1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ የእርሻ መሬትና የውጭ መዋዕለ-ነዋይ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 15 2001

ርካሽ የምግብና የባዮ-ነዳጅ ምርት ለማግኘት በአፍሪቃ የእርሻ መሬት ላይ ዓይናቸውን የሚያሳርፉት የውጭ ባለሃብቶች ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው።

https://p.dw.com/p/Hc9T

በርካታ የአፍሪቃ መንግሥታትም እንዲሁ ለም የእርሻ መሬትን ለምሳሌ የእሢያና ሳውዲት አረቢያን ለመሳሰሉት አገሮች መሸጡን ወይም ማከራየቱን በሰፊው ተያይዘውታል። የነዳጅና የሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች ዋጋ ማቆልቆል፤ የመዋዕለ-ነዋይ እጥረትና የቱሪዝም ገቢ መቀነስ፤ እንዲሁም ፈላሽ አፍሪቃውያን በተለይም በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ወደ አገር የሚልኩት ገንዘብም እየመነመነ መሄድ ለገበያው መድራት አስተዋጽኦ ሳይኖረው አልቀረም። ችብችባ ወይስ አረንጓዴ ዓብዮት? ለመሆኑ አገሬው ሕዝብ ከዚህ ምን የሚያገኘው ጥቅም አለ?

መሬት ርካሽ የሆነበት ቦታ እረስ! ዛሬ በርከት ባሉ የአፍሪቃ አገሮች ውስጥ በአሠርተ-ዓመታት ኪራይ በተግባር ከተሰማሩትና ምናልባትም ወደፊት ለመሰማራት ከሚፈልጉት የውጭ መዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ፍልስፍና በስተጀርባ ያለው ሃቅ ይህ ነው። በሌላ በኩል የምግብ ዋጋ መናር ከፍተኛ በሆነባትና የረሃብተኛው ቁጥር እየጨመረ በሄደባት በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ለም መሬት ተቆርሶ ለውጭ መንግሥታት ወይም የግል ባለሃብቶች መሰጠቱ ብዙ የሚያከራክር ጉዳይ ሆኗል። የምግብ እጥረትና የኑሮ ውድነት ያስከተለው ብርቱ ችግር ማሕበራዊ ፈንጂ ሆኖ ብዙዎች አገሮችን ከለየለት ቀውስ ላይ እንዳይጥል ባሰጋበት በዛሬው ጊዜ ጉዳዩ ከባድ የሞራል ጥያቄን የሚያስነሣ ነው። አንዳንድ ተቺዎች የውጭ ባለሃብቶች በአፍሪቃ የያዙትን የለም መሬት ዘመቻ አዲስ ቅኝ አገዛዝ እስከማለትም ደርሰዋል።

አፍሪቃውያን መንግሥታት የያዙት የመሬት ችብችባ በክፍለ-ዓለሚቱ ሕዝብ ዘንድም የቁጣ መንስዔ እየሆነ መሄዱ ቢቀር በማዳጋስካር ምሳሌ በቅርብ የታየ ጉዳይ ነው። የቀድሞውን ፕሬዚደንት ማርክ ራቫሎማናናን ከሥልጣን ለፈነቀለው የደሴቲቱ ዓመጽ መነሻው ይህ እንጂ ሌላ አልነበረም። ራቫሎማናና 1,3 ሚሊዮን ሄክታር ስፋት ያለውን የደሴቲቱን መሬት ለደቡብ ኮሪያው ኩባንያ ዴው ለ 99 ዓመታት በኪራይ ለመስጠት ተነስተው ነበር። ይህም ከማዳጋስካር ለም መሬት ግማሹ መሆኑ ነው። ሃሣቡ ቢሳካ የኮሪያው ኩባንያ በጣም ርካሽ በሆነ ክፍያ በመሬቱ ላይ በቆሎና የወይራ ዘይት ተክል በማልማት ወደ እሢያ በመርከብ እየጫነ ለመላክ ነበር የወጠነው። ዴው እንዳለው በአንጻሩ 70 ሺህ የሥራ መስኮችንም መክፈት ይቻል ነበር።

