1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ፖለቲካ በጋዜጠኞቿ ዓይን

ዓርብ፣ ሰኔ 27 2006

ዶይቸ ቬለ በዚህ ሳምንት ያስተናገደው ሰባተኛው የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መድረክ ትናንት ተጠናቀቀ። በጉባዔው ከ100 ሀገራት በላይ የተውጣጡ ወደ 2,000 የሚጠጉ የመገናኛ ብዙኃን፣ የፖለቲካ እና የኤኮኖሚው

https://p.dw.com/p/1CVPZ

ዘርፍ ተወካዮችና ባለሙያዎች በተለያዩ አርዕስት ላይ ተወያይተዋል። እአአ በ2011 ዓም የሕዝብ ዓመፅ በአንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት ተቃውሞ ቀስቅሶ ነበር። ያ ተቃውሞ ዛሬ ከሦስት ዓመት በኋላ ምን ላይ እንደሚገኝ ጉባዔው መክሮበታል።

Symbolbild Arabischer Frühling
ምስል Mohammed Al-Shaikh/AFP/Getty Images

ትናንት በተጠናቀቀው በሦስት ቀኑ የመገናኛ ብዙኃን ጉባዔ የተሳተፉት ከአንጎላ፣ ቻድ፣ ዚምባብዌ እና ኢትዮጵያ የመጡት የድረ ገፀ አምደኞች እና የመብት ተሟጋቾችም « የተላለፈው ዓብዮት » በሚል ርዕስ ስር በአህጉሩ ስለሚታየው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በሰፊው ተወያይተዋል።

በዚያን ጊዜ በዐረብ ሀገራት የተካሄደውን የሕዝብ ዓመፅ አርአያ በማድረግ የሀገሪቱን መንግሥት የሰብዓዊ መብት እንደሚጥስ እና ሀሳብ የመግለጽ ነፃነትን እንደሚጨቁን በመውቀስ በአዲስ አበባ «በቃ » በሚል ስም አንድ እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር። የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ያኔ በግብፅ የተካሄደው ዓይነት ዓብዮት ኢትዮጵያ ውስጥ ሊካሄድ እንደማይችል ነበር የተናገሩት። በርግጥም ንቅናቄው ወዲያው ቆመ። እርግጥ፣ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ሲሞቱ ብዙዎች ሁኔታዎች ይለወጣሉ ብለው ተስፋ አድርገው ነበር። ግን የውይይቱ ተሳታፊ ጋዜጠኛ እሸቴ በቀለ እንዳለው፣ ያ የጠበቁት ለውጥ ሳይመጣ ነበር የቀረው።

« በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሙስና አለ። አስተዳደራዊ መዋቅሩ በችግሮች የተተበተበ ነው። ፍትሓዊ የሀብት እና የሥልጣን ክፍፍልም የለም። ችግሩ ብዙ ነው። »

ሌሎቹ ከከአንጎላ፣ ከቻድ እና ከዚምባብዌ የመጡት የውይይቱ ተሳታፊዎችም የያኔው ተቃውሞ ገና በእንጭጩ መደምሰሱን ነው ያመለከቱት። ለምሳሌ በአንጎላ የፀጥታ ኃይላት በፕሬዚደንት ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ አንፃር በተካሄደ ተቃውሞ ወቅት ሦስት ተሟጋቾችን መግደላቸውን ማካ አንጎላ የተባለውን ፀረ ሙስና ድረ ገፅ ያቋቋመው ራፋየል ማርኬስ ደ ሞራይስ አስታውሶዋል።

Robert Mugabe
ምስል picture-alliance/AP Photo

« የአምባገነኖች መረብ እርስ በርስ ይረዳዳል፣ አንዱ ካንዱ ሀሳብ ይወስዳል። በዚህም የተነሳ ነው አንጎላ ሙጋቤን ለመርዳት የሀገርዋን አልማዝ ወደ ዚምባብዌ የምትወስደው። »

ዚምባብዌን እአአ ከ1980 በጠቅላይ ሚንስትርነት እና በፕሬዚደንትነት የሚመሩት የ90 ዓመቱ ሮበርት ሙጋቤ መንግሥት ግዙፍ በየዕለቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈፅም፣ የተበላሸ የኤኮኖሚ አስተዳደር እንደሚከተል እና የተቃውሞ ቡድኖችን እንደሚጨቁን በ2003 ዓም « የዚምባብዌ ሴቶች ተነሱ » የሚል በሰላማዊ ዘዴ የሚታገል የሴቶች ንቅናቄ ያቋቋመችው እና ከ50 ጊዜ በላይ የታሰረችው ተሟጋቿ ጄኒ ዊልያምስ አስታውቃለች። እንድርሷ አስተያየት፣ በምርጫ የተገኘ ዴሞክራሲ የለም።

« ሰዎች በየመንገዱ የሚወጡበት ምክንያት ሊታወቅላቸው ይገባል። ምርጫ ዴሞክራሲ ስለማያመጣ ነው። ዚምባብዌ ነፃነቷን ስታገኝ የ18 ዓመት ወጣት ነበርኩ። እስካሁን በሀገሪቱ ዴሞክራሲ አይቼ አላውቅም፣ ብዙ ምርጫዎች ግን አይቻለሁ።

በቱኒዝያ፣በግብፅ እና በሊቢያ የተካሄዱት የሕዝብ ዓመፆች የመንግሥት ለውጥ አስገኝተዋል ። ይሁንና፣ በነዚህ ሀገራት ሀቀኛ ለውጥ ይመጣል በሚል ተፈጥሮ የነበረው የጋለ ስሜት በጠቅላላ ጠፍቶዋል።

Eric Topona
ምስል E. Topona

አፍሪቃ ውስጥ ፖለቲካ ላጭበርባሪዎች ነው የሚለው ማርኬስ ለውጥ ለማስገኘት ከተፈለገ ከሲቭሉ ማህበረሰብ የወጣ ጥሩ ሰዎች ሥልጣኑን መያዝ አለባቸው ይላል ፣ ጄኒ ግን የሲቭሉ ማህበረሰብ ተግባር መንግሥትን ኃላፊነቱን ማሳወቅ ነው ባይ ነች። ሌሎቹ ግን ለውጥ ያመጣሉ ብለው አያስቡም። አዲሶቹ መሪዎች ከሕዝቡ ይበልጥ በፀጥታ ኃይላቸው ነው የሚተማመኑት። ጄኒ እንደምትለው፣ በዚምባብዌ የሥልጣን ለውጥ ያልተደረገው በሰሜን አፍሪቃ የታየው ዓይነት ምስቅልቅል እንዳይደገም ነው ።

ለሕገ መንግሥቱ ስጋት ደቅኖዋል በሚል አምና ታስሮ የነበረው እና ዛሬ ለፈረንሳይኛ ክፍል የሚሰራው የቻድ ጋዜጠኛ ኤሪክ ቶፖና የጋዜጠኞች ስራ ስህተቶችን ማሳየት፣ ሙስናን ማጋለጥ፣ ድህነትንም በስሙ መጥራት መሆኑን አመልክቶዋል።

«ጋዜጠኛ ነኝ፣ እና ማንኛውም ጋዜጠኛ በትክክል የማይሰራ ነገር ሲያይ መተቸት አለበት፣ ፖለቲከኞች ማህበራዊ ፍትሕ እንዲኖር ባለመጣራቸው የቻድ ሕዝብ በጠቅላላ ሲራብ እያንዳንዱ ጋዜጠኛ ሂስ መሰንዘር ይኖርበታል። »

ፊሊፕ ዛንድነር

አርያም ተክሌ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