1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍቃኒስታን ምርጫ ዉጤትና ዉዝግቡ

ሐሙስ፣ ጳጉሜን 5 2001

ይሕ የቅሬታ ሰሚ ኮሚሽኑ የአደባባይ መግለጫ «ገለልተኛ» የሚባለዉ የምርጫ ኮሚሽን ካወጀዉ ዉጤት ጋር የሚቃረን ነዉ።አስመራጭ ኮሚሽኑ ቅሬታዉን የተቀበለዉ አይመስልም

https://p.dw.com/p/JcOa
ድምፅ ቆጠራዉምስል AP

100909

የአፍቃኒስታን ሕዝብ የወደፊት መሪዉን ለመምረት ድምፁን ከሰጠ ዛሬ ሰወስተኛ ሳምንቱን ደፈነ።እስካሁን ይፋ በሆነዉ ዉጤት መሠረት በሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳት ሐሚድ ካርዛይ አሸናፊ ናቸዉ።ይሁንና የምርጫዉ ሒደት ተጨብርብሯል የሚለዉ ወቀሳ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል።ዋነኛዉ የካርዛይ ተቀናቃኝ ዉጤቱን «ሕገ ወጥ» ሲሉት፥ የምርጫዉ ቅሬታ ሰሚ ኮሚሽን በበኩሉ በተወሰኑ አካባቢዎች የተሰጠዉ ድምፅ እንዲጣራ ጠይቋል።Kai Küstner የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

የአስመራጭ ኮሚሽኑ የበላይ ሐላፊ መግለጫ።ማክሰኞ-ማታ።ለፕሬዝዳት ሐሚድ ካርዛይ አሰደሳች ቃላት ነበሩ።በኮሚሽኑ መግለጫ መሠረት ካጠቃላዩ ድምፅ ዘጠና-አንድ ከመቶዉ ተቆጥሯል።ካርዛይ ከሐምሳ-አራት ከመቶ የሚበልጠዉን አግኝተዋል።ዉጤቱ በተሰማ በማግስቱ ትናንት ካርዛይ የምርጫዉን-ሒደትና ዉጤት አድንቀዉ፥ ምርጫ አስፈፃሚ፥ መራጮችን አመስግነዋል።

የካርዛይ አድናቆት ምሥጋና የተሰማዉ የምርጫዉ መዛባቱ፥መራጩ ድምፅ መጭበርበሩ ደምቆ፥ ተደጋግሞ በሚነገርበት ወቅት ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደግፈዉ የቅሬታ ሰሚ ኮሚሽን በስድስት መቶ ጣቢያዎች የተሰጠዉ ድምፅ በድጋሚ እንዲቆጠር ወስኗል።ECC በሚል የእንግሊዝኛ ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የኮሚሽን ሐላፊ ግራንት ኪፐን እንደሚሉት መስሪያ ቤታቸዉ ከዚሕ ዉሳኔ የደረሰዉ ድምፁ ለመጭበርበሩ በቂ መረጃ በማግኘቱ ነዉ።

«ከደረስንበት ዉሳኔ የደረስነዉ፥-ባደረግነዉ ምርመራ በድምፅ መስጪያ ጣቢያዎችና በድምፅ መስጪያ ሳጥኖች መዛባቶች መኖራቸዉን በግልፅ በሚያሳዩ መረጃዎች ላይ ተመስርተን ነዉ።»

ይሕ የቅሬታ ሰሚ ኮሚሽኑ የአደባባይ መግለጫ «ገለልተኛ» የሚባለዉ የምርጫ ኮሚሽን ካወጀዉ ዉጤት ጋር የሚቃረን ነዉ።አስመራጭ ኮሚሽኑ ቅሬታዉን የተቀበለዉ አይመስልም።እንዲያዉም የአስመራጭ ኮሚሽኑ የበላይ አብዱል አሊ ነጃፊ እንዳሉት የቅሬታ ሰሚ ኮሚሽኑ ለመስሪያ ቤታቸዉ ያቀረበዉ ስሞታ እርስ በርሱ የሚቃረን ፍቺ ያለዉ ነዉ።

«የዳሪዉና የፓሽቱኑ ቋንቋዎች ፍቺ ከእንግሊዝኛ ትርጉሙ ጋር ሲነፃፀር ግልፅ አልነበረም።ለዚሕም ነዉ ECC ማብራሪያ እንዲሰጠን ከሸኚ ደብዳቤ ጋር አያይዘን መልሰን የላክነዉ።»

ኮሚሽነር ነጃፊ እንደሚሉት ቆጠራዉ ከተጠናቀቀ በሕዋላ የሚቀርበዉ ቅሬታ ይመረመራል።ይሕ ማለት እስካሁን ያልተቆጠረዉም ድምፅ ተቆጥሮ አጠቃላይ ዉጤቱ ከታወጀ በሕዋላ ተጭበረበረ የተባለዉ ድምፅ ይመረመራል።ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠለትን ድምፅ ከቆጠሩ በሕዋላ ወደ ማጣራቱ የሚኬድበት መንገድ በርግጥ ግልፅ አይደለም።በአፍቃኒስታን የቀድሞዉ የአዉሮጳ ሕብረት መልዕከተኛ ፍራንቼስኮ ቬንድሬል እንደሚሉት በምርጫዉ የደረሰዉን ጥፋት መጠገን መቻሉ አጠራጣሪ ነዉ።

«በርግጥ የቅሬታ ሰሚ ኮሚሽኑ የሚይዘዉን አቋም በግልፅ እስኪያስታዉቅ ድረስ መጠበቅ አለብን።በእኔ እምነት ግን ሒደቱ ታማኝነት የለዉም።እነዚሕ ምርጫዎች አሁን ባሉበት ሁኔታ ሕጋዊ መንግሥት ሊመሰረትባቸዉ አይቻልም።»

በ28.3 ከመቶ ድምፅ የሁለተኝነቱን ሥፍራ የያዙት የካርዛይ ዋነኛ ተፎካካሪ አብዱላሕ አብዱላሕ የድምፅ አሰጣጡ መጭበርበሩን ያልተናገሩበት ጊዜ የለም።አስመራጭ ኮሚሽኑን ገለልተኝነት እንደሚጠራጠሩም በተደጋጋሚ አስታዉቀዋል። በዚሕም ምክንያት ኮሚሽኑ የቀረቡት የቅሬታ አቤቱታዎች ለማታራት መፍቀዱን ይጠራጠራሉ።

Kai Küstner/Negash Mohammed

Hirut Melesse