1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራቅ እዉነት፣የባለጉዳዮች ፍላጎት እና ምርጫዉ

ሰኞ፣ የካቲት 29 2002

የትናንቱ ምርጫ ሒደት ኦባማ እንዳሉት የኢራቅ እልቂት ፍጅት የመቀነሱ፥ሐገሪቱ የራስዋን ፀጥታ፥ የሕዝቧን ደሕንነት በራሷ ሐይል ለማስጠበቅ የመቻልዋ ምልክት ነዉ

https://p.dw.com/p/MNDF
ምርጫዉምስል AP

08 03 10
የዓለም ዘዋሪዎችን ትኩረት፣የግዙፍ መገናኛ ዘዴዎቻቸዉን ሥርጭት-ሕትመት በማጨናነቅ ለስድስት አመታት የያዘችዉን የአለም የንደኝነት ሥፍራ በአፍቃኒስታን ከተቀማች በአመት አለፋት።ፕሬዝዳንት ኦባማ ሥለ አፍቃኒስታን፣ካሉ፣ካደረጉ ግን ዘለዋት አያዉቁም።ጠቅላይ ሚንስትር ብራዉን ቅዳሜ አፍቃኒስታንን የጎበኙት አርብ ሥለዚያች ሐገር ያሉትን ብለዉ ነበር።ሥለ ኢራቅ።የሪያድ፥ ደማስቆ፥ ካይሮ ገዢዎች ሥለ ምስቅልቅል አካባቢያቸዉ ከተናገሩት እጅግ-እጅጓ እሷ ናት።የቴል አቪቭ-ቴሕራን ጠላቶች ያማትሯታል።አለምን ሰቅዞ የያዘዉ የእልቂት ፍጅት በር የተበረገደበት ወረራ ሰባተኛ አመት ሊዘከር-ዕለታት ሲቀሩት ኢራቆች መረጡ።ትናንት።የኢራቅን እዉነት፣የባለጉዳዮችን ፍላጎት እና ምርጫዉን ላፍታ ቅኝታችን ርዕሥነት መረጥ ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።

ቦምቡ፥-መንገድ ዳር የተቀበረዉ፣ ከሩቅ የሚወነጨፈዉ ፥ በመኪና የተጫነዉ፥ ሰዉ ያሸረጠዉ ቦምብ-ይፈናዳል።ሕይወት-አካል፥ ሐብት ንብረት ያጠፋል።ቀሪዉን ያሸማቅቅ-ያሸብራል።ለሰባት አመት ሁለት ሳምንት ፈሪ።ትናንት ግን ብዙዉ ኢራቃዊ አልበገርም አይነት አለ።እሳቸዉ አንዱ ናቸዉ።

«ዛሬ ጠዋት ባግዳድ ዉስጥ ለድምፅ መስጪያ ጣቢያነት በሚያገለግሉ ትምሕርት ቤቶች ብዙ ቦምቦች ፈንድተዋል።መኖሪያ ቤቶችም ተመተዋል።ፅንፈኞች ፍራቻ ሊነዙብን ነዉ-የሚሹት። አንፈራም። እንመርጣለን።አማኝ ሕዝቦች ነን።»
ትናንት ብቻ-በትንሽ ግምት አርባ ሰዉ-ተገድሏል።የቆሰለዉን በዉል የቆጠረዉ የለም።በለቅሶ-ዋይታ፥ ሐዘን-ሰቆቃዉ መሐል-ባግዳዴዉ እንዳሉት ኢራቆች መረጡ።መምረጥ ከሚችለዉ አስራ-ዘጠኝ ሚሊዮን ሕዝብ መካካል ግማሽ ያሕሉ ድምፁን ሰጥቷል።ሰወሰት መቶ ሃያ-አምስት መቀመጫዎች ላሉት ምክር ቤት ስድስት ሺሕ እጩዎች ተወዳድረዋል።

Flash Irak Wahl 2010
መረጠችምስል AP

የምርጫዉ ዉጤት በርግጥ አለየም።ከአራት አመት በፊት እንደተደረገዉ ከትላልቆቹ የፖለቲካ ማሕበራት በምርጫዉ አልሳተፍም ያለ ግን የለም።ሰባት ትላልቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተካፍለዋል።እና ምናልባት ከጠቅላይ ሚንስትር ኑሪ አል መሊኪ፥ ከፕሬዝዳት ጀላል ጠለባኒ እኩል ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማም ተደስተዋል።

