1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራቅ ምሥቅልቅል

ሰኞ፣ ሰኔ 9 2006

የአንጎሎ-አሜሪካን መሪዎች አዲሲቱ ኢራቅ በደም-አስከሬን፤ በሽብር፤ እልቂት፤ በጥፋት ዉድመት ቀለል ካለም እስረኞችን በማሰቃየት- ከድፍን ዓለም አንደኛ ሐብታም ሐገር ስትሆን-ሰዉዬዉም እንደ ሁሉም ዓለም አዩ።እንደ ሁሉም ኢራቃዊ ኖሩበት።አማረሩ።እንደ ሐይማኖት መሪ-አወገዙ፤ እንደ ወጣት ጥፋቱን-ሊያጠፋ ተነሳ።

https://p.dw.com/p/1CJNf
ምስል Reuters/Alaa Al-Marjani

በሁለት ሺሕ ሰወስት (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ ኦቆጣጠር ነዉ) የዋሽግተን ለንደን መሪዎች ለኢራቅ ሕዝብ ያንቆረቆሩትን ተስፋ ከንቱነት፤የጥፋት መሸፈኛቸዉን ዉንጀላ ባዶነት ለማጋለጥ፤ የደፈሩ፤ ጥፋቱ እንዳይደገም የመከሩ በርግጥ ነበሩ።አሉም። ሰሚ ግን የላቸዉም።የኢራቅ ሕዝብ ከታደለ እንደተሰደደ፤ ካልሆነለት በቦምብ፤ መድፍ አረር ያለቁ ሙታኑን ቀብሮ አሟሙትን እንዳሰላሰለ-አስራ አንደኛ ዓመቱን ተዘናገረ።ዛሬም ያልቃል።የባቢሎኖቹ ምድር ከባግዳድ፤ እስከ ሞሱል፤ ከፋሉጃሕ እስከ ባቁባ በደም አበላ ትታጠባለች።ሲያንስ እሰወስት ሲበዛ እብዙ ለመሸንሸን ተሰነጣጠቃለች።የሰሞኑ ጥፋት-እልቂት መነሻ፤ ሠብብ ምክንቱ ማጣቃሻ፤ እስተምሕሮቱ መድረሻችን ነዉ ።

ሥለ ዉልደት ዕድገታቸዉ ከሚታወቀዉ፤ የሚጠየቀዉ ይበልጣል።በ1971 ግድም ሰማራ-መወለዳቸዉን ግን ብዙዎች ይስማሙበታል።ሥማቸዉ ሰወስት ነዉ። ኢብራሒም አዋድ ኢብራሒም አል-በድሪ አል-ሰማሪይ-ረጅም ነዉ።ኢብራሒም አዋድ ኢብራሒም አል-በድሪ-መለስ ይላል። አቡበከር አል ባግዳዲ-አጭር ነዉ ።ባጭሩ እንጥራቸዉ።

ከባግዳድ ዩኒቨርሲቲ በእስልምና እስተምሕሮት በዶክትሬት ዲግሪ መመረቃቸዉን ብዙዎች ይናገራሉ።አንዳዶች የፕሬዝዳንት ሳዳም ሁሴንን አገዛዝ በመቃወም ይታገሉ ነበር ይላሉ።ሌሎችን ደግሞ የሳዳምን አገዛዝን «መቃወሙን ይቃወሙ ነበር።ተቃዉሟቸዉ ግን ሐይማኖት ከሚያስተምሩበት ከሰማራ መስጊድ ያለፈ አልነበረም ባይ ናቸዉ።ዶክተር ኢብራሒም ወይም አቡ-ዱዓ (የፀሎት አባት-መሪ እንደማለት ነዉ) ይባሉም ነበር።

Abu Bakr al-Baghdadi
ምስል picture alliance/AP Photo

የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ምርጥ ጦራቸዉ ከዘመናይ ጦር መሳሪያዉ ጋር ለኢራቅ ሕዝብ ነጻነት ብልፅግናን ታጥቆ መምጣቱን ዋሽግተን ላይ ሲያዉጁ ሰዉዬዉ ሠማራ-ሆነዉ ያደምጡ ነበር።መጋቢት አሥራ-ሰባት 2003።

