1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍቃኒስታን ፀጥታና የአሜሪካ መራሹ ጦር የመዉጣት ዕቅድ

ሰኞ፣ ሰኔ 20 2003

የጀርመን መከላከያ ሚንስትር ቶማስ ደ ሚዜየር ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ነገሩ አብረን እንዘምታለን አብረን እንመለሳለን አይነት ነዉ

https://p.dw.com/p/RW60
የአፍቃኒስታንና የአሜሪካ አንድነት አርማምስል DW

27 06 11


«አፍቃኒስታን ዉስጥ በታሊባን ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሰንበታል።ይቆጣጠራቸዉ የነበሩ በርካታ አካባቢዎችንም ማርከንበታል።ሐይላችንን ስናጠናክር የተባባሪዎቻችን ቁርጠኝነትም አድጓል።ይሕ አብዛኛዉ የሐገሪቱን ግዛት ለማረጋጋት ረድቷል።»

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ።ሮብ ማታ።በሣልስቱ አርብ ሰሜን ባዛአር ተሸበረች። አምስት ሠላማዊ ሰዎችና አንድ ፖሊስ ተገደሉ።ቅዳሜ ደቡብ አፍቃኒስታንን ሎጋር ወረዳን ያሸበረ ቦምብ አርባ ያሕል ሰላማዊ ሰዎችን ፈጀ።ሐምሳ አቆሰለ።ዛሬ ቃራባግሕ ወረዳ መንገድ ላይ የተቀበረ ቦምብ ፈነዳ።ሰባት ሰዉ ገደለ።በርግጥ ኦባማ እንዳሉት አፍቃኒስታን ተረጋግታለች? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ሮብ ያሉትን ቅዳሜም ደግመዉታል። አፍቃኒስታን የዘመተዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ተልዕኮዉን በድል እየተወጣ ነዉ።እና ወደ ሐገሩ ይመለሳል።

«ለፅኑ ሴትና ወንድ መለዮ ለባሾቻችን፥ ለሲብል ሠራተኞቻችን እና ለበርካታ ተባባሪዎቻችን ምስግና ይግባቸዉና አላማችን ግቡን እየመታ ነዉ።በዚሕም ምክንያት ከሚቀጥለዉ ወር ጀምሮ-እስከ ዓመቱ ማብቂያ ድረስ አስር ሺሕ ወታደሮችን ከአፍቃኒስታን ማዉጣት እንችላለን።በተጨማሪም እስከ መጪዉ በጋ ድረስ 33,000ወታደሮችን ወደ ሐገራቸዉ እንመልሳለን።ይሕ ከዚሕ ቀደም ዌስት ፖይንት ላይ ባወጅኩት መሠረት የዘመተዉን ጦር ቁጥር የሚያክል ነዉ።»

በአዋጁ መሠረት የዩናይትድ ስቴትስ ጦር እስከ ሁለት ሺሕ አስራ-አራት(ዘመኑ በሙሉ እጎአ ነዉ) ድረስ አፍቃኒስታንን ሙሉ በሙሉ ለቅቆ ይወጣል።በአሜሪካ ጦር ዉጊያ፥ በአሜሪካ መሪዎች ፍቃድና ድጋፍ የካቡልን ቤተ-መንግሥት የዛሬ አስር-አመት ግድም ከአሜሪካ ጦር አዛዦች የተረከቡት ፕሬዝዳት ሐሚድ ካርዛይ ኦባማን አበጀሕ የማይሉበት ብቃት ድፍረትም ሊኖራቸዉ አይችሉም።

Obama Soldaten Abzug aus Afghanistan
የአሜሪካ ወታደሮችምስል picture alliance/dpa

«ፕሬዝዳንት ኦባማ ትናንት ማታ ያወጁትን የአፍቃኒስታን ሕዝብ በደስታ ተቀብሎታል።አሁንና በሚቀጥለዉ አመት ሊቀነስ የታቀደዉ ጦር ቁጥር፥ አፍቃኒስታን ፀጥታዋን የማስከበሩን ሐላፊነት ራስዋ እየተረከበች እና በራሷ አቅም የግዛቷን ደሕንነት ለማስጠበቅ እየሞከረች ለመሆኑ ምልክት ነዉ።ሥለ በአዋጁ ተደስተናል።»

ፕሬዝዳንት ካርዛይ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ከአፍቃኒስታን እንዲወጣ መታወጁን የአፍቃኒስታን ሕዝብ ይደግፈዋል ማለታቸዉን እንጂ ሕዝቡ የሚደግፍበትን ምክንያት፥ የደገፈበትን ሁኔታ በርግጥ አልተነገሩም።ፕሬዝዳት ኦባማ ሮብ ማታ ተናግረዉ እስከ ሐሙስ ጠዋት በነበረዉ አንድ ሌሊት ፕሬዝዳት ካርዛይ የሕዝባቸዉን ድጋፍና ተቃዉሞ ያሰባሰቡበትን ሥልትም ከሳቸዉ ሌላ የሚያዉቅ ማግኘት ከባድ ነዉ።

