1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቺዎች ህብረቱ ከአወቃቀሩ አንስቶ ወጣቶችን ችላ ይላሉ

ዓርብ፣ ጥር 26 2009

ሁሌም ጥር መገባደጃ ላይ አዲስ አበባ ትንፋሽ ያጥራታል፡፡ ዋና ዋና ጎዳናዎቿ ይዘጋጋሉ፡፡ፖሊሶች መንገድ ህንጻውን ይወራሉ፡፡ ነጭ ለባሾች ዓላፊ አግዳሚውን በዓይነ ቁራኛ ይከታተላሉ፡፡ የአፍሪካ ህብረት ዋና ጽህፈት ቤትን በጉያዋ እንደማቀፏ የማታስታጉለው ዓመታዊ ድግስ አለባት ነውና መዲናይቱ እንዲህ ጭንቅ ጥብብ ማለቷ፡፡

https://p.dw.com/p/2WwvY
Südafrika Proteste Studenten Universität
ምስል Getty Images/AFP/M. Safodien

የአፍሪካ ህብረት የወጣቶች ጉዳይ ግድ ይለዋልን?

ድግሱ ጉባኤ ነው፡፡ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችን በአንድ የሚያሰባስብ፡፡ አንዳንዶች “የአምባገነኖች ማህበር” ሲሉ ይወረፉታል፡፡የበርካታ ሀገራት መሪዎች በይስሙላ ምርጫ ስልጣን ላይ ለብዙ ዓመታት እንደሚቆዩ የሚታዘቡቱ ደግሞ ሌላ ስያሜ ይሰጡታል፡፡ ከመፈንቅለ መንግስት አሊያም ከድንገታዊ ህዝባዊ ዓመጽ ተርፈው ለጉባኤው ብቅ የሚሉ መሪዎች “እንኳን ለዚህ አበቃህ” የሚባባሉበት ነው ይሉታል፡፡ ያም ተባለ ይህ መሪዎቹ የየጊዜውን ጭብጥ እየመረጡ ለስብሰባ መቀመጣቸውን ቀጥለዋል፡፡ 

ዘወትር የሚስተዋለው ችግር ግን መሪዎቹ ለውይይት የመረጡትን አጀንዳ እንኳ በቅጡ ሳይወያዩ እና ውሳኔ ሳያሳልፉ በወቅታዊ ጉዳዩች ተጠምደው ጉባኤውን ማጠናቀቃቸው ነው፡፡ በዚህ ሳምንቱ ጉባኤ የሆነውም ተመሳሳዩ ነው፡፡ የጉባኤው ዋና ጭብጥ ”በአህጉሪቱ ካለው ህዝብ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የሚይዙትን ወጣቶች በመጠቀም ከብዛታቸው ማትረፍ” የሚል እንደሆነ አስቀድሞ ተገልጿል፡፡ ሆኖም በአዲስ አበባው ጉባኤ የታደሙ ርዕሳነ ብሔራት እና መራሕያነ-መንግስታት ከዚህ ይልቅ ሌሎች ጉዳዩች ትኩረታቸውን ተቆጣጥሮ እንደነበር በስብሰባው ተሳታፊ የነበሩት ዲዚሬ አሶባዲ ይናገራሉ፡፡    

“ያለፉት ጥቂት ጉባኤዎችን የተመለከትክ እንደሆነ ውይይቶቹ በዋናነት ያተኮሩት ስለ ሰላምና ጸጥታ፣ ለአፍሪካ ህብረት ስለሚደረግ የገንዘብ መዋጮ እና ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ነው፡፡ በቅርቡ በተጠናቀቀው ጉባኤ ደግሞ አፍሪካ ህብረትን እንደገና ስለማዋቀር፣ የሊቀመንበር ምርጫ እና ሞሮኮን እንደገና ወደ አፍሪካ ህብረት መቀላቀል ያሉ ተጨማሪ ጉዳዮች ለውይይት ቀርበዋል፡፡ በዋናው ርዕሰ ጉዳይ ላይ በፍጥነትም ቢሆን ተወያይተው ሁሉንም የሚገዛ ውሳኔ ቢያሳልፉ ኖሮ እመርጥ ነበር” ይላሉ ዲዜሬ፡፡ 

