1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ዋንጫ.፣ አትሌቲክስ፣ ቴኒስ

ሐሙስ፣ ጥር 24 2004

የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ወደ ሩብ ፍጻሜው እየተሸጋገረ ነው። የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ወደ ሩብ ፍጻሜው እየተሸጋገረ ሲሆን አስተናጋጆቹ ሃገራት ኤኩዋቶሪያ ጊኒና ጋቡን ጠንከር ባሉ ምድቦቻቸው ውስጥ ፉክክሩን በመቋቋም

https://p.dw.com/p/13tBe
ምስል AP

ወደፊት መዝለቃቸው ታዛቢዎችን ጥቂትም ቢሆን ሳያስደንቅ አልቀረም። ውድድሩ ከመከፈቱ በፊት የእነዚህ ሁለት አገሮች መጨረሻ የመጀመሪያው የምድብ ዙር ይሆናል ሲሉ የተነበዩት ጥቂቶች አልነበሩም። በምድብ-አንድ ውስጥ ኤኩዋቶሪያል ጊኒ ምንም እንኳ ትናንት በዛምቢያ 1-0 ብትረታም በስድሥት ነጥቦች በሁለተኝነት ወደ ሩብ ፍጻሜው ማለፉ ተሳክቶላታል። በሰባት ነጥቦች የምድቡ አንደኛ የሆነችው አንዴም ያልተሽነፈችው ዛምቢያ ናት።

በዚሁ ምድብ ውስጥ ሊቢያ ሶሥተኛ ሆና ስትቀር በውድድሩ መክፈቻ ግጥሚያ በኤኩዋቶሪያል ጊኒ መሸነፏ ለክስረቷ ወሣኝ መሆኑ የኋላ ኋላ በግልጽ ታይቷል። ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ሤኔጋል ባልታሰበ ሁኔታ በሶሥቱም ግጥሚያዎቿ ተሽንፋ በዜሮ ነጥብ ከውድድሩ መሰናበቷ ነው። የሆነው ሆኖ ይህ ምናልባት ብዙዎች ያልጠበቁት ውጤት እምብዛም የሚያስደንቅ አይደለም። አፍሪቃ ውስጥ ትናንሽ የተባሉት ሃገራት እየጠነከሩ ለመቀጠላቸው እንደገና ጥሩ ምስክር ነው። አለበለዚያ ግብጽን፣ ናይጄሪያን፣ ካሜሩንንና ደቡብ አፍሪቃን የመሳሰሉት ቀደምት ሃገራት በማጣሪያው ተሰናክለው ባልቀሩ ነበር። ውድድሩን የሚታዘበው የቀድሞው የአይቮሪ ኮስት ኮከብ ተጫዋች ሎራን ፖኩም እንዲሁ ያረጋገጠው ፉክክሩ እየተጠናከረ መሄዱን ነው።

“እግር ኳስ ጨዋታ እርግጥ ዕድልንም ይጠይቃል። ግን ደግሞ የፉክክር ብቃትና ችሎታም ወሣኝነት አለው። እና ለሩብ ፍጻሜ ያለፉትም ቡድኖች ቢሆኑ ገና ከባድ ትግል ነው የሚጠብቃቸው። እንግዲህ ስምና ዝና ብቻውን በቂ አይደለም። ሜዳ ላይ የሚታየው ጨዋታ ነው ወሣኙ”

