1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ሃያ ሶስት የአፍሪቃ ሀገራት ስምምነቱን ፈርመዋል

ረቡዕ፣ ጥር 23 2010

በሳምንቱ መጀመሪያ በአዲስ አበባ ተካሄዶ በነበረው የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት ይፋ ተድርጓል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ 23 የአፍሪቃ ሀገራት የፈረሙት ይህ ስምምነት በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ተነግሮለታል፡፡

https://p.dw.com/p/2rrht
Boeing 737-800 Absturz Libanon Flash-Galerie
ምስል AP

ሃያ ሶስት የአፍሪቃ ሀገራት ስምምነቱን ፈርመዋል

በዓመት ሁለቴ የሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ብዙውን ጊዜ ዋና ትኩረቱን የሚሰጠው በአህጉሪቱ ለሚያጋጥሙ የጸጥታ እና የደህንነት ችግሮች ነው፡፡ አፍሪቃ እዚህም እዚያም የሚፈነዱ ግጭቶች እና ህዝባዊ ተቃውሞዎች በየጊዜው አያጧትምና ጉባኤውም ያንን ተከትሎ መላ ለማበጀት መታተሩ ብዙም አይደንቅም፡፡ ባለፈው እሁድ እና ሰኞ አዲስ አበባ ላይ የተካሄደው 30ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ግን ከተለመደው ለየት ባለ መልኩ ለኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ቦታ ሰጥቷል፡፡ የጉባኤው ዋና ጭብጥ የሆነው ሙስናን የመዋጋት አጀንዳ ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡ አንድ የአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት ይፋ የማድረጊያ ስነስርዓትም ሌላኛው የጉባኤው ቀልብ ሳቢ ሁነት ነበር፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ 23 ሀገራት ስምምነቱን መፈረማቸውን ተከትሎ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ መመስረቱን ይፋ ያደረጉት በዚህኛው ጉባኤ ላይ ተዘዋዋሪውን የህብረቱን ሊቀመንበርነት የተረከቡት የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ነበሩ፡፡ “ዛሬ አንድ የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያን ይፋ እናደርጋለን፡፡ ይህ ለማጓጓዣው ዘርፍ ትልቅ እርምጃ ነው፡፡ አህጉር አቀፍ ነጻ የንግድ ስፍራን ለማጽደቅ ተቃርበናል” ብለዋል ነበር ካጋሜ ለጉባኤው ባሰሙት ንግግር ፡፡

Gipfel Afrikanische Union in Addis Abeba
ምስል Imago/Xinhua

ካጋሜ የአየር ትራንስፖርት ገበያው ለ300 ሺህ አፍሪካውያን ቀጥታ የስራ ዕድል እና ለሚሊዮኖች ደግሞ በተዘዋዋሪ ዕድል እንደሚፈጥር በንግግራቸው ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሲቪል አቭዬሽን ባለስልጣን ዳይሬክተር ጄነራል ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛውም ከስምምነቱ ትሩፋቶች አንዱ የስራ ዕድል እንደሆነ ይስማማሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ ለሌሎች አፍሪካውያን የሚያስገኛቸውን ጠቀሜታዎችንም አንድ ሁለት እያሉ ይዘረዝራሉ፡፡

“አንዱ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱን በቀላሉ የማግኘት ዕድል ይኖራቸዋል፡፡ ሁለተኛ በህብረት በመስራታቸው በአፍሪካ ገበያ የአፍሪካ አየር መንገዶች የበለጠ ድርሻ እንዲኖራቸው፣ ገበያው በፈቀደ መጠን እና ገበያው ለሁሉም እኩል በሆነ ዕድል የሚሰራ በመሆኑ ለሁሉም፤ ለህዝቡም ለአየርመንገዱም፤ አገልግሎት ይኖረዋል፡ ለህብረተሰቡ አንደኛ በቀጥታ የአየር አገልግሎት በእነዚህ ሀገራት መካከል በቀላሉ ማግኘት ይችላል፡፡ ሁለተኛ ከበረራው የሚመነጩ ቀጥታ እና ቀጥታ ያልሆኑ የኢኮኖሚ ጥቅሞች ወይም የገቢ ጥቅሞችን ያስገኛል፡፡ ማንም አየር መንገድ ወደ አንድ ሀገር ሲበር እዚያ ሀገር ላይ የተለያዩ ስራዎች ስለሚሰሩ፣ የተለያዩ አገልግሎቶች ስለሚሰጡ በዚያ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍል ይኖራል” ይላሉ ኮሎኔል ወሰንየለህ፡፡  

የዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማህበር በጎርጎሮሳዊው 2015 ባወጣው መረጃ መሰረት በአፍሪካ ሀገራት መካከል ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት ላይ መደረሱ ከሚፈጥረው የስራ ዕድል ባሻገር በአህጉሪቱ ውስጥ በዓመት አምስት ሚሊዮን ተጨማሪ ተጓዦች የመብረር ዕድልን ይሰጣቸዋል፡፡ በስምምነቱ ምክንያት በሀገራት መካከል ያለው የአየር ትራንስፖርት ትስስር ማደግ እና የመጓጓዣ ወጪ መቀነስ ለዚህ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ አዲሱ ስምምነት ተግባራዊ ሲሆን የአየር ትራንስፖርት ዋጋን አሁን ካለው በ25 በመቶ እንዲቀንስ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት ኮሎኔል ወሰንየለህ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

አዲሱ ስምምነት ለአየር ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ጊዜያቸውን እንዲቆጥቡ ከማድረጉ በተጨማሪ በረጃጅም ጉዞ የሚያጋጥማቸውን እንግልት ያስቀርላቸዋል ተብሏል፡፡ አሁን ባለው አሰራር መሰረት የአንድ አገር አየር መንገድ ከሌላ ሀገር ተነስቶ ወደ ሶስተኛ ሀገር ቀጥታ በረራ ለማካሄድ ከዚያ ሀገር ጋር የተፈጸመ ስምምነት ግድ በማለቱ አየር መንገዶች ዙሪያ ጥምጥም እንዲጓዙ ይገደዱ ነበር፡፡ የአሁኑ ስምምነት ይሄን እክል እንደሚያስተካክል እምነት ተጥሎበታል፡፡ ኮሎኔል ወሰንየለህ ማብራሪያ አላቸው፡፡ 

Boeing 787 Ethiopian Airlines
ምስል Reuters

በአፍሪካ አንድ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ በአህጉር ደረጃ መመስረቱ ሁለት ሀገራት የሁለትዮሽ ስምምነት ሲፈጽሙ በአየር መንገዶች ላይ ሲቀመጥ የነበረውን ገደብም ያስቀራል፡፡  የስምምነቱ ሌላ ጠቀሜታ አፍሪካውያን አየር መንገዶች ከአህጉሪቱ ውጭ ባሉ ተመሳሳይ አገልግሎት ሰጪዎች የተወሰደባቸውን የገበያ ድርሻ የማስመለስ ዕድል መስጠቱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአህጉሪቱ ካለው የአየር ትራንስፖርት የገበያ ድርሻ ውስጥ 80 በመቶው የተያዘው የአፍሪካ ባልሆኑ አየር መንገዶች ነው፡፡ ኮሎኔል ወሰንየለህ ስምምነቱ በዚህ ረገድ የሚያመጣቸውን ለውጦች ይዘረዝራሉ፡፡

የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት እነዚህ ሁሉ ጠቀሜታዎች አሉት ቢባልም የተቃወሙት አፍሪቃውያን ግን አልጠፉም፡፡ መከራከሪያቸው ደግሞ ስምምነቱ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኬንያ ኤርዌይስ ፣ የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ያሉትን ትልልቅ ኩባንያዎች ይበልጥ ጡንቻቸውን የሚያፈረጥም እንጂ ሌሎቹን የሚያዳክም ነው የሚል ነው፡፡ በስምምነቱ አነስተኛ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ጨርሰው ይጠፋሉ ሲሉ የሚሞግቱም አሉ፡፡ ኮሎኔል ወሰንየለህ ይህን አስተያየት አይቀበሉትም፡፡

አንድ የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት በ30ኛው የአፍሪካ  ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ይፋ ይደረግ እንጂ ጥንሰሱ ረጅም ጊዜ ቆይቷል፡፡ የአሁኑ ስምምነት በጎርጎሮሳዊው 1999 የአፍሪካ መሪዎች ያማሳኩሩ ላይ ከተስማሙበት የሚመነጭ ነው፡፡ ይሄ እንደመነሻ ተወስዶ በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 2000 ዓ.ም የአፍሪካ መሪዎች ቶጎ ላይ ባካሄዱት ስብሰባ አንድ የአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ እንዲኖር ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት ደግሞ ገበያው እንዲጀምር ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 ሀገራት እሺታቸውን በፊርማቸው ገልጸው ነበር፡፡

የአፍሪካ ህብረት የ2063 ርዕይ አካል የሆነው ይህ የትራንስፖርት ገበያ ተግባራዊ ለመሆን ገና መሰራት ያለባቸው ነገሮች ይቀሩታል፡፡ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አብዲሳ ያደታ ከዚህ በኋላ በየሀገራቱ መከናወን የሚገባቸውን ጉዳዩች ያስረዳሉ፡፡

የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ። 

ተስፋለም ወልደየስ

ሂሩት መለሰ