሲሆን፤ የወቅቱ የድርጅቱ የመጨረሻ ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ ነበሩ። የኅብረቱ መመስረቻ ጉባኤ ደቡብ አፍሪቃ ደርባን ላይ በተካሄደበት ወቅት መቀመጫው አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን ከውሳኔ ተደርሷል። ከውሳኔው ሶስት ዓመታት ቀደም ብሎ ደግሞ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ሊቢያ፥ ሲርት ከተማ ላይ ባካሄደው ልዩ ጉባኤው የሊቢያ የያኔው መሪ ኮሎኔል ሙኣማር ጋዳፊ የሚመሰረተው የአፍሪቃ ኅብረት የአውሮጳውያኑን ኅብረት በምሳሌነት እንዲወስድ ሀሳብ አቅርበው ነበር። አህመድ ጋዳፋዳድ የተሰኘው ልጃቸው ደግሞ እንደአሜሪካን ሁሉ United States of Africa እንድትመሰረት ምኞቱን በእዚህ መልኩ ገልጾ ነበር።

«በእርግጥ በቂ አይደለም፤ ሆኖም በአንድነት ወደፊት እናቀናለን። እናም እርግጠኛ ነኝ፤ ከቀን ወደ ቀን ግባችን ወደሆነው የተባበሩት የአፍሪቃ አገራት ምስረታ እንደርሳለን።»

የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ምንም እንኳን በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ ጠንካራ ሆኖ ለመውጣት ማለሙ ባይቀርም በርካታ ጦርነቶችና የሠብዓዊ ጥሰቶች የሚስተናገድበት አህጉር ከመሆን አላመለጠም። አህጉሩ የቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት የፍልሚያ አውድማ ሆኖ የታሪክ ጠባሳ ትቶ አልፏል። ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ያደረገችው ጦርነት የእዚሁ የቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት ግለት አንዱ ማሳያ ነበር።


ሶማሊያ መንግስት አልባ ሆና ለሁለት አስርት ዓመት ስትዘልቅ የአንድነት ድርጅቱም ሆነ ኅብረቱ ፈጣን ምላሽ መስጠት ተስኖት ቆይቷል። በሩዋንዳ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በዘር ፍጅት ሲያልቅ፣ በሱዳን ዳርፉር ሠብዓዊ መብት አለቅጥ ሲጣስ፣ በኢትዮጵያ ረሀብ ሚሊዮኖችን እንደቅጠል ሲያረግፍ ይኸው ድርጅት ይህ ነው የተባለ ነገር አልፈፀመም። በ2005 የኢትዮጵያ ምርጫ የኅብረቱ መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ምርጫ ተጭበረበረ ብለው አደባባይ በወጡ በርካታ ዜጎችና በፀጥታ ኃይላት መካከል በተከሰተ ግጭት በርካቶች ሲገደሉ ኅብረቱ አይቶ እንዳላየ ማለፉን ነበር የመረጠው። የአረቡ አብዮትን ተከትሎ በግብፅ፣ በሊቢያና በኮትዲቯር በታዩ ውዝግቦች ወቅትም ይኸው ኅብረት የውጭ ጣልቃ ገብነትን አስወግዶ በመስራት የሚጠበቅበትን ሳያደርግ ነው የቀረው በሚል ይወቀሳል።

የኅብረቱ ሠላም አስከባሪ ጦር በዳርፉር ሶማሊያና ኮንጎ ሰፍሮ ቢገኝም በተለይ በኮንጎ የሚታየውን አመፅና ጥፋት ማቆም የተሳነው ይመስላል። መሪዎቿ መደማመጥ ተስኗቸው የኅብረቱን ሊቀመንበር ሳይመርጡ የተለያዩበት ወቅትም የቅርብ ጊዜ ትዝታ በመሆን ዓለምን አስደምሞ አልፏል። በእርግጥ በስተመጨረሻም ቢሆን ደቡብ አፍሪቃዊቷ ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማን የመጀመሪያዋ ሴት ሊቀመንበሩ አድርጎ መርጧል። ሊቀመንበሯ ለኅብረቱ የሰነቁትን ራዕይ እንዲህ ይገልፃሉ።


«መንግስታቱ ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ነው መተባበር ያለበት። የአህጉሪቱ ነዋሪዎች በአጠቃላይ ሊያከብሩና ወደፊት በቀጣዮቹ 50 ዓመታት ውስጥ ማየት የምንፈልጋት አፍሪቃ ምን ትመስላለች ሲሉ ለራሳቸው መግለጽ ይገባቸዋል። የምናከብረው ባለፉት 50 ዓመታት ያሳካነውን ነው። ያ እንዲሳካ ስላደረጉት ጀግኖቻችንም እናከብራለን »

አፍሪቃ ውስጥ ከ1960 እስከ 1990 ድረስ ባሉት ዓመታት አንድም ገዢ ፓርቲ ስልጣን በገዛ ፍቃዱ ሲለቅ አልታየም። መፈንቅለ መንግስትና የምርጫ ማጭበርበር በአፍሪቃ የተለመደ ይመስላል። ያም በመሆኑ ኅብረቱ ማዳጋስካር፣ ጊኒ ቢሳዎና መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክን ስልጣን በኃይል ይዛችኋል ሲል ከአፍሪቃ ኅብረት አባልነታቸው አግዷቸዋል። የጋና ዲሞክራሲ ግን ሳይጠቀስ አይታለፍም።

የአፍሪቃ ኅብረት 54 አባል አገራት ሲኖሩት አህጉሪቱ ውስጥ ሆና የአፍሪቃ ኅብረት አባል ያልሆነች አንድ አገር ትገኛለች፤ ሰሜን አፍሪቃዊቷ ሞሮኮ። የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ለምዕራብ ሠሐራ ዕውቅና መስጠቱን ተከትሎ ሞሮኮ ከአፍሪቃ አንድነት ድርጅት አባልነቷ ራሷን ካገለለች 20 ዓመታት ሊሞላት ነው። አፍሪቃ በግማሽ ምዕተ ዓመት ጉዞዋ ያሳለፈችው ውጣ ውረድ እንዲህ በቀላሉ ተገልፆ የሚታለፍ አይደለም። የሆኖ ሆኖ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የመግባቢያ ሠነድ አዲስ አበባ ላይ ከተፈረመ 50ኛ ዓመቱ የፊታችን ቅዳሜ ይሞላና ለሌላ 50ኛ ዓመት መንደርደሩን ይቀጥላል።


ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