(የኢራቅ ሕዝብ ሆይ) ተጣማሪ ሐይላችን የ(ገዢዎችሕን) ሥልጣን ሲይዝ የሚያስፈልግሕን ምግብና መድሐኒት እንሰጥሐለን።የሽብሩን መረብ እንበጣጥሰዋለን።አዲሲቱ፤ ባለፀጋ፤ ነጻ ኢራቅን እንድትገነባ እንረዳሐለን።በነጻይቱ ኢራቅ ጎረቤቶችሕን መዉረር አይኖርም።የመርዝ ፋብሪካ አይኖርም።ተቃዋሚዎች አይገደሉም።የማሰቃያ ማዕከላት፤የመድፈሪያ ክፍሎች አይኖሩም።አምባ ገነኑ በቅርቡ ይወገዳል።የነፃነትሕ ቀን ቀርቧል።»

ሰዉዬዉ ያኔ-አስተማሪም ሆኑ ታጋይ-እንደ አብዛኛዉ ኢራቃዊ በቦምብ ሚሳዬሉ ፍላፃ መሐል እየተሹለከለኩ-የጆርጅ ቡሽዋን «አዲሲቱን ኢራቅ» በተጨባጭ ለማየት ጊዜ አልፈጀባቸዉም።በሐብት ምንጭዋ-ነዳጅ ዘይቷ ምትክ የሰዉ ደም-ሲፈስ-ሲቀዳባት፤ የነዳጅ ዘይቷ ጉርጓዶች -እየጋዩ በሰዉ አፅም-አስከሬን ሲደፈኑ የጆርጅ ቡሽዋን ባለፀጋ ኢራቅ እንደ ሁሉም ኢራቃዊ በርግጥ አዩ።

የአንጎሎ-አሜሪካን መሪዎች አዲሲቱ ኢራቅ በደም-አስከሬን፤ በሽብር፤ እልቂት፤ በጥፋት ዉድመት ቀለል ካለም እስረኞች በማሰቃየት- ከድፍን ዓለም አንደኛ ሐብታም ሐገር ስትሆን-ሰዉዬዉም እንደ ሁሉም ዓለም አዩ።እንደ ሁሉም ኢራቃዊ ኖሩበት።አማረሩ።እንደ ሐይማኖት መሪ-አወገዙ፤ እንደ ወጣት ጥፋቱን-ሊያጠፋ ተነሳ።

Irak Unruhen ISIL Kämpfer in Mosul 11. Juni 2014
ምስል SAFIN HAMED/AFP/Getty Images

ወዲያዉ አሜሪካኖች በአሸባሪነት ጠርጥረዉ አሰሩት። 2005።ካምፕ ቡካ ከተባለዉ እስር ቤት በአራተኛ አመቱ ሲፈታ-ይበልጥ አክራሪ፤ ይበልጥ ፅንፈኛ ሆኖ፤ እነ አቡ ሙሳብ አል-ዘርቃዊ ይዘዉሩት የነበሩ የሽብር ቡድናትን ተቀየጠ።አል-ባግዳዲ ሆነ የትግል ሥሙ።

በ2006 ከተለያዩ ቡድናት ተሠባጥሮ የተመሠረተዉን የኢራቅ እስላማዊ መንግሥት «አይ ኤስ አይ »ድርጅትን የእልቂት ትርምሲቱን ኢራቅ የፈጠሩት ሐያላን ፖለቲከኞችና መገናኛ ዘዴዎች ሲያሰኛቸዉ የአል-ቃኢዳ ቅርንጫፍ፤ ሲላቸዉ በአልቃኢዳ ዓላማ የተነሳሳ፤ ሲፈልጋቸዉ የሱኒ አሸባሪ ሌላም ማለቱ አልገደዳቸዉም።

ቡድኑን ቀርብ ብለዉ ያጠኑ እንደሚሉት ግን ድርጅቱ ከአልቃኢዳና በአል-ቃኢዳ ከሚደገፉ ሐይላት ያፈነገጡ፤አሜሪካ መራሹን ወረራ የሚቃወሙ፤አሜሪካኖች በተከሉት የሺአ መንግሥት በተለይም ሱኒዎችን ባገለለዉ የኑሪ አልመሊክ አገዛዝ የተማረሩ፤ አልፎ ተርፎም የቀድሞ የኢራቅ መንግሥት ጦር አባላትን ሁሉ ያቀፈ ነዉ።የአዉሮጳ ሕብረት የፀጥታ ጥናት ተቋም ተመራማሪ ፍሎሬንስ ጋዉብ አንዷ ናቸዉ።

