1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪካ የህክምና ባለሙያዎች ፍልሰት

ዓርብ፣ ሐምሌ 9 1996

በአፍሪካ የኤች አይ ቪ ኤይድስ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ባለበት በአሁኑ ወቅት የሰለጠኑ የህክምና ባለሙያዎች ሃገራቸውን እየለቀቁ ወደ በለፀጉት ሃገራት መሄዳቸው አግባብ አለመሆኑ ተገለፀ ። የችግሩን አሳሳቢነት የገለፀው እና ለሰብአዊ መብት መከበር የቆመ የህክምና ባለሙያዎች ድርጅት ትናንት ባወጣው መግለጫ የሰለጠኑ የህክምና ባለሙያዎች ፍልሰትን ለመግታት ያስችላሉ ያላቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች አቅርቧል ።

https://p.dw.com/p/E0fU

እንደ ዓለም የጤና ድርጅት ቢሆን ይመረጣል ግምት ለአንድ መቶ ሺ ሰዎች ሃያ የህክምና ዶክተሮች ያስፈልጋሉ ። ከሰሃራ በታች ካሉ አርባ ስምንት ሃገራት ውስጥ አስራ ሶስቱ ያላቸው የህክምና ባለሙያ ግን ለመቶ ሺ አምስት እና ከአምስት በታች ነው ። አስራ ሰባት የአፍሪካ ሃገራትም የዓለም የጤና ድርጅት ካወጣው ግምት ባነሰ የነርሶች እጥረት አጋጥሟቸዋል ። እንደ ድርጅቱ ግምት ለመቶ ሺ ሰዎች ቢያንስ አንድ መቶ ነርሶች ያስፈልጉ ነበር ። የሚታየው ግን ከዚህ በግማሽ ባነሰ ነው ። ይህም በዛ ተብሎ የሰለጠኑ የአፍሪካ የህክምና ዶክተሮች ሃገራቸውን እየለቀቁ ወደ በለፀገው ሃገር ይሰደዳሉ ። ነርሶችም ቢሆኑ እንዲሁ ሃገር ለቀው በመውጣት በበለፀገው ዓለም ሥራ የማያጡበት የሙያ መስክ አድርገውታል ።

‘’ የሰለጠኑ የህክምና ባለሙያዎችን ፍልሰት ለመከላከል የተነደፈ የድርጊት መርሃ ግብር ‘’ የሚል ርዕስ ይዞ የወጣው የሰብአዊ መብት ድርጅት እንዳለው ባለሙያዎቹ ሃገራቸውን ለቀው ወደ ሃብታም ሃገራት የሚሰደዱት በአብዛኛው የተሻለ ክፍያ ፍለጋ ነው ። የተቀሩት ደግሞ በየሃገሮቻቸው ያለው የህክምና አገልግሎት መስጫ ቁሳቁስ እና ሥፍራ አለመሟላት የሚፈጥርባቸው ጭንቀት ለመሰደዳቸው ምክንያት ሆኗል ። ድርጅቱ የህክምና ባለሙያዎች ፍልሰት የከፋ መሆኑን ለማሳየት ቦትስዋናን እንደ ምሳሌ ጠቅሷታል ። ቦትስዋና ከእ.አ.አ 1978 እስከ 1999 በነበሩት ሃያ አንድ ዓመታት ውስጥ ካሰለጠነቻቸው ስድስት መቶ የህክምና ዶክተሮች ውስጥ በሃገር የቀሩት ሃምሳ ብቻ ናቸው ።

