1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኡሁሩ ኬንያታ ክስ መጓተት

ሐሙስ፣ ኅዳር 25 2007

ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀሎኞች መዳኛ ፍርድ ቤት (አይ ሲ ሲ )በኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ላይ የቀረበው ክስ በአንድ ሳምንት ውስጥ እንዲጠናቀቅ አለያም ክሱ እንዲሰረዝ ወሰነ ።የፕሬዝዳንቱን ጉዳይ የያዙት አቃቤ ህጎች መረጃ ለማሰባሰብ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸዉ ያቀረቡትን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ዉድቅ አድርጎቷል።

https://p.dw.com/p/1DzQT
Kenia Präsident Uhuru Kenyatta in Nairobi
ምስል Reuters/T. Mukoya


ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2007 በተደረገው የኬንያ ምርጫ ማግስት በተፈጠረው ትርምስ ለጠፋው ህይወትና ንብረት እጃቸው አለበት ተብለው ተከሰው ዘ-ሄግ በሚገኘው አለም አቀፍ ፍርድ ቤት(አይ ሲ ሲ) ችሎት የቆሙ ብቸኛው በስልጣን ላይ ያሉ መሪ ናቸው። ጉዳዩን የያዙት አቃቤ ህጎች ፕሬዝዳንቱ እጃቸው አለበት ላሏቸው የግድያ፤ግዞት፤አስገድዶ መድፈር፤ማሰቃየትና ሌሎች በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ የኬንያ መንግስትን ትብብር ጠይቀው ነበር። ከሳሾች ባለፈው ወር መጨረሻ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ደብዳቤ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸውም ጠይቀው ነበር። ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ በአንድ ሳምንት ውስጥ መረጃውን እንዲያቀርቡ አሊያም ክሱን እንዲሰርዙ አሳስቧል። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት አጊና ኦጅዋንግ ክሱ በአውሮጳውያኑ አዲስ አመት የመጀመሪያ ወራት እልባት እንደሚያገኝ ይናገራሉ።
«አቃብያነ ህጎቹ ዝግጁ ነን ካሉ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ የሚታይበትን ቀን ያሳውቃል።ይህም ከመጪዎቹ በዓላት በኋላ በታህሳስ እና ጥር አካባቢ ይሆናል። ከሳሾች ክሱን ለማጠናከር የሚያስችል አስፈላጊው ማስረጃ የለንም ካሉ ጉዳዩ የሚያበቃለት ይሆናል። ይህም ቢሆን ከሚቀጥለው አመት ታህሳስ ወይም ጥር በፊት ይፋ አይሆንም። አቃብያነ ህጎቹ ውስን ማስረጃ በእጃቸው ያለ በመሆኑ የክስ ሂደቱን ሊጀምር በሂደትም በሌሎች ጉዳዮች እንደሚደረገው ተጨማሪ ማስረጃ ለመሰብሰብ ሊያመለክት ይችላል።»
ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ ለክስ ባበቃቸው ምርጫ ማግስት ቀውስ 1,200 ሰዎች መሞታቸውን እና 600,000 ያህል ደግሞ ከቀያቸው መፈናቀላቸው ይነገራል። ይሁንና የአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ጠቅላይ አቃቢት ህግ ፋቱ ቤንሱዳና ባልደረቦቻቸው ጉዳያችንን ያስረዳልናል በማለት የጠየቋቸው የኩባንያዎች እና ባንኮች ዶሴዎች፤ የስልክ ንግግሮች፤የሃገር ውስጥ እና የውጪ የገንዘብ ዝውውሮችን የሚያሳዩ ማስረጃዎች ፈልገን አላገኘንም ብለዋል። ምስክሮቻቸውም ለደህንነታችን ሰጋን ብለው ወደ ኋላ ሸሽተዋል።
ኬንያታ ተሳትፈውበታል የተባለው ወንጀል የተፈጸመው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2007 ነበር። የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት (አይ ሲ ሲ) ክሱን የመሰረተው ግን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በመጋቢት 2011 ዓ.ም. ነው። ከአራት አመታት በኋላ። ፍርድ ቤቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪቃ ሃገራት ከፍተኛ ተቃውሞም ገጥሞታል። አፍሪቃውያን ላይ ይበረታል እየተባለም ይተቻል። አሁን በፍርድ ቤቱ በመታየት ላይ የሚገኙት ዘጠኝ ጉዳዮች በሙሉ የአፍሪቃውያን ናቸው። የአፍሪቃ ህብረት አባል ሃገራት አለምን ያሰጋሉ የሚባሉ ወንጀሎችን ለመዳኘት ከተቋቋመው ፍርድ ቤት ራሳቸውን ሊያገሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል። በፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ላይ የቀረበው ክስ ቀጣይ እጣ ፈንታ የፍርድ ቤቱን ህልውና ሊወስን ይችላል።

Niederlande Kenia Anhörung zu Gewalt nach Präsidentenwahl in den Haag William Samoei Ruto
ምስል dapd
Uhuru Kenyatta Empfang in Kenia 9. Oktober
ምስል Reuters/Noor Khamis


እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሃመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