«በጥልቅ ከታየ፤ እስላማዉያን አሉበት፤በጎሳ የሚደገፉ አሉበት፤የቀድሞ የባዓዝ አባላት፤ የቀድሞ ጦር አባላት ብዙ ናቸዉ።ቀደም ሲል የኢራቅ ሱኒዎች በሳዑዲ አረቢያ ይደገፋሉ ተብሎ በሠፊዉ ይታመን ነበር።አሁን ግን ትንሽ ወሰብሰብ ያለ ነዉ።»

አል ባግዳዲ ከእስር ቤት እንደተፈታ የዚያ ድርጅት የመሪነት ሥልጣን ያዘ።ዩናይትድ ስቴትስ በ2011 አል-ባግዳዲን ለያዘ ወይም ላስያዘ አስር ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት አዉጃለች።ይሁንና የሶሪያዉ ጦርነት ሲፋፋም የአል-ባግዳዲ ቡድን በዩናይትድ ስቴትስ፤ ከሚደገፉ ሐይላት ጋር አብሮ የፕሬዝዳን በሽር አል-አሰድን መንግሥት ሲወጋ የዋሽግተን፤ብራስልስ መንግሥታት አይተዉ እንዳላዩ አለፉት።

Irak Mossul Flüchtlinge 12. Juni 2014
ምስል Reuters

እንዲያዉም በሳዑዲ አረቢያና በቀጠር ገንዘብ እየተገዛም በነፃ እየተሰጠም ምዕራባዉን መንግሥታት በቱርክ፤ በሊባኖስና በዮርዳኖስ በኩል ለሶሪያ አማፂያን ከሚልኩት ጦር መሳሪያና የዉጊያ ቁሳቁስ ያ ቡድን ይቀራመት ገባ።ሥሙንም የኢራቅና የሌቫንት (ሻም) እስላማዊ መንግሥት «አይ ኤስ አይ ኤስ» በምሕፃሩ ብሎ አሻሻለዉ።

ኢራቅን አተራምሰዉ ከነትርምሷ ጥለዋት የወጡት አንግሎ-አሜሪካኖች ሶሪያ ላይ «አይ ኤስ አይ ኤስ»ን እና ሌሎች አማፂያንን አስቀድመዉ፤የምዕራብ አዉሮጳ ሕያላንን፤እስራኤልን፤ የአረብ ቱጃሮችን እና ቱርኮችን አስከትለዉ፤የደማስቆ ገዢዎችን ካስቀደሙት ከሩሲያና ከኢራን ጋር ሶሪያን ሲያተራምሱ ብዙ የማይታወቁት ሰዉዬ-የሚመሩት ቡድን ብዙ የምትታወቀዋን ሞሶሉን በቅፅበት ተቆጣጠረ።የፊሪድሪሽ ናዉማን ጥናት ተቋም ባልደረባ ፋልኮ ቫልደ እንደሚሉት ሞሱል-ለኢራቅ ሁሉም ናት።

«ሞሱል ለየኢራቅ ሁለተኛ ከተማ ናት።ሥልታዊ ናት።ሞሱል የነዳጅ ዘይት መላኪያ ማዕከል ናት።ወደ ሶሪያ መሻገሪያ ናት።»

አማፂያኑ-ወትሮም የሚነዱት-መኪና አሜሪካ ሠራሽ ነዉ።ጠመንጃቸዉ-M16፤ መትረየሳቸዉ M 60 እና M 240።የጦር ሜዳ መነፅራቸዉ፦የሌሊት መመልከቻ ባትሪያቸዉ፤ አንዳዴ የሚለብሱት መለዮ (ዩኒፎርም) ሳይቀር-እርስዎ ካዩት-«ሜድ ኢን ዩኤስኤ» የሚል ያነባሉ

ሞሱል የሰፈረዉን የኢራቅ መንግሥት ጦርን በመብረቃዊ ዱላ ሲፈረካክሱት ሐፓቺ የተሰኙ የአሜሪካ ሔሊኮብተሮች እንደተኮለኮሉ ተረከቡ።ከሞሶል ያመለጡት የግዛቲቱ አገረ ገዢ እንዳስታወቁት አማፂያኑ ሞሱል የታጨቀዉን ግማሽ ቢሊዮን ዶላር፤ ከዶላሩ ብዙ የሚበልጥ ወርቅም አጋብሰዋል።

