1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራን ምርጫና የለዉጥ ተስፋ

ሰኞ፣ ሰኔ 10 2005

በርግጥም ባሁኑ ምርጫ የድምፅ ማጭበርበር፥ ሐሜቱም መኖሩ አልተነገረም።በሁለት ሺሕ ዘጠኝ የታየዉ አይነት ወቀሳ፥ ትችት፥ የአደባባይ ሥልፍ ግጭትም የለም።ጥያቄዉ ሩሐኒ የሚጠበቁትን ያክል፥ መስራት ይችሉ ይሆን ወይ ነዉ?

https://p.dw.com/p/18rKA
epa03748799 Iranian President-elect Hassan Rowhani greets media during a press conference in Tehran, Iran, 17 June 2013. President-elect Rowhani said on 17 June that Iran would be ready to reduce tensions with arch-enemy United States based on goodwill and mutual respect. 'With the US we have an old wound but we are still ready to look into the future and reduce tensions, but on the basis of goodwill and mutual respect,' Rowhani said. On the topic of Syria he said that Iran would continue supporting the government of Syrian President Bashar al-Assad until an election in 2014. EPA/ABEDIN TAHERKENAREH +++(c) dpa - Bildfunk+++
ሐሰን ሩሐኒምስል picture-alliance/dpa

ከእስራኤልና ከእስራኤል ጥብቅ ደጋፊ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር እንደተፋጠጠች፣ በጣሙን በሒዝቦላሕ በጥቂቱ በሐማስ በኩል እንደተኮራኮመች፣ለዉጊያም እንደተዛዘተች ነዉ።ከምዕራብ አዉሮጶች ጋርም ትወዛገባለች።ኢራን።የሞስኮ፣ ቤጂንጎች ወዳጅ ናት።በሶሪያዉ ጦርነት ከደማስቆ ገዢዎች ወግና ከምዕራቦችና ለምዕራቦች ካደሩት ከአረብ ነገሥታት፥ ከቱርክ መሪዎችም ጋር በተዘዋዋሪ ትፋለማለች። ደግሞ በተቃራኒዉ የቱርክ ወዳጅ ባትባል ጠላት አይደለችም።አሜሪካኖች የመሠረቱት የባግዳድ መንግሥትም ሸሪክ ነች።ልዕለ መሪዋ የያዙትን ሥልጣን እንደያዙ ናቸዉ።አዲስ ፕሬዝዳንቷን ግን አርብ መረጠች።ነባሩን ለወጠችም።ኢራን። ጥቅል መርሕ፣ አቋሟ የጠላቶችዋ አስተሳሰብስ ይለዉጥ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
             

የምርጫዉ ዋዜማ።የዓለም ብቸኛ ልዕለ-ሐያል ሐገር የዩናይትድ ስቴትስ እና የጥንታዊቱ፥ ታሪካዊት፥ ሐገር የቃላት እንኪያ ሠላንቲያ ከ1979ኙ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የኢራን እስላማዊ አብዮት ድል ጀምሮ እንደነበረዉ ነበር። የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ምክትል ቃል አቀባይ ፓትሪክ ቬንትሬል እንዳሉት ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ የኢራኑ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የኢራንን ሕዝብ ፍላጎት የሚወክል ይሆናል ብላ አትጠብቅም።
                  
«ምርጫዉን በተመለከተ፥ ያልተመረጠዉ እና በኢራን ሕዝብ ዘንድ ተጠያቂነት የሌለዉ የኢራን የበላይ ጠባቂ ምክር ቤት፥ እጩ ሊሆኑ የሚችሉ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን እጩነት ግልፅ ባልሆነ መመዘኛ በእጩነት እንዳይቀርቡ አግዷል።ሥለዚሕ ምርጫዉ ግልፅነት ሥለሚጎድለዉ ተወዳዳሪዎቹ የኢራንን ሕዝብ ይወክላሉ ብለን አናምንም።»