Gipfel Afrikanische Union Addis Abeba
ምስል dapd

በኦክስፋም ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ህብረት አገናኝ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዲዚሬ ውሳኔዎች ቢተላለፉም እንኳ የጉባኤው የተለመደ ችግር ካልተቀረፈ ውጤቱ መጥፎ ይሆናል ይላሉ፡፡ እንደእርሳቸው አባባል ብዙውን ጊዜ ውሳኔዎች የሚጸድቁት ተጨባጭ እና በጊዜ የተከፋፈለ የድርጊት መርሃ ግብር ሳይኖራቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ውሳኔዎችን ለመተግበር እንቅፋት ሲሆን ቆይቷል፡፡ 

በአፍሪካ ህብረት የወጣቶች ፕሮግራም ባለሙያ የሆነው ዳንኤል አዱኛ ጉባኤው ለዋናው ርዕሰ ጉዳይ በቂ ጊዜ አልሰጠም የሚለውን ትችት ይቀበላል፡፡ ሆኖም ጉባኤው ወጣቶችን ሙሉ ለሙሉ አላገለለም ባይ ነው፡፡ ተሰናባቿ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ በመጨረሻ ንግግራቸው የአፍሪካ ህብረት የወጣቶችን ጉዳይ የሚያቀነቅን እና ድጋፍ የሚያሰባስብ ልዩ የወጣቶች ልዑክ እንደሚመድብ ማሳወቃቸውን በምሳሌነት ይጠቅሳል፡፡ 

ለሀገራት መሪዎች በዙር የሚሰጠውን የአፍሪካ ህብረት የሊቀመንበርነት ቦታ የተረከቡት የጊኒው ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ ዓመቱ የወጣቶች መሆኑን ሲያውጁ ያስተዋወቁትን ፍኖተ ካርታም ያነሳል፡፡ ፍኖተ ካርታው ዋናውን ርዕሰ ጉዳይ አስመልክቶ ዓመቱን ሙሉ የሚደረጉ ክንዋኔዎችን የያዘ ነው፡፡ በስራ ዕድልና የስራ ፈጠራ፣ ትምህርትና ክህሎት ማዳበር፣ ጤናና ደህንነት እንደዚሁም ወጣቶች ስላላቸው መብቶችና እነርሱኑ በማብቃት ዙሪያ በአራት የትኩረት አቅጣጫዎች ተከፋፍሏል፡፡ ዳንኤል ማብራሪያ ያክልበታል፡፡  

“አሁን ይሄ 'Harnessing demographic dvidened to investment in youth' የአንድ ጊዜ የስብሰባው አርዕስት ብቻ አይደለም፡፡ የዓመቱ የ2017 ማለት ነው አርዕስት ነው፡፡ ሌሎቹ ጉዳዩች ስብሰባው እንዳበቃ መፍትሄም ካገኙ በዚያው ይቋጫሉ፤ መፍትሄም ካላገኙ ለሚቀጥለው ውሳኔ ይተላለፋል፡፡ ይሄ ግን ልክ በግብርናም ይሁን፣ ሴቶች ላይ ይሁን፣ ወጣቶች ላይ ሲመደብ ምንድነው ሀሳቡ የወጣቶችን ችግር በአንድ ስብሰባ ወይም በአንድ ዓመት ለመፍታት ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ ለዚህ ሀሳብ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ትኩረት መስጠት ነው” ሲል የስያሜውን ስብሰባ ተሻጋሪነት ያስረዳል፡፡

Dlamini-Zuma
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

የእዚህ ዓመት ዋና ርዕሰ ጉዳይ ወጣቶች ላይ እንዲያጠነጥን ያደረገው ሁለት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ተመርኮዞ እንደሆነ ዳንኤል ያስረዳል፡፡ የመጀመሪያው የአህጉሪቱ የስነ-ህዝብ አወቃቀር ነው፡፡ አፍሪካ  በወጣቶች የተሞላች ነች፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከአህጉሪቱ አጠቃላይ ህዝብ  65 በመቶ ያህሉ ዕድሜያቸዉ ከ35 ዓመት በታች ነው፡፡ እንደ አፍሪካ ህብረት ትንበያ በጎርጎሮሳዊው 2020 ከአራት የአህጉሪቱ ሰዎች መካከል ሶስቱ ዕድሜያቸው 20 ይሆናል፡፡ ይህን ወደ ስራ ኃይል ስንመነዝረው አፍሪካ በየዓመቱ ለስራ የሚደርሱ 10 ሚሊዮን ወጣቶች ይኖሯታል ማለት ነው፡፡   