ከምድብ-ሁለት አይቮሪ ኮስት በቀደምትነት ወደ ሩብ ፍጻሜው ዙር ስታልፍ ከሱዳን 2-2 የተለያየችው አንጎላ በሁለተኝነት የማለፍ ትልቅ ዕድል አላት። እርግጥ ሱዳን ቡርኪና ፋሶን ካሸነፈችና አንጎላ ደግሞ በአይቮሪ ኮስት ከተረታች ሁለቱ ቡድኖች እኩል አራት ነጥብ ስለሚኖራቸው የጎል ብልጫ ወሣኝ ሊሆን ይችላል። በምድብ-ሶሥት ውስጥ ሌላዋ አብሮ አስተናጋጇ ጋቡን ምንም እንኳ ከባድ ምድብ ቢገጥማትም ፈተናዋን በታላቅ ብቃት ነው የተወጣችው። ጋቡን በእኩል ስድሥት ነጥብ ቱኒዚያን በሁለተኝነት አስከትላ ከወዲሁ ወደ ሩብ ፍጻሜው ዙር ስታልፍ ብዙ የተጠበቀባት ሞሮኮ ደግሞ እንደ ኒጀር ሁሉ በባዶ ነጥብ ከወዲሁ ወድቃ ቀርታለች።
ሞሮኮ በነገው ዕለት ከኒጀር የምታደርገው ግጥሚያ የሚለውጠው ምንም ነገር የለውም። የጋቡንና የቱኒዚያ ግጥሚያም የምድቡን አንደኛ ከመወሰን አያልፍም። በምድብ-አራት ጋናና ጊኒ አንደኛና ሁለተኛ ሲሆኑ ማሊ ሶሥተኛ ናት። የምድቡ ሁለተኛ ማንነት ጊኒ ወይም ማሊ የሚለይለት ከነገ በስቲያ ረቡዕ ነው። ሩብ ፍጻሜው ግጥሚያዎች በፊታችን ቅዳሜና ዕሑድ የሚካሄዱ ሲሆን የቀጣዩን ሣምንት ግማሽ ፍጻሜ አቋርጦ የዋንጫው ግጥሚያ የሚደረገው ዕሑድ፤ የካቲት አራት ቀን ይሆናል።

በአፍሪቃ እግር ኳስ ላይ ካተኮርን አይቀር የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በአፍሪቃ ሻምፒዮና ውድድር ግብጽን አዲስ አባባ ላይ በተካሄደ ግጥሚያ አራት-ለባዶ በማሽነፍ ታላቅ ድል ተቀዳጅቷል። ቡድኑ ከሁለት ሣምንታት በፊት ካይሮ ላይ ባደረገው የመጀመሪያ ግጥሚያ 4-2 ተረትቶ መመለሱ የሚታወስ ነው። ብሄራዊው ቡድን ቀጣዩን ግጥሚያ የሚያካሂደው ከታንዛኒያ ጋር ይሆናል።

አትሌቲክስ

የኢትዮጵያ አትሌቶች ባለፈው አርብ የዱባይ-ማራቶን ፍጹም የበላይነት በማሣየት ለእጥፍ-ድርብ ድል በቅተዋል። በወንዶች ከአንድ እስከ ሶሥት በመከታተል ያሸነፉት አየለ አብሸሮ፣ ዲኖ ሰፊርና ማርቆስ ገነቲ ነበሩ። በሴቶችም አሰለፈች መርጊያ ስታሽንፍ፣ ኬንያዊቱ ሉሢ ካቡ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ማሬ ዲባባ ሶሥተኛ ወጥታለች። የኢትዮጵያ አትሌቶች በዱባዩ ማራቶን ከማሸነፋቸው ባሻገር ያስመዘገቡትም ጊዜ እጅግ ግሩም ነበር። በወንዶች ከሁለት ሰዓት ከአምሥት ደቂቃ በታች፤ በሴቶችም ከሁለት ሰዓት ሃያ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ነው ሩጫቸውን የፈጸሙት።

ጃፓን-ኦሣካ ላይ በተካሄደ ሌላ የሴቶች ማራቶን ሩጫ ደግሞ የአገሪቱ ተወላጅ ሪዛ ሺጌቶሞ በሁለተኛ የማራቶን ተሳትፎዋ አሸናፊ በመሆን በመጪው የለንደን ኦሎምፒክ የመሳተፍ ተሥፋዋን ልታጠናክር ችላለች። የ 24 ዓመቷ አትሌት ሩጫውን የፈጸመችው በሁለት ሰዓት ከ 23 ደቂቃ 23 ሤኮንድ ጊዜ ነበር። የኡክራኒያዋ ቴቲያና ሽሚርኮ ሁለተኛ ስትሆን ሶሥተኛ የወጣችው ጃፓናዊቱ አዙሣ ኖጂሪ ናት።