የቴሕራን ሹማምንት አፀፋም ዋዛ አልነበረም።የሐገሪቱ ላዕላይ መሪ ዓሊ ሁሴይን ኻማኒ ባለፈዉ ዓርብ።
               
«በቅርቡ የአሜሪካ ብሔራዊ የፀጥታ ምክር ቤት አባል የሆኑ አንድ ግለሰብ የኢራን ምርጫ ተቀባይነት ያለዉ ነዉ ብለን አንቆጥረዉም ብለዉ መናገራቸዉን ሰማሁ።ጥሩ! ምን ይሁን ታዲያ? ገሐነብ ግቡ።የኢራን ሕዝብ እናንት አሜሪካዉን የምትፈልጉት ለፈፀም፥ የማትፈልጉትን ላለመፀም የሚጠብቅ ከሆነ ይሕ (ለኢራን) ኪሳራ ነዉ።»

ኢራኖችን የሚወክለዉ ሐይል ማንነት-አሜሪካኖች እንዳሉት በሕዝብ ያልተመረጠዉ ሐይል፥ ወይም ቴሕራኖች እንደተናገሩት ላዕላይ ምክር ቤት ይሁን አይነት መለየት በርግጥ ከባድ ነዉ። አያቶላሕ ዓሊ ኻማኒ የሚመሩት የኢራን ላዕላይ ምክር ቤት ከምርጫዉ ሒደት እስከ ሐገሪቱ ፀጥታ ያለዉን እንቅስቃሴ መቆጣጠሩ ግን ሐቅ ነዉ።


ከሁለት ሺሕ አምስት ጀምሮ የኢራንን የፕሬዝዳንት ሥልጣን ይዘዉ የነበሩት ማሕሙድ አሕመዲ ነጃድ የሥምንት ዓመት ዘመነ-ሥልጣናቸዉ ማብቃቱ፥ የኢራን ሕዝብ በምትካቸዉ አዲስ ፕሬዝዳት መምረጡም እዉነት ነዉ።አሸናፊዉ።
              
«ሚስተር ሐሰን ሩሐኒ ከአጠቃላዩ ድምፅ 18, 613,ሺ 329ኙን በማግኘት በአብላጫ ድምፅ አሸንፈዋል።የአስራ-አንደኛዉ ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ናቸዉ።ድምፅ መስጠት ከሚችለዉ 50 ሚሊዮን 483 ሺሕ 192 ሕዝብ፥ 36 ሚሊዮን፥ 704 ሺ 156 ሕዝብ ማለት፥ ሰባ ሁለት ነጥብ 7 ከመቶዉ መርጧል።»

የኢራን የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር ሙስጠፋ መሐመድ ናጅር።ሩሐኒ ሥልሳ-አራት ዓመታቸዉ ነዉ።አያቶላሕ ኾሚኒ የሚመሯቸዉ እስላማዊ አብዮተኞች የያኔዉን የኢራን ዘዉዳዊ አገዛዝ ለማስወገድ አንድ ሁለት ማለት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ከኢራን ፖለቲካ ተለይተዉ አያዉቁም።በ1965 እንደ ወጣት የእስልምና ሐይማኖት ተማሪ በየዩኒቨርቲዉ በተለይም የሚደረገዉን እንቅስ በተለይም የእስልምና ሐይማኖት ተማሪዎች ያደርጉት በነበረዉ ትግል ግንባር ቀደም ተሳታፊ ነበሩ።

በ1979 የኢራንን የረጅም ጊዜ ገዢ የሻሕ መሐመድ ሬዛ ፓሕላቪ ዙፋናዊ አገዛዝ በተወገደ ማግሥት በተመሠረተዉ የኢራን እስላማዊት ሪፐብሊክ መንግሥት ዉስጥ በተለያዩ ደረጃዎች ሠርተዋል።የኢራን ምክር ቤት አፈጉባኤ፥ የኢራን የኑክሌር ጉዳይ ተደራዳሪ ሆነዉ አገልግለዋል።በፕሬዝዳት አኽበር ሐሺሚ ራፍሳንጃኒ እና በመሐመድ ኻታሚ የሥልጣን ዘመን የኢራን ላዕላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ሆነዉ ለአስራ-ሥድስት ዓመታት ያሕል ሠርተዋል።