በመሠረቱ የአሜሪካ ጦር አፍቃኒስታን የዘመተዉ በአፍቃኒስታን ሕዝብ ጥያቄ አልነበረም።የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ መስተዳድር ባለሥልጣናትም አል-ቃኢዳን ለማደን፥ ለአል-ቃኢዳ ከለላ የሰጠዉን ታሊባን ለማስወገድ እንጂ በአፍቃኒስታን ሕዝብ ጥያቄ ጦር ማዝመታቸዉን አልተናገሩም።

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ አለም አቀፍ ፀረ-ሽብር ዘመቻ ያወጁበት እና አፍቃኒስታን ጦር ያዘመቱበት ሁለተኛ ወር ሲዘከር እንዳሉትም ጦራቸዉ አፍቃኒስታን የዘመተዉ፥ አፍቃኒስታን ላይ ያስመዘገበዉ ድልም የአሜሪካኖች እንጂ የአፍቃኒስታን ሕዝብነቱን ለመናገር አልደፈሩም ነበር።

«የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ወንድና ሴት ባልደረቦች፥ በሙሉ ክሒልና ድል ሐላፊነታቸዉን እየተወጡ ነዉ።የአሸባሪዎችን ማሠልጠኛ ጣቢያዎች አዉድመናል።የመገናኛ ዘዴዎቹን አጥፍተናል።የታሊባንን የመዋጋት አቅም አዳክመናል።አብዛኛዉን የአየር መቃዋሚያዎቹን ደምስሰናል»

ሙለሐ መሐድ ዑመር መሐመድ ይዘዉት የነበረዉን ቤተ-መንግሥት ለመረከብ ያኔ ዋይት ሐዉስ ደጅ ይጠኑ የነበሩት ሐሚድ ካርዛይ ዛሬ በአስረኛ አመቱ አሁን ያሉትን ያሉት ከአንጀት ይሁን ካንገት አይታወቅም።የአፍቃኒስታን ሕዝብ የአሜሪካ ጦር ሐገሩ መግባት መዉጣቱን መወሰን፥ በመዉጣት መግባቱ መደሰት-መከፋቱን ቀርቶ የካርዛይን መሪነት መቀበል አለመቀበሉን እንኳን በትትክል የጠየቀዉ፥ በግልፅ የወሰነበት ጊዜም ግን የለም።

Barack Obama im Weißen Haus Unterschrift Automat Flash-Galerie
ኦባማምስል picture alliance/Photoshot

አሜሪካ መራሹ ጦር አፍቃኒስታን በመዝመቱ የአፍቃኒስታንን ሕዝብ-እንደ ሕዝብ መጠቀም መጎዳቱም እንደ ተመልካቹ የሚበየን፥ በሰል ያለ ጥናት የሚጠይቅ፥ ብዙ አከራካሪ፥ አወዛጋቢ ሊሆን ላይሆንም ይቻላል።የኦባማንም ሆነ የካርዛይን መልዕክት ብዙ መንግሥታት ተቀብለዉታል።እዚያዉ አፍቃኒስታን ያሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ ባለሥልጣናት ግን ከኦባማ እስከ ካርዛይ ያሉት መሪዎችና ባለሥልጣናት የአሜሪካ ጦር እንዲወጣ ለመወሰኑ የሰጡትን ምክንያት አይቀበሉትም።

የታሊባን ሸማቂዎች ከሚቆጣጠሩት አካባቢ ዉጪ ያለዉን የአብዛኛዉን ተራ አፍቃናዊ ስሜትና ፍላጎት ከዋሽንግ-ካቡል፥ ከፓሪስ ለንደን፥ ከኒዮርክ-ብራስልስ መሪዎች በተሻለ ሁኔታ የሚያዉቁት በካቡል የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ድርጅት ተጠሪ ወይዘሮ ዦርዤት ጋኞን እንደሚሉት ሰላማዊዉ ሰዉ አጣብቂኝ ዉስጥ ነዉ።«ብዙ፥ ብዙ፥ ብዙ የአፍጋን ሲቢሎች እመሐል መቃረጣቸዉን ይነግሩናል።በተፋላሚ ሐይላት ሁለት ወጥመድ ተይዘናል ብለዉ ነዉ የሚያስቡት።ከአደጋ የሚጠብቀን የለም።አንደኛዉ ወገን ከተጠጋን በሌለኛዉ ወገን እንጎዳለን።ሌላዉን ከተጠጋን በተቃራኒዉን እንገደላለን።እያሉ ይነግሩናል። ሥለዚሕ በተሻለ ሁኔታ ከአደጋ ሊጠበቁ ይገባል።ገለልተኛነታቸዉም ሊከበርላቸዉ ይገባል።»