እግር ኳስ፤ ቡንደስሊጋ/ አውሮፓ

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ሬያል ማድሪድ በሣምንቱ አጋማሽ በባርሤሎና ተረትቶ ከንጉሣዊው ዋንጫ “ኪንግስ-ካፕ” ጥሎ ማለፍ ውድድር ከተሰናበተ በኋላ ሰንበቱን ከሽንፈቱ መልሶ አገግሟል። በፖርቱጋላዊው አሰልጣኝ በሆሴ ሞሪኞ የሚመራው የማድሪድ ክለብ በሰንበቱ ግጥሚያው ሬያል ሣራጎሣን 3-1 ሲረታ የሊጋ አመራሩን ወደ ሰባት ከፍ ሊያደርግ በቅቷል። ለዚሁም ምክንያት የሆነው ዋነኛ ተፎካካሪው ባርሣ ከቪላርሬያል ባዶ-ለባዶ በሆነ ውጤት መወሰኑ ነው። ለሬያል ማድሪድ ጎሎቹን ያስቆጠሩት ካካ፣ ክሪስቲያኖ ሮናልዶና ሜሱት ኦዚል ነበሩ። ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ባርሤሎና ዘንድሮም የበላይነቱን ለማስከበር ከባድ ትግል የሚጠብቀው ነው የሚመስለው። ሶሥተኛው ቫሌንሢያ ሲሆን በነገራችን ላይ በፊታችን ረቡዕ የኪንግስ-ካፕ ግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር የባርሤሎና ተጋጣሚ ነው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙንሺን ቮልፍስቡርግን 2-0 በመርታት በጎል ብልጫም ቢሆን በአመራሩ ቀጥሏል። ለባየርን ድሉ በብዙ ትግል የተገኘ ሲሆን ቡድኑ ቀደም ካለ ድክመቱ በመላቀቅ ላይ መሆኑን ነው ሆላንዳዊ አጥቂው አርየን ሮበን የተናገረው።

“ጨዋታው ምናልባት በጣም ጥሩ የሚባል አልነበረም። ግን መሻሻል መኖሩን ታዝበናል። እናም በዚሁ በመቀጠል በትጋት መሰልጠንና መስራት ነው ያለብን። ዛሬ ከበፊቱ የበለጠ ታግለናል ለማለት እወዳለሁ”

ዶርትሙንድና ሻልከም የየበኩላቸውን ግጥሚያ በማሸነፍ ሲወጡ በመሳሳይ አርባ ነጥቦች ባየርንን በቅርብ ይከተላሉ። ግላድባህ ደግሞ አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ አራተኛ ነው። ብራመንና ሌቨርኩዝን በበኩላቸው 1-1 በመለያየት ከአመራሩ ብዙ ላለመራቅ የነበራቸውን ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በዚሁ የተነሣ በግላድባህና በአምሥተኛው በብሬመን መካከል ያለው ልዩነት ወደ ስምንት ሊሰፋ በቅቷል።

በእንግሊዝ ሣምንቱ የፕሬሚየር ሊጉ መደበኛ ጨዋታዎች ሣይሆን የፌደሬሺኑ ዋንጫ FA Cup አራተኛ ዙር ግጥሚያዎች የተካሄዱበት ነበር። ከነዚሁም ዋነኛው በነበረው ግጥሚያ ሊቨርፑል ማንቼስተር ዩናይትድን 2-1 በማሸነፍ ከውድድሩ አሰናብቷል። ቼልሢይም ኩዊንስ-ፓርክ-ሬንጀርስን 1-0 በማሸነፍ ወደተከታዩ ዙር ካለፉት ክለቦች አንዱ ነው። በሌሎች ግጥሚያዎች ደግሞ አርሰናል ኤስተን ቪላን 3-2 ሲረታ ኒውካስል ዩናይትድ በአንጻሩ በዝቅተኛው የሁለተኛ ዲቪዚዮን ክለብ በብራይተን ተሸንፎ ከውድድሩ ወጥቷል።

በተቀረ በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ጁቬንቱስ በአንዲት ነጥብ ልዩነት ኤ.ሢ.ሚላንን አስከትሎ መምራቱን ሲቀጥል በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን ደግሞ አይንድሆፈን አንደኝነቱን ለመያዝ በቅቷል። ትዌንቴ ሁለተኛ፤ አልክማር ሶሥተኛ! በፈረንሣይ ሊጋ ፓሪስ-ሣንት-ዠርማንና በፖርቱጋል ሻምፒዮና ደግሞ ቤንፊካ ሊዝበን አሁንም ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።