ላዕላይ መሪ ዓሊ ሁሴይን ኻማኒ የሚመሯቸዉ የአክራሪ አያቶላሆችን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ችላ እያሉ ለዘብተኛ የሚባለዉን መርሕ መከተል የጀመሩትም ከፕሬዝዳት አሕመዲነጃድ በፊት የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን ይዘዉ ከነበሩት ከመሐመድ ኻታሚ ጋር የቅርብ ግንኙነት ከመሠረቱ በሕዋላ ነዉ።የመሐመድ ኻታሚና የተባባሪዎቻቸዉን ጠንካራ ድጋፍ ባያገኙ ኖሮ ባሁኑ ምርጫ ለዕጩነት መብቃታቸዉ አንዳዶች እንደሚሉት ሲበዛ አጠራጣሪ ነበር።

ዕጩነቱን የኢራን የበለይ ጠባቂ ምክር ቤት ካፀደቀላቸዉ በሕዋላ እንኳን ወግ አጥባቂዎቹ የጋረጡባቸዉን የተለያዩ መሰናክሎች በዘዴ ማለፍ ግድ ነበረባቸዉ።በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት ኢራንን ከምዕራባዉያን ጋር ለሚያዛዝተዉ የኑክሌር መርሐ-ግብር ዉዝግብ በድርድር እልባት ለመፈለግ ቃል ገብተዋል።ምዕራባዉያንና በምዕራባዉያን ግፊት በኢራን ላይ በተጣላዉ ማዕቀብ የተጎዳዉን ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል አበክረዉ እንደሚሰሩም በተደጋጋሚ አስታዉቀዋል።
                  
«ሐገሪቱን ለማበልፀግ፥የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል እና ሠላምና መረጋጋትን ለማስፈን ከፈለግን ሕግና ሥርዓትን ከማስፈንና ለሕግ ከመገዛት የተሻለ አማራጭ የለንም።»

የቀድሞዉ የቴሕራን ከንቲባ ማሕሙድ አሕመዲነጃድ በ2005 ለፕሬዝዳትነት ሲወዳደሩ የደኸዉን ኢራናዊ የዕለት ከዕለት ኑሮ ለማሻሻል፥ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ቃል ገብተዉ ነበር።አያቱላሆች በሚመሯት ኢራን በአንፃራዊ መመዘኛ ወጣቱ፥ ከመንፈሳዊዉ ይልቅ ዓለማዊዉን ትምሕርት (ምሕንድስና) የተማረዉ ከደኸ የሚወለደዉ ፖለቲከኛ የገባዉን ቃል አያከብርም ብሎ የጠረጠረ አልነበረም።

በከንቲባነት ዘመነ-ሥልጣናቸዉ የትልቂቱን ከተማ አስተዳደር በመለወጥ፥ የመሠረተ-ልማት አዉታሮቿን በማሻሻላቸዉ ከሁሉም በላይ ለዶሆቹ የከተማይቱ ነዋሪዎች ጠቀም ያለ ድጎማ በመሥጠታቸዉ ያተረፉት ሥምና ዝና መላዋ ኢራንን ለመለወጥ ይችላሉ የሚል ተስፋ አሳድረዉ ነበር።

ኮት ሰደሪያ እንጂ-እንደ አያቶላሆቹ ጀላቢያ አያጠልቁም።ደግሞ በተቃራኒዉ ኮት ይልበሱ እንጂ ከራባት አያስሩም።ለፕሮቶኮል አይጨነቁም።ለመጀመሪያ ጊዜ ቴሕራን ቤተ-መንግሥት እንደገቡ በዉድ ዋጋ የተገዛዉ የፅሕፈት ቤታቸዉ ምንጣን ከቢሮ እንዲወጣ ነበር ያደረጉት።

በመጀመሪያ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ ከነዳጅ ዘይት ከሚገኘዉ ጠቀም ያለ-ገንዘብ እየቆነጠሩ ዝቀተኛ ገቢ ያለዉን ሕዝብ ኑሮ ለመደጎም ያደረጉት ሙከራ በሆነ-ደረጃ ተሳክቶላቸዉ ነበር።ይሁንና አሕመዲነጃድ ኢራንን ወትሮም በጠብ ከሚፈልጓት ከእስራኤል፥ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከምዕራብ አዉሮጶች ጋር የገጠሙት የለየለየት አተካራ ለሳቸዉም ለሐገራቸዉም፥ ብዙም የፈየደዉ የለም።በኢራን ላይ ምዕራባዉያን ሐገራት በየግላቸዉ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት የጣሉ እና ያስጣሉት ተጨማሪ ማዕቀብ የሐገሪቱን ምጣኔ ሐብት ክፉኛ ነዉ የጎዳዉ።