ያም ሆኖ አሜሪካ አለች ሁሉም አለ ነዉ።ፕሬዝዳት ኦባማ የሰጡት ምክንያት፥ የአፍቃኒስታን ሕዝብ ፍላጎት ምንም ሆነ ምን፥ ዩናይትድ ስቴትስን ተከትለዉ አፍቃኒስታን ጦር ያሰፈሩት መንግሥታት አሜሪካን ተከትለዉ ጦራቸዉን እንደሚያስወጡ እያስታወቁ ነዉ።

አፍቃኒስታን ዉስጥ ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሎ በርካታ ጦር ያሰፈረችዉ ብሪታንያ ከአሜሪካ ጦር ጋር ያዘመተችዉን ጦሯን ከአሜሪካ ጦር ጋር ለማስወጣት ማቀዷ ሲዘገብ፥ ካናዳም የዕቅዱ ተካፋይ ናት።አነስተኛ ቁጥር ያላቸዉ ወታደሮች ካዘመቱት አንዷ ቤልጂግ መከላከያ ሚንስትሯ እንዳሉት በመጪዉ ጥር የጦርዋን ቁጥር በግማሽ ትቀንሳለች።ቤልጂግ ያዘመተችዉ ወታደር ስድስት መቶ ነዉ።

አንድ ሺሕ አምስት መቶ ወታደሮች ያዘመተችዉ ስጳኝ ከጦርዋ አስር በመቶዉን እስከ መጪዉ የጎሮጎሮሳዉያን አመት አጋማሽ ድረስ ታስወጣለች።የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሆሴ ሉዊስ ሮድሪጎስ ሳፓቴሮ ባለፈዉ አርብ እንዳሉት የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሙሉ በሙሉ ከአፍቃኒስታን የሚወጣበት ጊዜ፥የስጳኝ ጦርም ተተቃልሎ ሐገሩ የሚመለስበት ነዉ።2014

ከዩናይትድ ስቴትስና ከብሪታንያ ቀጥሎ ሰወስተኛዉን በርካታ ወታደር ያዘመተችዉ የጀርመን መከላከያ ሚንስትር ቶማስ ደ ሚዜየር ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ነገሩ አብረን እንዘምታለን አብረን እንመለሳለን አይነት ነዉ።

«የዩናይትድ ስቴትስ አቋም የብልሆች ነዉ።ከዚሕ ቀደም ተነጋግረንበታል።ለአፍቃኒስታን የተነደፈዉ ሥልት አካል ነዉ።የጋራ ሥልት ይሆናል።በመጪዉ ግንቦት የኔቶ ጉባኤ ቺካጎ ዉስጥ ሲደረግ የአሜሪካ ጉባኤተኞች ሚቀጥለዉን እርምጃ እንደሚያፀድቁ የአሜሪካዉ ፕሬዝዳት አስታዉቀዋል።ይሕ ማለት አብረን እንዘምታለን፥ አብረን እንመለሳለን ነዉ።አብረን ማለት ደግሞ በጋራ እንወስናለን ማለት ነዉ።»

አሜሪካ መራሹ ጦር አል-ቃኢዳንና ታሊባንን ለማጥፋት አፍቃኒስታን ከዘመተ አስር አመት ሊደፍን ሰወስት ወር ቀረዉ።በዚሕ ጊዜ ዉስጥ ታሊባን ተወግዶ ካቡል ላይ ለምዕራቦች ያደረ መንግሥት ተመሥርቷል።የአል-ቃኢዳዉ መሪ ኦስማ ቢን ላደን ከወር በፊት ተገድለዋል።ግን ፓኪስታን ዉስጥ።አፍቃኒስታን ዉስጥ መንገዶች፥ ትምሕርት ቤቶች፥ የጤና ጣቢያዎች ተገንብተዋል።

የሴቶች እኩልነትም ቢያንስ በአዋጅ ደረጃ ተከብሯል።ሰሜን አፍቃኒስታን ማዝሪ ኢ ሸሪፍ አይነቶቹን ከተሞች ያዩ እንደሚሉት ደግሞ የቦሊ ዉድ ፊልም ሙዚቃ ከየአዳራሽ-ራዲዮ ጣቢያዉ ሲንቆረቆር ይሰማል።