«ይሕ በኢራቅ ታሪክ እጅግ አስፈላጊ የማዕዘን ድንጋይ ነዉ።በደርዘን የሚቆጠሩ ፓርቲዎችና ተጣማሪዎች በሺሕ የሚቆጠሩ የምክር ቤት እጩ እንደራሴዎችን አስመዝግበዋል።-ሴቶችናወንዶችን። በሐምሳ ሺሕ የምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ ተሰጥቷል።በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢራቃዉያን በከፍተኛ ስሜትና ተስፋ ድምፃቸዉን ሰጥተዋል።የዛሬዉ ምርጫ የወደፊቷ ኢራቅ በኢራቃዉያን እጅ መሆኗን በግልፅ ያመለክታል።»

ፕሬዝዳት ኦባማ የሚደሰቱ-ያሉትን የሚሉበት ብዙ-ምክንያት ነዉ ያላቸዉ።የስጳኙን የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ሆዜ ማርያ አዝናርን፥የአዉስትሬሊያ አቻቸዉን ጆን ሐዋርድን በየዝባቸዉ የተዋዉሞ ድምፅ፥ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌርን በበታቾቻቸዉ ግፊት፥መከላከያ ሚንስትር ዶናልድ ራምስ ፌልድን፥ ከነምክትላቸዉ፥በአለቆቻቸዉ ጫና ከየሥልጣናቸዉ ያስወገደዉ የኢራቅ ወረራ መዘዝ መሆኑን ኦባማ ጠንቅቀዉ ያዉቁታል።

ፕሬዝዳት ጆርጅ ቡሽን ክብር፥ ሥም፥ ዝና ተወዳጅነታቸዉን አራቁቶ -ጡረታ የዶለዉ፥የፖለቲካ ፓርቲያቸዉን በሕዝብ ድምፅ ያስቀጣዉ የዚያ ወረራ ለእሳቸዉም እንደማይለመስ ኦባማ በርግጥ ሊዘነጉት አይችሉም።ለሥልጣን ከተመረጡበት ዋና የዉጪ መርሐቸዉም አንዱ ኢራቅ የሰፈረዉን የዩናይትድ ስቴትስ ጦርን ማስወጣት ነዉ።ይሕን ሊያደርጉ ቀን ቆርጠዋል።ጦሩን ከዋና ዋና ከተሞች አስወጥተዋልም።

የትናንቱ ምርጫ ሒደት ኦባማ እንዳሉት የኢራቅ እልቂት ፍጅት የመቀነሱ፥ሐገሪቱ የራስዋን ፀጥታ፥ የሕዝቧን ደሕንነት በራሷ ሐይል ለማስጠበቅ የመቻልዋ ምልክት ነዉ።በርግጥም ኢራቂ ቦዲ ካዉንት የተባለዉ ተቋም እንደዘገበዉ በ2009 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ኢራቅ ዉስጥ የተገደለዉ ሰላማዊ ሰዉ ቁጥር በሁለት ሺሕ ስምንት ከተገደለዉ በግማሽ ያሕል የቀነሰ ነዉ።አራት-ሺሕ ስድት መቶ ብቻ።

የመከላከያ ጉዳይ አጥኚ ስቴፋን ቢድል ይሕ የበጎ ተስፋ ጭላንጭል መሆኑን ይመሰከራሉ።የኦባማ መስተዳድር ባለሥልጣናት ሥለ ኢራቅ የሚሰጡትን በጎ ተስፋ-ያክል ግን ተስፋ የለም።

«እንደሚመስለኝ ሁኔታዉ አንዳዶች እንደሚሉት በቀቢፀ ተስፋ የተሞላ አይደለም።ኢራቅ በሁለት ሺሕ ስድስትና ሰባት እንዳየነዉ ወደለየለት ጦርነት ትገባለች የሚሉ ወገኖችን ያክል ቀቢፀ-ተስፈኛ አይደለሁም።ይሁንና የዚያኑ ያክል ሁኔታዉ ብዙ አሜሪካኖች በተለይም በኦባማ መስተዳድር ዉስጥ ያሉት -የኢራቅ ችግር መፍትሔ አግኝቷል።ኢራቅ ወደለየለት ሁከትና ትርምስ አትመለስም ብለዉ እንደሚናገሩትም አይደለም።እንደሚመስለኝ አሁን ያለዉ ሁኔታ ከሁለት ወደ አንዱ ሊያመራ የሚችል የሽግግር ሒደት ነዉ።»

ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ላለፉት ሰላሳ አመታት በየሰበብ አስባቡ-የምትጋጭ፥ የምት ወዛገብ፥ የምትሻኮተዉ ኢራን በሳዳም ሁሴን የሥልጣን ዘመን ተጨቆኑ፥ ተረገጡ ለሚባሉት ለሺዓ ፖለቲከኞች መሸሸጊያ ሆና ዙሪያ መለስ ድጋፍ ስትሰጥ ኖራለች።ጠቅላይ ሚንስትር ኢያድዊ፥ ከሳቸዉ በፊት የነበሩት ኢብራሒም ጀአፈሪ፥ ዩናይትድ ስቴትስን ኢራቅን እንድትወር ከፍተኛ ግፊት ያደርጉ የነበሩት አሕመድ ቻሊቢ በአሜሪካኖች የደም፥ ገንዘብ፥ ድጋፍ የሳዳም ሁሴንን መንበር የያዙት ከኢራን እየገቡ ነዉ።
ብዙዎች እንደሚሉት በሳዳም ሁሴን መንግሥት መወገድ ያሸነፈች፥ የተደሰተች፥ ምናልባት የተጠቀመችዉ ኢራን-እንጂ አሜሪካ አይደለችም።ባሁኑ ምርጫ ሱኒዎች በሰበብ አስባቡ በምርጫዉ እንዳይሳተፉ ግፊት የሚያደርጉትም የኢራን ታማኞች ሊሆኑ-ይችላል የሚል ግምት አለ።ወደ ኢራን የሚያደሉት የሺዓ ፖለቲከኞች እንዲያሸፉ ቴሕራኖች ጠቀም ያለ ገንዘብ ማፍሰሳቸዉም በሰፊዉ ይወራል።
የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ኢራን አል-ቁድስ የተሰኘዉን እና ሌሎች የኢራቅ ደፈጣ ተዋጊ ቡድናትን ታስታጥቃለች።የኢራንን ተፅዕኖ-ዩናይትድ ስቴትስ፥ ስዑዲ አረቢያ፥ ግብፅና ዮርዳኖስን የመሳሰሉ የዋሽንግተን ወዳጆች እንደዋዛ የሚያዩት አይደለም።ወደ ዉጪ ከተሰደዉ ኢራቃዊ ከግማሽ የሚልቀዉን የምታስተናግደዉ ሶሪያ ግን ከሱኒነቷ ይልቅ-ፖለቲካዊ ፍላጎትዋ የጠላቷ ጠላትን እንድትመርጥ ግድ እንዳላት ነዉ-እስካሁን።ኢራንን።

የዋሽንግተን ሪያድ፥ አማን-ካይሮ፥ የቴሕራን-ደማስቆ ጥልፍልፍ የኢራቅ ፖለቲከኞችን-ከፖለቲካዊ ልዩነታቸዉ አልፎ በሐይማኖት ሱኒ-ሺዓ፥ በጎሳ ኩርድ-አረብ እያለ እንዳያናክሳቸዉ ነዉ-ሥጋቱ። የምርጫ ዉጤት ሽኩቻዉን የሚያረክስ አይነት ካልሆነ የወታደራዊ ጉዳይ አዋቂ ስቴፋን ቢድል እንደሚሉት በጎ-መጥፎ አቃርጠዉ የያዟት የኢራቅ ወደ እኩዩ ልትንሸራተት ትችላለች።

«ምናልባት መጥፎ ነገር ከተከሰተ እንበል ለምሳሌ ሱኒዎቹ ምርጫዉ ተጭበርብሯል።በሙስና ተንሰራፍቷል፥ እና ጥቅማችን ላደጋ ተጋልጧል ብለዉ ካመኑ አደገኛ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል።»

Flash Irak Anschläge Wahltag 2010 Bagdad
እና---ሽብሩምስል AP

የሜክሲኮ ጦር ከአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ታጣቂዎች ጋር ከፍተኛ ዉጊያ የገጠመበት ግዛት አስተዳዳሪ «ይሕ የዉጊያ ቀጠና» አሉ ባለፈዉ አርብ።«ይሕ የኛ ኢራቅ ነዉ።» አከሉ።በርግጥም ፕሬዝዳንት ፌሊፕ ካልዴሮስ ከ2006 ወዲሕ ብቻ ከ18 ሺሕ ስድስት መቶ በላይ ሕይወት ያጠፉትን የአደዛዥ ነጋዴዎችን ካለጠፉ-አዝናርን፥ ብሌርን፥ ሐዋርድን እንደሚሆኑ በትክክል ተረድተዉታል።የኢራቅ ምሥቅልቅል ግን ለሜክሲኮዎች ከአብነት በላይ ብዙ ትርጉም አይነረዉም።ለኢራቆች የመኖር-አለመኖር ጥያቄ ነዉ።ለሐያላኑ፥ ላካባቢዉም ሐገራትም የበላይ በታችነት ሽኩቻ አዉድ። ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።