«የሚብሰዉ አማፂያኑ ሞሱል አለመቆማቸዉ ነዉ» ይላሉ ቫልደ።አልቆሙም።ባለፈዉ ጥር ፋሉጃሕንና መላዉ የአምባር ግዛትን ተቆጣጥረዋል።ከሞሱል በኋላ ቲግሪቲን፤ ባቁባን ይዘዉ ባግዳድን በ45 ደቂቃ ጉዞ ርቀት ላይ ሆነዉ እየቃኝዋት ነዉ።እነሆ-ያ ድብቅ ሰዉዬ-አሜሪካኖች የተከሉትን የአል-መሊኪ መንግሥትን ሲያገረግበዉ-የኢራቅን መንግሥት መርዳት አለብን-አሉ የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ።

«ኢራቅ ተጨማሪ ርዳታ ትፈልጋለች።ከኛ እና ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ተጨማሪ ርዳታ ትፈልጋለች። የትኛዉንም አማራጭ አላስቀርም። ምክንያቱም እነዚሕ ጂሐዲስቶች ኢራቅ ቀርቶ ሶሪያ እንኳ ቢሆን እግራቸዉን እንዳይተክሉ የማደረግ ድርሻ አለብን።»

Freiwillige Kämpfer wollen für die irakische Armee kämpfen 12.06.2014 Bagdad
ምስል Reuters

ኦባማ አዉሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከባቸዉን ወደ መካከለኛዉ ምሥራቅ አዝምተዋል።ሶሪያ ላይ ከዩናይትድ ስቴትስና ከተከታዮችዋ ጋር ተዘዋዋሪ ጦርነት የገጠመችዉ የዩናይትድ ስቴትስና የእስራኤል ቀንደኛ ጠላት-ኢራንም ልክ-እንደ አሜሪካ አዉሮጶች ሁሉ የባግዳድ መንግሥትን ለመርዳት ዝግጁነቷን አረጋግጣለች።ፕሬዝዳንት ሐሰን ሩኸኒ እንዳሉት መንግስታቸዉ የባግዳድ መንግሥትን ለመርዳት ይፋ ጥያቄ ብቻ ነዉ የሚጠብቀዉ።

«የኢራቅ መንግሥት የኛን ድጋፍ ከጠየቀ ጥያቄዉን እናጤነዋለን።እስካሁን ድረስ የርዳታ ጥያቄ አልቀረበልንም፤ ከተጠየቅን ግን በዓለም አቀፍ ሕግ-መሠረትና በጥያቄዉ ላይ ተመሥርተን የኢራቅን ሕዝብና መንግሥት እንረዳለን።»

ከዚሕ በፊት ያልጠቀመችዉ ዩናይድ ስቴትስም ሆነች ኢራን አሁን ለኢራቅ ሕዝብ የሚተክሩት መኖሩ በርግጥ አጠያያቂ ነዉ።የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ እንዳሉት ያሁኑ ጥፋት-የዩናይትድ ስቴት መራሹ ወረራ ዉጤት ነዉ።ኢራቅም እሰወስት ለመከፋፈል ከመጨረሻዉ መጀመሪያ ላይ ናት።

Irak Unruhen Freiwillige melden sich in Bagdad
ምስል Ali Al-saadi/AFP/Getty Images

ከ1991 ዱ የፋርስ ባሕረ-ሠላጤ ጦርነት ወዲሕ በአሜሪካኖች ድጋፍ አርቢል ላይ ራሥ-ገዝ መስተዳድር ያቆሙት ኩርዶች ሰሜናዊ ኢራቅን ከነፃ መንግሥት እኩል እየገዙ ነዉ።ሱኒዎች ISIS ኖረ አልኖረ ለአል-መሊኪ አይነቱ አገዛዝ እጅ አይሰጡም።ሺአዎችም የሱኒዎች ብቻ መንግሥት እንዲገዛቸዉ አይፈቅዱም።እብሪት የወለደዉን ጥፋት-በሌላ ጥፋት ለማጥፋት ሞክሮ-ጥፋት የመተካት ሥልት በድርድር ዉይይት ካልተተካ ላቭሮቭ ያሉት ሕቅ ባጭር ጊዜ መፍጋቱ አያጠያይቅም።

እንግዲሕ ጠቅላይ ሚንስትር ኑሪ አል መሊኪ ሲሆን ሐገራቸዉን ለማዳን ወይም እስካሁን እንደኖሩበት ስልጣናቸዉን ላጭር ጊዜ ለመጠበቅ አልማዞች-አንዷን ለመምረጥ፤ ወይም ዋሽግተን ቴሕራኖችን እኩል ለማስተናገድ መቀለጣጠፉን ሊያቁበት ግድ አለባቸዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