1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ

ሰኞ፣ ጥቅምት 15 2003

አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ነበሩ። ዘንድሮ እነዚህ ሀገራት የነጻነት ቀናቸውን ያከብራሉ። በእርግጥ ከቅኝ ግዛት ከተላቀቁ ሃምሳ ዓመት ሞላቸው። እነደሰው ሰብዓዊ ክብር ያላገኙት፤ መሰረታዊ የሰው ልጅ መብቶች የተነፈጉዋቸው አፍሪካውያን ያ ዘመን የጨለማ ይሆንባቸዋል።

https://p.dw.com/p/PnhV
ምስል AP

ከሀምሳ ዓመት በኋላም በጨለማው ዘመን የነበረው ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት አፍሪካውያንን መፈናፈኛ ሲያሳጣ ግን የነጻነት ትርጉም በእርግጥ ከወረቀት ያለፈ፤ አዲስ ያውም የራስ ጉልበተኛ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ የሚያስብል ይሆናል። ሰላም ጤና ይስጥል? አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ቀኗን ባለፈው ሀሙስ አከበረች። የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከሚከሰትባቸው የዓለማችን ክፍሎች አፍሪካን የሚቀድማት አልተገኘም። ግን እንደ ቀን አሰበችው-ሀሙስ። የእለቱ ማህደረ ዜና የአፍሪካን የሰብዓዊ መብት ይዞታን ይቃኛል። አብራችሁን ቆዩ።

--------------------------------------------

አኤአ 1960። አፍሪካ አባዛኛው ክፍሎቿ ከቅኝ ገዢዎች አጅ የወጡበት ዘመን። ሃምሳ ዓመት ሞላው። ዘንድሮ የግማሽ ክፍለ ዘመን ጉዞ ሲቃኝ እንደ መላኪያዎቹ የሚለያይ፤ እንደ አነጻጻሪው የተለያየ የሚመስል አይነት ነገር ነው። አፍሪካ በኢኮኖሚው፤ በፖለቲካው፤ በማህበራዊው የደረሰችበት ላይ ቆም ብሎ የ50 ዓመቱን ጉዞ ለቃኘ በእርግጥ የሚያገኘው ምስል ሊለያይ ይችላል። ከሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አንጻር ግን አፍሪካ ከቀድሞዋ የተሻለች ለመሆኗ አስረጂው ብዙም ጉልበት ያለው አይመስልም።ዓለም ዓቆፉ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች የለንደን ዳይሬክተር ቶም ፖርቴውስ በቅኝ ግዛት ዘመን የነበረውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ከአሁኑ ጋር ማነጻጸር ይከብዳል ይላሉ።

ድምጽ

የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ከቅኝ ግዛት ዘመኑ ማነጻጸር እንደባለሙያው በእርግጥ ከበድ ያለ ነው። አንዳንዶች አፍሪካውያን በራሳቸው በአፍሪካውያን መመራት ከጀመሩ በኋላ የሰብዓዊ መብቱ ጥሰት የከፋባቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ባለፈው ሳምንት የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ቀን አዲስ አበባ ላይ ሲከበር በአፍሪካ ህብረት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር አልፒኒ ጋንሱዋ ያሉት በእርግጥ አፍሪካ ከሰብዓዊ መብት አንጻር ገና ብዙ ይቀራታል።

ድምጽ

የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ቀን መከበር የጀመረው እኤአ ከ1986 ጀምሮ ነው። በየዓመቱ ኦክቶበር 21 እየተከበረም ላለፉት 26 ዓመታት ዘልቋል። ዘንድሮ የሰብዓዊ መብትን ማወቅ ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላም መምጣት ቁልፍ ጉዳይ ነው በሚል መሪ ቃል የተከበረው የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ቀን የአህጉሪቱ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ የት እንደደረሰ በግልጽም ባይሆን በጨረፍታ አሳይቷል። የአፍሪካ ህብረት ዋና ጸሀፊ ዣን ፒንግ እያሽቆለቆለ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። በአፍሪካ ዓይነቱ የተለያየ ውጤቱ ግን ተመሳሳይ የሆነ የመብት ጥሰት በአራቱም አቅጣጫዎች ቀጥለዋል። በየዓመቱ የየሀገራቱን የሰብዓዊ መብቶች ይዞታን ሮፖርት የሚያወጣው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች፤ በተለይ የእርስ በእርስ ጦርነት የሰብዓዊ መብቱን ሁኔታ የከፋ እንዲሆን እንዳደረገው አስታውቋል። በድርጅቱ የለንደን ዳይሬክተር ቶም ፖርቴዎስ እንደሚሉት በአፍሪካ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከቦታ ቦታ ይለያያል።

