1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሕአዴግ ጉባኤ ዉሳኔዎች

Eshete Bekeleማክሰኞ፣ ነሐሴ 26 2007

ከአለፉት 24 ዓመታት ወዲህ በስልጣን ላይ የቆየው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ትናንት ባጠናቀቀው ድርጅታዊ ጉባዔ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ላይ ትኩረት ሊሰጥ ነው ተባለ። የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ችግሩ መፍትሄ ካላገኘ ለስርዓቱ አደጋ ሊሆን እንደሚችል ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/1GPjL
Äthiopien Ministerpräsident Hailemariam Desalegn
ምስል Getty Images

[No title]

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ግንባር ኢሕአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝን በሊቀመንበርነት፤ አቶ ደመቀ መኮንን በምክትል ሊቀ-መንበርነት በመምረጥ ተጠናቋል። ከጉባዔው መጠናቀቅ በኋላ ኢህአዴግ ይፋ ባደረገው የአቋም መግለጫ «የመሬት፣የግብር ኣሰባሰብ፤የመንግስት ግዥና ኮንትራት አስተዳደር» ጉዳዮች ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን አስታውቋል።

ኢህአዴግ በመቀሌ ያካሄደውና ሊቃነ-መናብርቱን የመረጠበት ጉባዔ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ቢመክርም የመልካም አስተዳደር ጉድለት ቀዳሚው መሆኑን ጋዜጠኛ የማነ ናግሽ ይናገራል።

በግንቦት ወር የተካሄደውን አገራዊ ምርጫ መቶ በመቶ ያሸነፈው ኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔውን ከ2 እስከ ሁለት ዓመት ተኩል ባለ የጊዜ ልዩነት ያካሂዳል። አራት ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈው ግንባር ለ 24 አመታት ስልጣን ላይ የቆየ ሲሆን እስካሁን ግንባር እንጂ ፓርቲ አይደለም። ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት አስመዝግባለች የሚባለውን ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደ መከራከሪያ የሚያቀርበው ኢህአዴግ በሰብዓዊ መብት አያያዝ፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ሚዲያ ይዞታ የከፋ ትችት ይሰነዘርበታል። ጋዜጠኛ የማነ ናግሽ አሁን ትኩረት ያሻዋል የተባለው የመልካም አስተዳደር ጉዳይ መፍትሄ ካላገኘ ለስርዓቱ አደጋ ሊሆን ይችላል መባሉን ተናግሯል።

በጉባዔው መጠናቀቂያ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት ምክትል ሊቀ-መንበር ደመቀ መኮንን የመልካም አስተዳደር ችግርን አስጊነት ቢናገሩም ኢህአዴግ ያስቀመጠው አዲስ የመፍትሄ አቅጣጫ የለም ማለታቸውን ጋዜጠኛ የማነ ናግሽ ይናገራል። ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