ግን ስምምነቱ ገና ይፋ ከመውጣቱ የሕዝቡ ቁጣና ተቃውሞ ደሴቲቱን ማናወጽ ይጀምራል። የተቀረው ቁጣው የፕሬዚደንት ራቫሎማናናን ውድቀት ማስከተሉ ነው። ከሥልጣን የፈነቀሏቸው አዲሱ መሪ አንድሪይ ራጆሊና ደግሞ ውሉን ወዲያው ውድቅ አድርገውታል። ይህ እርግጥ የማዳጋስካር ሃቅ ብቻ አይደለም። የእርሻ መሬቶቻቸውን ለውጭ ባለሃብቶች ለሽያጭ ወይም ለኪራይ የሚያቀርቡት የአፍሪቃ አገሮች ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው የሚገኘው። በአፍሪቃ ለም መሬት ለመጠቀም በክፍለ-ዓለሚቱ ላይ ዓይናቸውን ካሳረፉት አገሮች መካከል ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ሳውዲት አረቢያና ኩዌይት ይገኙበታል።

እነዚሁ አገሮች የውስጥ ፍጆታቸውን ለመሸፈን በአፍሪቃ ምግብና የባዩ ነዳጅ ተክል የሚያመርቱበትን መሬት ይፈልጋሉ። ምያቱም እያደገ የሄደውን ብሄራዊ ፍላጎታቸውን በራሳቸው መሸፈን አይችሉም። በዚህ በጀርመን "ሃንደልስብላት" የተሰኘው የኤኮኖሚ ጋዜጣ በቅርቡ እንዳተተው የዓለም የእርሻ ድርጅት የ FAO ጠበብት ሂደቱን የሃብታም አገሮች የዕጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ እንዳይሆን ሲሉ ነው ያስጠነቀቁት። እርግጥም ተጎጂው አገሬው ሕዝብ እንዳይሆን በጣሙን የሚያሰጋ ነው። በአሕጽሮት FIAN በመባል የሚታወቀው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ባልደረባ ሶፊያ ሞንሣልቭ እንዳሉት አሁን በሚታየው ሂደት አርሶ አደሩ መሬቱን ያጣል፤ በዚሁም ራሱን የመቀለብ ዕድሉን ነው የሚነፈገው።

"የሚያሳዝን ሆኖ አዘውትረን የምንታዘበው የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶቹ መሬቱን የመጠቀሙን መብት በሚያገኙበት ጊዜ ወይም መሬቱን ሲገዙ በዚያ ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ያላንዳች ካሣና ሌላ ቦታ የመስፈር ዕድል በሃይል ሲፈናቀሉ ነው። ይህ ደግሞ የመኖርያና የምግብ ማግኘት መብትን እጅጉን የሚጥስ ሲሆን በዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ውል ረገድም የሰውልጆችን መብት የሚረግጥ ነው። በቀላሉ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም"

በችብቸባው ድርጊት የተሰማሩ አፍሪቃውያን መንግሥታት አንዳንዴ ተቃውሞን ለማርገበና ዕርምጃቸውን ለመደገፍ የምንሸጠው ወይም የምናከራየው አገሬው ለእርሻ የማይጠቀምበትን መሬት ነው ይላሉ። ይሁንና እነዚህም ጥቅም ላይ ያልዋሉ የሚባሉት መሬቶች በተለይ ለገጠሩ ድሃ ገበሬ እጅግ ጠቃሚዎች ናቸው። ለምሳሌ ለግጦሽ፤ ማገዶ፣ የመድሃኒት ተክልና ሌሎች የተፈጥሮ ምርቶችን ለመሰብሰብ ያስፈልጉታል። የታናናሾቹ ገበሬዎች መብት በዚህ መልክ መረገጡን ከቀጠለ ሶፊያ ሞንሣልቭና ሌሎች ጠበብትም የሚያስጠነቅቁት ጉዳዩ የሕብረተሰብ ዓመጽን ሊያፈነዳ እንደሚችል ነው።

