1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሕአዴግ ሃያኛ ዓመትና የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ 2

ረቡዕ፣ ግንቦት 24 2003

ኢትዮጵያ ውስጥ እሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ይሄው ባለፈው ሣምንት ሃያ ዓመቱን ደፈነ። ይህንኑ ጊዜ መለስ ብለን ስንዳስስ በተለይም የአገሪቱ የኤኮኖሚ ዕድገት አንዱ ዓቢይ መከራከሪያ ጉዳይ ነበር።

https://p.dw.com/p/RRER
ምስል picture alliance/dpa

ያለፉት ሃያ ዓመታት በኢትዮጵያ የነጎዱት ተሥፋ፤ ስጋትም የተዋሃዳቸው ሆነው ነው። የሕዝቡ ተሥፋ በአንድ በኩል በተለይም በኤኮኖሚ ዕድገት የሚያሳዝን ሆኖ ዛሬም የአገሪቱ መለያ ከሆነው ከድህነትና ከረሃብ መላቀቅ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀን ሶሥቴ በመመገብ ጠግቦ ለማደር እንዲበቃ በጊዜው መመኘት ማለማቸው አልቀረም። ይህ ሁሉ ተሥፋ ዛሬ ከምን ደረሰ፤ ብዙ የተነገረለት የኤኮኖሚ ዕድገትስ በማሕበራዊ ዕድገት ተንጸባርቋል ወይ? በኢትዮጵያ የፊናንስና ልማት ሚኒስቴር የግንኙነት ሃላፊ አቶ ሃጂ ኢብሣ በበኩላቸው እንደሚሉት መንግሥት ቀደም ባሉት አስተዳደሮች ዘመን አቻ ያልታየለት ዕድገትን አስመዝግቧል።

ይሁን እንጂ በሌላ በኩል ብዙዎች የዕድገቱን መጠን አጠያያቂ ሲያደርጉ ዕድገቱ በሕዝብ የኑሮ ሁኔታ መሻሻል እስካልተከሰተ ድረስ ዋጋ እንደሌለውም ነው የሚያስገነዝቡት። መረጃዎችን ለመጠቃቀስ ኢትዮጵያ ዛሬም የፖለቲካ ለውጥ ከተደረገ ከሃያ ዓመታት በኋላም በዓለም ላይ በዝቅተኛ የልማት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሊትስ-ዴቨሎፕድ ተብለው ከተደለደሉት የድሃ ድሃ አገሮች አንዷ ናት። በቅርብ በወጣ የሰብዓዊ ዕድገት መረጃ ዝርዝር መሠረት ኢትዮጵያ ከ 178 አገሮች 171ኛዋ ሆና ነው የምትገኘው። በሌላ በኩል ታዲያ መንግሥት እንደሚለው ባለፉት ዓመታት በተከታታይ ከፍተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት ከታየ ለመሆኑ ለምንድነው ይሄው በሕዝብ የኑሮ ሁኔታ መሻሻል ሲንጸባረቅስ የማይታየው? በተወካዮች ም/ቤት ብቸኛው የተቃዋሚ ወገን እንደራሴ አቶ ግርማ ሰይፉ እንደጠቀሱት ለዚሁ ምክንያቶች አልጠፉም።

ባለፉት አራትና አምሥት ዓመታት በኢትዮጵያ እንደ መንግሥቱ የዕድገት አሃዞች ሁሉ በሕብረተሰቡ ውስጥ የዋጋ ግሽበትንና የኑሮ ውድነትን ያህል ብዙ ያነጋገረ ሌላ ጉዳይ አይገኝም። ከሶሥት ዓመታት በፊት የምግብ ዋጋ ንረት ለብዙሃኑ የራስ ምታት በነበረበት ወቅት ፕሮፌስር መረራ ጉዲና በቀድሞው የተወካዮች ም/ቤት መንግሥት ላቀረበው የዕድገት ሪፖርት “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ” ሲሉ ነበር የተረት ምላሽ የሰጡት። ጊዜው ዛሬም ብዙ ቤተሰብ በፈረቃ እስከመመገብ የደረሰበት፤ ሥራ አጥነትም ይብስ እየተስፋፋ የሄደበት ነው። በውጭ የምግብ ዕርዳታ ላይ ያለው ጥገኝነትም ቀደም ሲል እንደታለመው ገና ያለፈ ታሪክ አልሆነም። በአጭሩ አሁንም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አልተቻለም። ለምን? የቀድሞው የም/ቤት ዓባል አቶ ተመስገን ዘውዴ እንደሚያስረዱት በተለይ ትልቁ ችግር የነጻ ገበያ ስርዓት አለመከበር ነው።

ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ በበኩላቸው የእርሻ ልማትን ከአምራች ኢንዱስትሪ ያስተሳሰረ የነጻ ገበያ ኤኮኖሚ መሠረተ-ዓላማዎችን የማይጋፋ ፍትሃዊ የዕድገት ፖሊሲ፤ የፖለቲካና የኤኮኖሚው ጋብቻም አገሪቱን አሁን ከምትገኝበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለማውጣት እንደሚበጅ ነው የሚያሳስቡትና የሚመክሩት። የፖሊሲ ተሃድሶ ያስፈልጋል ማለት ነው። መንግሥት በበኩሉ በአምሥት ዓመት የለውጥ ዕቅዱ ኤኮኖሚውን በሰፊው በማሳደግ አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገሮች ደረጃ ከፍ ለማድረግ ነው የሚያልመው። ይህ ታላቅ ግብ እንዲሣካ ከተፈለገ እርግጥ በሕብረተሰቡ ውስጥ ማሕበራዊ ኮንሤንስ፤ ማለት የሕብረተሰብ የሃሣብ ወይም የዓላማ አንድነት መስፈኑ ቁልፍ ነው።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዮ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