በዚህ ዕውነታ ላይ የተመሰረተው ሁለተኛው ቁልፍ ጉዳይ “አፍሪካ ከዚህ የሰው ሀብቷ ልታተርፍ ይገባል” የሚል ትልም አለው፡፡ ለዳንኤል ትልቁ ጥያቄ “ይህን ብዛት ያለው ወጣት ኃይል ተጠቅሞ ለሀዝቦቿ የተሻለ ህይወት መስጠት የምትችል እና ራሷን የምትቀይር አፍሪካን መፍጠር እንችላለን ወይ?” የሚለው ነው፡፡ በአህጉሪቱ የወጣቶች ቁጥር መብዛት መንታ ውጤት እንደሚኖረው ዳንኤል ይገልጻል፡፡ እንደ አንድ ዕድል ተወስዶ ሊጠቅም እንደሚችል ሁሉ አፍሪካን ወደ ባሰ ችግር ሊከታት እንደሚችልም ያብራራል፡፡ 

“የአርዕስቱ ዋና አላማ በአንድ በኩል ይሄ ነገር ምንም ካልተደረገ ችግር እንደሆነ ሰውን እናሳውቅ [የሚል ነው]፡፡ መሪዎች፣ የውሳኔ ሰጪ አካላት፣ የግሉ ዘርፍ፣ ህብረተሰቡ፣ ሲቪል ማህብረሰቡን ጨምሮ ይህ ነገር ያገባዋል፡፡ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ስለዚህ አንደኛው ትኩረት ለመሳብ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ማወቁ ብቻ ሳይሆን እዚህ ላይ አስበንበት አቅደንበት ይሄንን ያለንን ሀብት ከግምት በመክተት የምንወስናቸው ውሳኔዎች ይህንን ያለንን ስነ-ህዝብ አወቃቀር ከግንዛቤ የከተተ ይሁን [የሚል ነው]፡፡ ዋናው ዓላማ ይሄ ነው” ሲል ዳንኤል ያብራራል፡፡  

የአፍሪካ ህብረት እንዲህ ዓመቱን ለወጣቶች ቢሰጥም ከአወቃቀሩ አንስቶ ችላ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው በሚል ይተቻል፡፡ ህብረቱ በስሩ ካቀፋቸው ስምንት ኮሚሽኖች መካከል በአንጻራዊነት ውጤታማ እየተባለ የሚወደሰው ግጭቶችን የመከላከል እና የመፍታት ሚና ያለው የሰላምና የጸጥታ ኮሚሽን ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ያሉት ኮሚሽኖች በአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ወቅት “እኛም አለን” ለማለት ከመውተርተር በዘለለ እምብዛም ተደማጭ አይደሉም፡፡ 

World Economic Forum in Ruanda
ምስል World Economic Forum /Benedikt von Loebell

ከስምንቱ ኮሚሽኖች፤ የወጣቶችን ጉዳይ እንዲያስተናብር ኃላፊነት የተጣለበት የሰዉ ሐይልን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በአንድ አጣምሮ የያዘው ኮሚሽን  ነው።  ህብረቱ እንደ ጎርጎሮሳዊው 2006 የአፍሪካ ወጣቶች ቻርተር የተሰኘ ፖለቲካዊ እና ህጋዊ አንድምታ ያለው  ሰነድ አጽድቋል፡፡ ሰነዱ በአህጉር፣ በቀጠና እና በሀገራት ደረጃ ወጣቶችን በተመለከተ ለሚተገብሩ ጉዳዮች አቅጣጫ እንዲሰጥ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ 

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እስከዚህ ዓመት የሚቆይ የሶስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ሲያዘጋጅም ለወጣቶች ጥቂት ገጾች መመደቡም አይዘነጋም፡፡ እንዲያም ሆኖ በተቺዎች ዘንድ የወጣቶች ነገር “ገና መቼ ተነካና?” የሚል ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡ በወጣቶች ጉዳይ ላይ የአፍሪካ ህብረት ዳተኛ እንደደነበር የሚስማሙት የኦክስፋሙ ዲዚሬ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን “ለውጦች መታየት ጀምረዋል” ይላሉ፡፡   