አሕመዲነጃድ ሥልጣን ሲይዙ በአማካይ በዓመት በሰባት ከመቶ ያድግ የነበረዉ የኢራን ምጣኔ ሐብት ዘንድሮ እድገቱ ዜሮ ላይ ተገድቧል።የገንዘብ ግሽበት እስከ ሠላሳ ከመቶ ደርሷል።ሐሰን ሩኸኒም ሆኑ አምስቱ ተፎካካሪያቸዉ የአሕመዲነጃድ ቃል የበነነበትን፥በተደጋጋሚዉ ማዕቀብ የተጎዳዉን ሕዝብ ፍላጎት ጠንቅቀዉ ያዉቁታል።ሁሉም የሚያዉቁትን፥ የሚያዉቀዉ ሕዝብ በተለይ ወጣቱ በሚፈልገዉ መንገድ ለሕዝቡ በማድረስ ግን ሩሐኒን ያከለ የለም።   

ባአብዛኛዉ ከ1979ኙ እስላማዊ አብዮት ወዲሕ የተወለደዉ ወጣት ኢራናዊ የሚመኝና የሚፈልገዉን ለማድረግ ቃል-መግባታቸዉ የአብዛኛዉን ኢራናዊ ድምፅ ለማግኘት ጠቀማቸዉ።ተመረጡ።አሉም።

«ታላቁ፥ የተከበረዉ የኢራን ሕዝብ ለዚሕ ሐላፊነት ብቁነቴን ሥላረጋገጠለኝ ከፍተኛ ኩራት ይሰመኛል።ሐገሪቱን እንዳገለግል፥ የሕዝቡን ኑሮና ደሕንነት እንዳሻሽል፥ የሐገሪቱን ብሔራዊ ክብርና ጥቅም እንዳስጠብቅ ሐላፊነት ሰጥቶኛል።በዚሕ ጉዞ የናንነተ ድጋፍ በጣም እንደሚያስፈልገኝ ይሰመኛል።እንዳትለዩኝ እፈልጋለሁ፥ ትብብራችሁን እሻለሁ።»

ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች፥ ሩሐኒ በሚከተሉት የተሐድሶ ለዉጥ መርሕ ምክንያት በምርጫዉ ቢወዳደሩ እንኳን እንዳይመረጡ ተፅዕኖ ይደረግባቸዋል የሚል እምነት ነበራቸዉ።ደራሲ ባሕማን ኒሩማንድ፥ ሩሐኒ አይመረጡም ብለዉ ከሚያስቡት የኢራን ፖለቲካ አዋቂዎች አንዱ ናቸዉ።«አስደናቂ» አሉት የሩሐኒን ድል-ዛሬ።

«በጣም ነዉ የተገረምኩት።ከምርጫዉ በፊት የኢራን የበላይ ጠባቂ ምክር ቤት የኢራኑ ምርጫ ነፃ እንዲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ፈቅዷል ብዬ መናገር አለብኝ።ምንም አይነት መሰናክል አልነበረም፥ ምንም አይነት ማጭበርበር አልነበረም።እና በትክክል ፍፁም አብላጫዉ ድምፅ ለሩሐኒ ተስጥቷል ማለት ነዉ።በእዉነቱ በጣም ነዉ የተደነቅሁት።እንደሚመስለኝ ኢራንም ዉስጥ ሩሐኒ ያሸንፋሉ ብሎ የገመተ አይኖርም።»

በርግጥም ባሁኑ ምርጫ የድምፅ ማጭበርበር፥ ሐሜቱም መኖሩ አልተነገረም።በሁለት ሺሕ ዘጠኝ የታየዉ አይነት ወቀሳ፥ ትችት፥ የአደባባይ ሥልፍ ግጭትም የለም።ጥያቄዉ ሩሐኒ የሚጠበቁትን ያክል፥ መስራት ይችሉ ይሆን ወይ ነዉ?

