1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራቅ ጦር የራማዲ ድል

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 20 2008

የኢራቅ ጦር እራሱን «እስላማዊ መንግስት» እያለ የሚጠራውን ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን ከራማዲ ከተማ አስወጥቶ ከተማይቱን ሙሉ ለሙሉ ቢቆጣጠርም በመቶዎች የሚቆጠሩ የአክራሪ ቡድኑ ታጣቂ አባላት ከተማይቱ ውስጥ እንደሚገኙ ተዘግቧል። ዝርዝር ዘገባ አለው።

https://p.dw.com/p/1HWHI
Irak Rückeroberung von Ramadi
ምስል Getty Images/AFP/A. Al-Rubaye

[No title]

በዩናይትድ ስቴትስ እና ተባባሪዎቿ የአየር ድብደባ እገዛ የሚደረግለት የኢራቅ ጦር የአንባር አውራጃ መዲና የሆነችው ራማዲን መቆጣጠሩ የተነገረው ባለፈው ሰኞ ነበር። የኢራቅ ጦር ገስግሶ እስኪደርስ ድረስ ካለፈው ግንቦት ጀምሮ የራማዲ ከተማን እራሱን «እስላማዊ መንግስት» ብሎ በሚጠራው ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን ቁጥጥር ስር ነበረች። የኢራቅ ጦር በከተማዪቱ ድል እንደተጎናፀፈ ከገለጠ ከቀናት በኋላ ግን ከተማዪቱ ውስጥ ወደ 700 የሚጠጉ የአክራሪ ቡድኑ ታጣቂዎች መሸሸጋቸው ዛሬ ተዘግቧል። ራማዲን የተቆጣጠረው የኢራቅ ጦር ቃል አቀባይ ያሕያ ረሱል ጦራቸዉ ከተማይቱን ብቻ ሳይሆን ባካባቢዉ የሚገኙ ቀበሌዎችንም መቆጣጠሩን ተናግረው ነበር።

«የኢራቅ ሕዝብ ሆይ፤ የጀግናዉ ሠራዊታችንን ድል እናበሥርሐለን። ራማዲን ከእስላማዊ መንግሥት ጀሌዎች እጅ ተቆጣጥረን በዙሪያዋ የሚገኙ አካባቢዎችን አንድ፤ በአንድ ነፃ አዉጥተናል። የራማዲ ከተማ ነፃ ወጥለች። የጦሩ የፀረ-ሽብር ሐይል የኢራቅን ባንዲራ በመንግሥት ሕንፃዎች ላይ አዉለብልቧል።»

ዛሬ የወጡ ዘገባዎች እንደሚጠቅሱት ከሆነ ግን ቁጥራቸው 700 የሚደርስ የጽንፈኛው ቡድን ታጣቂዎች በከተማዪቱ እምብርት እና ምስራቃዊ ቀበሌዎች ተሸሽገዋል። አብዛኛው የአንባር አውራጃ የጽንፈኛ ቡድኑ ታጣቂዎች ከቀበሯቸው ፈንጂዎች መጽዳት እንደሚገባው የኢራቅ ጦር አስታውቋል።

የኢራቅ ጦር የራማዲ ከተማን ሲቆጣጠር የመጀመሪያው ታላቅ ድል ተብሎለታል። በእርግጥ ጦሩ ወደ ከተማዪቱ ሲዘልቅ ያለምንም ውጊያ እንደነበር ተዘግቧል። የራማዲ ፖሊስ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ሐሚድ አደል ራሺድ ጦራቸው ራማዲ ከተማ ሲገባ እንዲህ ብለው ነበር።

የኢራቅ ጦር በራማዲ ከተማ
የኢራቅ ጦር በራማዲ ከተማምስል Getty Images/AFP/A. Al-Rubaye

«ወታደሮቻችን አሁን ቦታውን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረዋል። የመንግሥት ሕንፃው ብቻ ከ100 እስከ 150 ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው። እንደ ፈጣሪ ፍቃድ እሱም ቢሆን አሁን ነፃ ይወጣል»

ይኽ በእንዲህ እንዳለ ዩናይትድ ስቴትስ እና ተባባሪዎቿ ኢራቅ እና ሶሪያ ውስጥ የሚገኙ የጽንፈኛ ቡድኑ ይዞታዎች ላይ ዛሬ 28 ዙር የአየር ድብደባ ማከናወናቸው ተገልጧል።

የኢራቅ ጠቅላይ ሚንስትር ሀይደር አል አባዲ ራማዲ ከተማን ለማረጋጋት በከፍተኛ ባለስልጣናት የሚመራ ኮሚቴ በአስቸኳይ እንዲቋቋም ትእዛዝ አስተላልፈዋል። ሠላማዊ ሰዎች በሰላም ወደየቤታቸው መመለስ እንዲችሉ በከተማዪቱ ተቀብረው የሚገኙ ፈንጂዎችም በፍጥነት እንዲወገዱ አሳስበዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለከተማዪቱ የመልሶ ግንባታ መንደርደሪያ 20 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብሎዋል። ራማዲ ከተማ በጽንፈኛው ታጣቂ ቡድን እና በዩናይትድ ስቴትስ የአየር ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ መጎዳቷ ተዘግቧል። የኢራቅ የንግድ ሚንስቴር መሥሪያ ቤት ወደ ራማዲ ከተማ ለድንገተኛ ጊዜ የሚሆን የምግብ ርዳታ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደነበረም ተናግሯል።

ማንተጋፍቶትስ ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