ቴኒስ፤ አውስትሬሊያን-ኦፕን

በአዲሱ 2012 ዓ.ም. የመጀመሪያው የሆነው ታላቅ የቴኒስ ውድድር የአውስትሬሊያን-ኦፕን ፍጻሜ ሰንበቱን በወንዶችም ይሁን በሴቶች ከቴኒስ አፍቃሪዎች ባሻገር በአጠቃላይ ስፖርት ላይ ዓይኑን ላሳረፈ ሁሉ ማራኪ ሆኖ ነው ያለፈው። በወንዶች በስፓኙ ተወላጅ በራፋኤል ናዳልና በሰርቢያው ኮከብ በኖቫክ ጆኮቪች መካከል የተካሄደው የፍጻሜ ግጥሚያ ማራቶን አምሥት ሰዓት ከ 53 ደቂቃ በመፍጀት እስከዛሬው ንጋት ድረስ ሲዘልቅ የስፖርተኞቹን ነርቭ ብቻ አልነበረም የጨረሰው። የ 24 ዓመቱ ጆኮቪች ከዚህ የአምሥት ምድብ ጨዋታ ድሉ በኋላ በሶሥት ታላላቅ የቴኒስ-ኦፕን ግጥሚያዎች በተከታታይ በማሸነፍ ፒት ሣምፕራስ፣ ሮጀር ፌደረርና ናዳል ይዘው ለቆዩት ክብር በቅቷል። ጆኮቪች ዛሬ በወጣው አዲስ የዓለም ቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይም ቀደምቱ እንደሆነ ነው የቀጠለው።

በሴቶችም የቅዳሜው የሜልበርን የፍጻሜ ግጥሚያ እንደ ወንዶቹ ብዙ ሰዓታት አያስቆጥር እንጂ ተመልካችን ቁጭ-ብድግ ያሰኘ ነበር። 82 ደቂቃዎች በፈጀው ግጥሚያ በመጨረሻ ሩሢያዊቱ ማሪያ ሻራፖቫ በቤላሩስ ተጋጣሚዋ በቪክቶሪያ አዛሬንካ መረታቱ ግድ ሆኖባታል። ሻራፖቫ ታዲያ ተጋጣሚዋን በማወደስ ሽንፈቷን በጥሩ የስፖርት መንፈስ ነው የተቀበለችው። ለዚህም በእርአያነት ልትወደስ ይገባታል።
“በማንኛውም ስፖርት እንደተለመደው ሁሉ አንዳንዴ ጥሩ ቀን ይገጥምሃል፤ አንዳንዴ ደግሞ አንድም ነገር አይሆንልህም። እና ዛሬ ቪክቶሪያ በብዙ ነገሮች የተሻለችዋ ነበረች። ግሩም ነው የተጫወተችው”

ድሉ ለቪክቶሪያ አዛሬንካ የመጀመሪያው ታላቅ ድል ብቻ አልነበረም። በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ አንደኝነቱን እንድትይዝም አብቅቷታል። በአዲሱ አሰላለፍ የዴንማርኳ ካሮሊን ቮዝኒያችኪ ከአንድ ወደ አራት ስታቆለቁል የቼኳ የዊምብልደን ሻምፒዮን ፔትራ ክቪቶቫ አሁንም በሁለተኝነቷ እንደጸናች ነው። ሻራፖቫ ሶሥተኛ!

ለማጠቃለል፤ ሰርቢያ ውስጥ ሲካሄድ የቆየው የአውሮፓ የዕጅ ኳስ ሻምፒዮና ትናንት በዴንማርክ ድል ተፈጽሟል። ዴንማርክ ለዚህ ድል የበቃችውና የለንደን ኦሎምፒክ ተሳትፎ ዕድሏንም ያረጋገጠችው አስተናጋጇን ሰርቢያን በፍጻሜው ግጥሚያ 21-19 በመርታት ነው።

መሥፍን መኮንን

July 30, 2011 - Stanford, California, U.S - Victoria Azarenka (BLR) competes during a doubles semifinal at the Bank of the West Classic at the Taube Family Tennis Center in Stanford, CA. Azarenka and partner Maria Kirilenko (RUS) advanced with a 4-6, 6-3 (10-5) win pixel
ምስል picture alliance/ZUMA Press
Fußball 1. Bundesliga Saison 2011 2012 19. Spieltag FC Bayern München gegen VfL Wolfsburg Allianz Arena München
ምስል dapd

ተክሌ የኋላ