"በቀላሉ ውሎቹ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደሚሰፍኑ በትክክል፤ በጥንቃቄ መመልከቱ ግድ ነው። ከእነዚሁ ድሆች አገሮች ብዙዎቹ ዓለምአቀፉን የሰብዓዊ መብት ከበሬታ ደምብ የተቀበሉ ዓባል ሃገራት መሆናቸውም ለኛ ጽናት አለው። እና ውሎች በሚፈረሙበት ጊዜ የአገሩ ሕዝብ ሰብዓዊ መብቶች ሊጠበቁ ይገባል"

በሌላ በኩል አንዳንድ መሠረታዊ ነገሮች ከተሟሉ የእርሻ መሬት ማከራየቱ ለአፍሪቃ አገሮች ጠቀሜታም ሊኖረው ይችላል የሚሉም ወገኖች አልታጡም። ከነዚሁ አንዱም የተባበሩት መንግሥታት የተፈጥሮ ጥበቃ ፕሮግራም UNEP የምግብ ነክ ጉዳይ ባለሙያ ክሪስቲያን ኔለማን ናቸው።

"ሌሎች አገሮች መሬቱን መከራየታቸው ይሄው በሚደረግባቸው አገሮች መዋዕለ-ነዋይን ሊያሳድግ ይችላል። ይህ ደግሞ የሥራ ቦታዎችን የሚፈጥር፣ የደሞዝ ዕድገትንና መሰል ሁኔታዎችን የሚያስከትል ነው። በአንጻሩም በተከራዮቹ ሃገራት የምግብ ዋስትናን የሚያጠናክር ነው የሚሆነው"

ኔለማን ለእርሻ ልማት የሚውል መሬትን እንደማንኛውም ምርት፤ እንጨት ወይም ነዳጅ ዘይት አድርገው ነው የሚመለከቱት። እርግጥ አያይዘው እንደሚያስገነዝቡት በአጠቃቀሙ ረገድ ጥሩ የሞራል መስፈርት መኖሩ ግድ ነው።

"ግልጽ በሆነ መንገድ የሚካሄድ ከሆነና በእርሻ ልማት ላይ መዋዕለ-ነዋይን በሥራ የማዋል ዕርምጃን ዋና ማተኮሪያው ካደረገ ይህ ጥሩ ነገር ነው። ግን የዋህ መሆን አያስፈልግም፤ ማለቴ የጉዳዩን ሁለት ገጽታ ለይቶ ማወቁ በጣም አስፈላጊ ነው። የሚያስከትለውን ጥቅም ብቻ ሣይሆን የሚመጣውን አደጋም ጭምር"

ጉዳዩ ናይጄሪያ በቅርቡ በሩዝ ተክል ረገድ ከታይላንድ ጋር ያደረገችው ውል ሁኔታ እንደሚጠቁመው አከራካሪ ነው። ታይላንድ የምዕራብ አፍሪቃይቱን አገር ደካማ የእርሻ ልማት ወደፊት ለማራመድ አንድ ሚሊያርድ ዶላር ገደማ የሚጠጋ መዋዕለ-ነዋይ በሥራ ላይ ለማዋል መፈለጓ ነው የሚነገረው። ግን ስምምነቱ የአገሪቱን ሩዝ አምራች ገበሬዎች ማሕበር ሊቀ-መንበር አቡባከር ዎሬን የመሳሰሉትን ብዙም አላስደሰተም።