እርግጥ ነዉ ሰሜን አፍቃኒስታንን ድሮም ቢሆን የሚቆጣጠሩት ታሊባንን ይዋጉ የነበሩ የአካባቢዉ አማፂያን እንጂ ታሊባን አልነበረም።ከአስር አመት በፊት ቢሆን ኖሩ ግን የሰሜን አፍቃኒስታን ሕዝብ አንድም ሸማቂዎቹን በማስተናገድ፥ ሁለትም የታሊባን ሐይላትን ጥቃት በመስጋት ከመሽሎክሎክ አልፎ ሥለ ፊልም ሙዚያ የሚያስብበት ጊዜ አልነበረዉም።

ዛሬ የማዘር ኢ ሸሪፍ ነዋሪዎች ከሌሎች አካባቢዎች በተሻለ ነፃነት ይንቀሳቀሳሉ።ካቡልን ጨምሮ ማዕከላዊና ደቡባዊ አፍቃኒስታን ሰላም ዉሉ ሠላም ያደረበት ጊዜ የለም።ኦባማ ሮብ ላደረጉት ንግግር ድጋፍ ይሁንታዉ ከየአካባቢዉ በሚንቆረቆርበት ከሐሙስ እስከ ትናንት በነበረዉ አራት ቀናት ብቻ ከሐምሳ በላይ ሰላማዊ ሰዎች በቦምብ ተገድለዋል።


ሁለት የስጳኝ፥ አንድ የካናዳ እና ሁለት ዜጎነታቸዉ ያልተጠቀሰ ወታደሮች በተቀበረ ፈንጂና በጥይት ተገድለዋል።ፕሬዝዳት ኦባማ ግን አብዛኛዉ አፍቃኒስታን ተረጋግቷል ይሉናል።ኦባማ ተረጋግቷል ያሉት የማዘር ኢ ሸሪፍንና አካባቢዉን ማለታችዉ ከሆነ በርግጥ አልተሳሰቱም። የአፍቃኒስታንን አብዛኛ ግዛት የሚያመለክት ከሆነ ግን የትልቂቱ ሐገር ትልቅ መሪ አንድም እዚያ የሚሆነዉን አላሉትም ሁለትም ያሉትን በቅጡ አላጤኑትም።

አሜሪካ መራሹ ጦር አፍቃኒስታን ከገባ ጊዜ ጀምሮ ዓለም ሥለ አፍቃኒስታን ዉጊያ፥ ሽብር፥ ግድያ፥ የግድያ ዛቻ ሳይሰማ ዉሉ-ያደረበት ዕለት የለም።ዘጠኝ አመት ከዘጠኝ ወሩ።ፕሬዝዳት ካርዛይ የአሜሪካ ጦር መዉጣትን በደስታ ይቀበላዋል ያሉት የአፍቃኒስታን ሕዝብ ከሃያ-እስከ ሰላሳ አራት ሺሕ የሚገመት የዋሕ ሠላማዊ ወገኖቹን ለጦርነቱ ገብሯል።ዛሬም ሰዓት በሰአት እየተገደለ፥ እንደተሸማቀቀ ነዉ።

በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ የታሊባን ሸማቂዎችና የመንግሥት ወታደሮች አልቀዋል።ሁለቱም አፍቃኖች ናቸዉ።ሁለቱም ዛሬም እየተገደላደሉ ነዉ።በሚሊዮን የሚቆጠር አፍቃናዊ ተሰዷል።ከሁለት ሺሕ አምስት መቶ ሐምሳ የሚበልጥ የአሜሪካ መራሹ ጦር ባልደረቦች ተገድለዋል። አብዛኛዉ አሜሪካዊ ነዉ።ምዕራባዉያኑ ሐገራት ከአምስት መቶ ቢሊዮን ዶላር በላይ ከስክሰዋል።የአስር አመቱ ዉጤት፥-እንደገና ኦባማ

«ዕዳ በበዛብንና ምጣኔ ሐብታችን እንቅፋት በገጠመዉ ወቅት፥ ባለፈዉ አስርት አንድ ትሪሊዮን ዶላር ለጦርነት አዉጥተናል።አሁን ግን ሐብታችንን በአሜሪካ ትልቅ ቅምጥ ሐብት ላይ ማዋል አለብን።በሕዝባችን ላይ።አሜሪካ ሆይ! ወቅቱ፥ እዚሕ ሐገር ዉስጥ ሐገር የምንገነባበት ነዉ።»

Hamid Karzai Januar 2011
ካርዛይምስል AP

የጦርነቱ የአስር አመት ዉጤት የጦሩ መዉጣት ምክንያትነ የማይሆንበት ምክንያት እንደገና ያነጋግራለን።ለዛሬዉ ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