“በአፍሪካ ህብረት እንደሚሳተፍ እና እንደታዛቢ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለወጣቶች ጉዳይ ተጨማሪ ጉልበት ተመድቦ አይቻለሁ፡፡  ይህ የሆነው ደግሞ በማዳም ድላሚኒ ዙማ አስተዳደር ወቅት ነው፡፡ በእርሳቸው አመራር ወቅት ከታዩ አወንታዊ ነገሮች አንዱ የወጣቶችን እና የሴቶችን ጉዳይ እንደገና ወደ ጠረጴዛው ማምጣታቸው ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት እንዲህ አልነበረም፡፡ ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት ወጣቶችን ኢላማ ያደረጉ በርካታ እንቅስቃሴዎች እና ተነሳሽነቶች ተመልክቻለሁ፡፡ የወጣቶች ክፍሉም ይበልጥ መነቃቃት አሳይቷል” ሲሉ ለውጦች ያሏቸውን ይዘረዝራሉ፡፡ 

ዲዚሬ አጀንዳ 2063 ተብሎ የሚታወቀውና በሚቀጥሉት 50 ዓመታት በማህበራዊና ኢኮኖሚ ረገድ በአህጉሪቱ ታላቅ ለውጥ ለማስመዘገብ ርዕይ ያስቀመጠው የአፍሪካ ህብረት ዕቅድም ለወጣቶችና ሴቶች ተገቢውን ቦታ ሰጥቷል ብለው ያምናሉ፡፡ በአዲስ አበባው ጉባኤ ወቅት የአፍሪካ ህብረትን ለማሻሻል በሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ የቀረበው እቅድ እንኳ የወጣቶችን ጉዳይ ያካተተ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ የአፍሪካ ህብረቱ ዳንኤል ነገሮች እየተለወጡ ናቸው የሚለውን በተጨማሪ ምሳሌ ያስደግፋል፡፡ “በስራ ዕድል ደረጃ ራሱ በኮሚሽኑ ውስጥ ወጣቶች ተሳታፊ አልነበሩም፡፡ ምክንያቱም የዕድሜ ገደብ የነበረው ከ35 ዓመት በላይ ነበር፡፡ ብዙ የስራ ልምድ ስለሚጠየቅ፡፡  አሁን ግን በርካታ በተለይ በታችኛው መግቢያ ደረጃ ላይ ያሉ የስራ ደረጃዎች ለወጣቶች በጣም ተለቅቀዋል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ብናይ በአፍሪካ ህብረት የተቀጠሩ የወጣቶች ቁጥር ከ200 በላይ ነው፡፡ ያውም ይሄም የባለሙያ ደረጃ የምንላቸው የስራ ቦታዎችን ነው፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት 50 የማይሞሉ ነበሩ፡፡ ይሄ ለውጥ ትልቅ ነው ማለት ሳይሆን ካለው አጠቃላይ ሰራተኛ ድርሻ አንጻር ግን በጣም ትልቅ ለውጥ ነው እየመጣ ያለው” ይላል ዳንኤል ቁጥሮችን እያጣቀሰ፡፡ 

DW Sendung Africa on the Move
ምስል DW

ከአፍሪካ ህብረት ድረ-ገጽ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው የህብረቱ ኮሚሽን በአዲስ አበባ በሚገኘው ዋና መቀመጫው እና በቀጠናዎች ባሉ ቢሮዎቹ ወደ 1‚500 የሚጠጉ ሰራተኞች አሉት፡፡ የኦክስፋሙ ዲዚሬ የአፍሪካ ህብረት እንዲህ አይነት መሻሻሎች ቢያደርግም ችግሩ ያለው “ዋና እርግማኑ” ጋር ነው ባይ ናቸው፡፡ ህብረቱ ተራማጅ የሆኑ የፖሊሲ ማዕቀፎች እና ውሳኔዎች ማርቀቅ እና ማጽደቅ ላይ ብርቱ እንደሆነ ዲዚሬ ይናገራሉ፡፡ እርግማኑ፤- ፖሊሲዎቹ እና ውሳኔዎቹ ገና ከመፅደቃቸዉ መሞታቸዉ ነው፡፡  

 

ተስፋለም ወልደየስ 

ነጋሽ መሃመድ