ድምጽ

የአፍሪካ ህብረት በኮሚሽን ደረጃ ያቋቋመው የሰብዓዊ መብት ክፍል ከስብሰባ ግርግር፤ ከተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች ያለፈ ጠብ የሚል ነገር ለመስራቱ ያሳየው ውጤት በእርግጥ ልብ የሚደርስ ለመሆኑ አጠራጣሪ ነው። በአፍሪካ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ በተመለከተ የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት በተለይ በምስራቃዊ ኮንጎ፤ በኡጋንዳና በዳርፉር ሱዳን የመብት ጥሰቱ የከፋ እንደሆነ ያሳያል።

ድምጽ

በአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን በተመለከተ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች መስሪያ ቤት በቅርቡ ጄኔቭ ላይ ይፋ ያደረገው ሪፖርት አስደንጋጭ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ የሰብዓዊ መብቱ ሁኔታ ለመሻሻሉ ዋስትና እንደሌለ ያሳያል ተብሏል። ሩዋንዳንና ኡጋንዳን ጨምሮ 6 ሀገራት የተከሰሱበት ምናልባት እስከ ዘር ማጥፋት ሊደርስ በሚችል ሰብዓዊ ጥፋት እንደተሰማሩ በተጋለጠበት ሪፖርት አፍሪካ በገዛ ልጆቿ የሚደርስባት ግፍ የሚልቅ የሚዘገንን መሆኑን ያሳያል። የዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ቃል አቀባይ ሪድ ብሮዲ የተፈጸመው ከባድ ወንጀል ነው ይላሉ

ድምጽ

የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት የለነደን ቢሮ ዳይሬክተር ቶም ፓርቴውስ በሌላው የአፍሪካ ክፍል ሌላ ገጽታ ያለውን የመብት ጥሰት በማሳየት ይቀጥላሉ። ኢትዮዽያ በእርግጥ ከሚጥሱት አንዷ ሆናለች።

ድምጽ

የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ብዙዎችን እያሰጋ እንዳለ ሁሉ የሚወቀሱት ሀገራት በድርሻቸው የፈጠራ ድርሰት ከማለት እስከ ማውገዝ በደረሰ ተቃውሞ ሪፖርቶችን ማጣጣላቸው የተለመደ፤ ሪፖርቱን ተከትሎ የሚሰማ ውግዘት ሆኗል። በቅርቡ ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች፤ የኢትዮዽያው ገዢ ፓርቲ የእርዳታ ገንዘብን ህዝቡንና ተቃዋሚዎችን ለማፈን እንደሚጠቀም ሲገልጽ ከአዲስ አበባ የተሰማው ተቃውሞ ጠንካራ ነበር። የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች መስሪያ ቤት በተለይ ሩዋንዳን በከሰሰ ጊዜ ኪጋሊ ያለችው ቢኖር ልብ ወለድ ወሬ የሚል ነበር። የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሉዊስ ሙሺኪዋቦ እንዳሉት ይህን መሰለሉ ሪፖርት የሚወጣበት ምክንያት ግልጽ ነው።

ድምጽ

በእርግጥ የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ይዞታ በተወሰነ ደረጃ መሻሻል እንደሚታይበት የሚናገሩት የሚወቅሱትም ናቸው። የለንደን የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ቤሮ ዳይሬክተር ቶም ፖርቴውስ ላይቤሪያና ሴራሊዎን አንጻራዊ በሆነ መልኩ መሻሻል አሳይተዋል ይላሉ።

ድምጽ

የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ጽህፈት ቤት ባንጁል ጋምቢያ ይገኛል። በአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ይዞታ እንዲሻሻል እየሰራ እንደሆነ ይገልጻል።

ድምጽ

የአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አብዛኞች የአፍሪካ ሀገራት 50ኛ ዓመት የነፃነት በዓላቸው በሚያከብሩበት በዚህ ዓመት በተለየ ስሜትና መንፈስ እንደሚታይ የገለጹት ---------የሰለጠኑት ሀገራትም ከደሙ ንጹ አይደሉም ሲሉ ይገልጻሉ።

ድምጽ

በእርግጥ አሁንም ለአፍሪካ ግጭትና የመልካም አስተዳደር እጦት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲኖሩ አድርገዋል። አሁንም ሴቶችና ህጻናት የሰብዓዊ መብት ጠሰቱ ዋንኛ ሰለባዎች መሆናቸው አልቆመም። የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት የእንግሊዝ ቢሮ ዳይሬክተት ቶም ፖርቴውስግጭቶች የቆሙ ቀን የሰብዓዊ መብት ጥሰቱም ይቆማል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።

ድምጽ

ድይሬክተር ቶም ሩዋንዳና ኢትዮዽያን በተለይ አንስተው ለውጥ እንዲያሳዩ የምጠብቃቸው ሀገራት ይሏቸዋል።

ድምጽ

የአፍሪካ የሀምሳ ዓመት የነጻነት ዘመን በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደታጀበ ዘልቋል። ለመጪው እኛም እንደ ዳይሬክተት ቶም ተስፋ ,አድረገን የዕለቱን ማህደረ ዜና አበቃን። መሳይ መኮንን ነበርኩ። ጤና ይስጥልኝ

መሳይ መኮንን

አርያም ተክሌ