ኤች አይቪ ኤይድስ የአፍሪካ ተቀዳሚ ችግር በሆነበት በአሁኑ ወቅት የህክምና ባለሙያዎች ሃገራቸውን ጥለው መውጣታቸው ደግሞ ችግሩን አባብሶታል ። በቫይረሱ ክፉኛ በተጠቁት ደቡብ አፍሪካ እና ቦትስዋና በሽታውን ለመከላከል በቂ ገንዘብ ቢመደብም በህክምና ባለሙያዎች እጥረት የተፈለገውን ሥራ ማከናወን አልተቻለም ። በርግጥ የህክምና ባለሙያዎች እራሳቸውን የሚከላከሉባቸው መሳሪያዎች በቂ ያለመሆን የሚያሳስባቸው ሲሆን በዚሁ ምክንያት በበሽታው የተያዙ እና የመያዝ ዕድላቸው ሰፊ ነው ። በከተሞች እና በገጠሮች መካከል ያለው የመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት አለመመጣጠን እና የሃብት ክፍፍል እኩል አለመሆን ለችግሩ መባባስ እንደ ምክንያት ይጠቀሳል ። ይህ ችግር ያሳሰበው የሃኪሞቹ የሰብአዊ መብት ድርጅት መፍትሄ ያላቸውን አማራጭ ሃሳቦች በዝርዝር አስቀምጧል ።

የመጀመሪያው የአፍሪካ መንግስታት የህክምና ባለሙያዎቻቸው እራሳቸውን ከተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች የሚከላከሉባቸው እንደ ግላቭስ እና ሲርንጂ የመሳሰሉ የህክምና ቁሳቁሶችን በበቂ እንደሚያቀርብሏቸው የሚል ነው ። ለዚህ ኃላፊነት መሟላት የውጭ የረድኤት ድርጅቶች እገዛ እንዲያደርጉ ተጠቁሟል ። የጤና የትምህርት ተቋማት የሚያሰጥኗቸው ተማሪዎች በአብዛኛው ከገጠሩ ክፍል ቢሆኑ እና ከተመረቁ በኃላ ተመልሰው ወገናቸውን እንዲያገለግሉ የሚያስችልም የዜግነት ትምህርት ቢሰጣቸው የሚለው ሌላው የመፍትሄ ሃሳብ ነው ። እስካሁን ብዙም ትኩረት የማይሰጠው እና የአፍሪካ መንግስታት እና የህክምና ዶክተሮች ቢፈጽሙት የተባለው ሃሳብ ነርሶች እና ሌሎች የጤና ረዳቶች ሃኪሞችን ተክተው መስራት የሚያስችል የህክምና ስልጠና የሚያገኙበት መንገድ ቢበረታታ ይላል ። የበለፀጉት ሃገራት የህክምና ተቋማት የህክምና አሰልጣኞችን በመልማት ላይ ወደአሉ ሃገሮች ልከው ቢያሰሩ የሚለውም ሌላ ተመራጭ ሃሳብ ነው ። በተለይ እነዚህ ባለሙያዎች በአፍሪቃ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል የሚያጠናክሩ እና የአቅም ግንባታ ስልጠና የሚሰጡ ሊሆን ይገባል ።

ሌላኛው ሃሳብ ምን ያህል ተቀባይነት ያገኛል የሚል ጥያቄ ያስነሳል እንጂ እንደ መፍትሄ ጥሩ ተብሎ ተወድሷል ። የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ያቀረበው ይኼው መፍትሄ የሰለጠኑ የአፍሪካ የህክምና ባለሙያዎችን የሚወስዱ የበለፀጉት ሃገራት የሰለጠኑ ዜጎቻቸው ለተወሰዱባቸው ሃገራት ካሳ እንዲከፍሉ የሚል ነው ። ለዓለም የገንዘብ ድርጅት ‘’ ለአይ ኤም ኤፍም ‘’ የተሰጠ ማሳሰቢያ አለ ። የገንዘብ አበዳሪው ድርጅት አይ ኤም ኤፍ ተበዳሪ የአፍሪካ ሃገራት ከሚያገኙት ገንዘብ ይበልጡን ለጤና አገልግሎት እንዲያውሉ ግዴታ እንዲጥልባቸው ተጠይቋል ። ሁሉም አማራጭ ሃሳቦች በወረቀት ያምራሉ ። በተግባር ግን እንዴት እና መቼ የሚለው ጥያቄ ፤ ጥያቄ እንደሆነ ይዘልቃል ።