እንደ ገበሬ በቂ የሙያ ሥልጠናም ሆነ የቴክኒኩ ዕውቀት የለንም። ገንዘብ የለንም፤ ሥልጣንም እንዲሁ! ስለዚህም ሁልጊዜ መንግሥት የሚያደርገውን ማየት ብቻ ነው የሚቀረን። ለነገሩ ችግሩን ለብቻችን ልንወጣው እንደምንችል እናውቃለን። ግን አሁን ሌሎች እንዲረዱን መጋበዛቸው እኛ ብቁ አይደለንም ማለት ነው"

አቡባከር ዎሬ እንደሚሉት መንግሥት ገንዘብ ለማቅረብ የገባውን ቃል እስካሁን ዕውን አላደረገም። እናም የመንግሥቱ ዕርዳታ ተጠቃሚዎች ታላላቅ ገበሬዎች ብቻ ሆነው ነው የሚገኙት። ይሁንና በሌላ በኩል የናይጄሪያ የእርሻ ሚኒስትር አባ-ሣያድ-ሩማ ትችቱን አይቀበሉትም።

"በዙ የገበሬ ማሕበራት ነው ያሉን፤ በተለይም የሩዝ ገበሬዎች! እንግዲህ በዕቅዱ አልተካተትንም የሚል ገበሬ ካለ ወይ ይህን አልተገነዘበም፤ አለበለዚያም ዘግይቶ ነው የመጣው። እኛ ግን ለገበሬዎቹ ገለጻ አድርገናል። መላውን የአገሪቱን የገበሬ ማሕበራት፣ የሁሉንም ፌደራል ክፍለ-ሐገራት የእርሻ ልማት ተወካዮች ጨምሮ ገበሬዎቹን ማገዝ በሚቻልበት መንገድ ተወያይተናል"

ያም ሆነ ይህ እየጨመረ ያለው በአፍሪቃ ለም መሬቶችን ለውጭ ባለሃብቶች የማከራየቱ ድርጊት በምን አቅጣጫ እንደሚራመድ ፍርድ ለመስጠት ጊዜው ገና ጨቅላ እንደሆነ የመስኩ ጠበብት የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል የእርሻው መሬት አጠቃቀም የተፈጥሮ እንክብካቤንና ማሕበራዊ መስፈርቶችን ሳይጠብቅ ከተካሄደ መሬቱ በቀድሞው የቅዥ ገዢዎች ዘይቤ መበዝበዙ የማይቀር ነው የሚሆነው። በአንጻሩ በአካባቢው ዕውቀትና መዋቅራዊው ይዞታ እንዲስፋፋ ቢደረግ አገሬው ሕዝብም የዕርምጃው ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል። እርግጥ የፋኦ ባልደረባ ፓውል ማቲዬ እንደሚያስገበዝቡት ውሎቹን በተመለከተ ሃላፊነቱ በመንግሥታቱ ትከሻ ላይ ብቻ ነው የሚያርፈው።

ዛሬ እየጨመረ የሚሄደው የሕዝብ ቁጥር፣ ተጽዕኖው መታየት የያዘው የአካባቢ አየር ለውጥና የምግብ እጥረት የምድራችንን ሕዝብ በሚገባ የመቀለቡን ጉዳይ ይበልጥ አስቸጋሪ እያደረገው ሲሄድ ነው የሚታየው። ከዚህ አንጻር በአፍሪቃ ለዚያውም ለሌሎች አገሮች የባዮ ኤነርጂ ፍጆት ሲባል ለም መሬት መባከኑ ለብርቱ ስጋት መንስዔ የሚሆን ነው። ለአፍሪቃ መንግሥታት በረጅም ጊዜ የሚበጀው ተገቢውን የመሬት ስሪት በማድረግ አምራቹን ገበሬ ማጠናከር፤ የራሱን መሬት አርሶ ከረሃብ ጥገኝነት እንዲላቀቅ ማድረጉ ነው የሚሆነው። በዓለምአቀፍ ደረጃም ችግሩን ለመወጣት የእርሻ ልማት ተሃድሶ ቢኖር ይመረጣል።

MM/AA/DW/DPA/RTRE/AFP