ግላስኮ-ብሪታንያ ዩኒቨርስቲ የተማሩት፥ እንግሊዝኛዉን በስኮቶች ቅላፄ የሚናገሩት ሩኸኒ ለዘብተኛ የፖለቲካ አስተሳሰብና መርሕ እንዲከተሉ እንደ መምሕር ተፅዕኖ ያሳረፉባቸዉ መሐመድ ኻታሚ ናቸዉ። ሐታሚ በ1997 ሲመረጡ፥ ኢራን ከእስራኤልና ከምዕራባዉያን መንግሥታት ጋር የገጠመችዉን ዉዝግብ ለማስወገድ የሚረዱ፥ «ለዘብተኛ፥ ተራማጅ፥ ለዉጥ ፈላጊ» የሚል አድናቆት ሲንዥጎደጎድላቸዉ ነበር።

ከሐገር ዉስጥ ወግ አጥባቂዎቹ ፖለቲከኞች፥ ከዉጪ የዋሽግተን፥ ብራስልስ፥ ቴልአቪቭ መንግሥታት አጣብቀዉ እንደያዟቸዉ የሥምንት ዓመት ልፋት ድካማቸዉ የረባ ዉጤት ሳያመጣ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ አበቃ። አሁን የሩሐኒ ድል ማድረግ እንደተሰማ የቴሕራኖች ዋነኛ ጠላት የምትባለዉ ዩናይትድ ስቴትስ የምርጫዉን ዉጤት እንደምታከብር ቃል ገብታለች።

የቴሕራንን መሪዎች የሚቃወሙትን የአረብ ነገሥታት የምታስተባብረዉ ሳዑዲ አረቢያ ለተመራጩ የኢራን ፕሬዝዳት «የእንኳን ደስ ያለሕ» መልዕክት አስተላልፋለች።የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን እቅጩን ተናገሩ።
             
«የኢራንን ምርጫ በተመለከተ እኛ እስራኤላዉያን (ለዉጥ ያመጣል የሚል) ምንም አይነት ተስፋ የለንም።ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም በምኞት እሳቤ መጠመድ የለበትም።ኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብሯን እንድታቆም የሚያደርገዉን ጫናም ማለዘብ የለበትም።»

መጪዉን ለማየት ያብቃን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ።ለዛሬዉ ይብቃን።

ነጋሽ መሐመድ

Iran's Supreme Leader Ayatollah Ali Khamenei casts his ballot at his office during the Iranian presidential election in central Tehran June 14, 2013. Iranians voted for a new president on Friday urged by Khamenei to turn out in force to discredit suggestions by arch foe the United States that the election would be unfair. REUTERS/Fars News/Hassan Mousavi (IRAN - Tags: POLITICS ELECTIONS TPX IMAGES OF THE DAY) ATTENTION EDITORS - THIS IMAGE WAS PROVIDED BY A THIRD PARTY. FOR EDITORIAL USE ONLY. NOT FOR SALE FOR MARKETING OR ADVERTISING CAMPAIGNS. THIS PICTURE IS DISTRIBUTED EXACTLY AS RECEIVED BY REUTERS, AS A SERVICE TO CLIENTS
ላዕላይ መሪ ዓሊ ኻማኒምስል REUTERS/Fars News
Said Jalili, Ali Akbar Velaiati, Mohammad baghe Ghalibaf, Mohsen Rezai, Hasan Rohani, Mohammad Gharazi
ሥድስቱ ዕጩዎች
Stichwort: Ahmadinedschad, Iran, Azadi Stadion Beschreibung: Mahmoud Ahmadinedschad bei einer Versammlung am 18.04.13 in Azadi-Stadion. Quelle: Isna Lizenz: Frei Zulieferer: Samira Nikaeen
አሕመዲነጃድምስል Isna
Iran Wahl 2013 Rechteeinräumung: Lizenzfrei, Fotograf ist im Iran. Er will seinen Namen nicht veröffentlichen, weil es gefährlich ist. Quelle: DW, zugeliefert von Hossein Kermani ***Wegen der niedrigen Qualität darf das Bild nicht als Karusselteaser oder Artikelbild verwendet werden***
መራጩ ሕዝብምስል DW

አርያም ተክሌ

 

















 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