1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢሬቻ ወጣቶች የተቃውሞ መፈክሮች አሰምተዋል

እሑድ፣ መስከረም 21 2010

የኢሬቻ በዓል ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ በሆራ አርሰዲ ሀይቅ በሰላም ተከብሯል። ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ክብረ በዓል ወቅት በደረሰ አደጋ በርካቶች መሞታቸውን ተከትሎ በከተማይቱ ስጋት አንዣብቦ ነበር። በዓሉን በስፍራው የተከታተለው ዘጋቢያችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር ኢሬቻ ያለምንም የጸጥታ ችግር መከበሩን ገልጾልናል።

https://p.dw.com/p/2l33v
Äthiopien Irreecha Feierlichkeiten
ምስል DW/Y. Gebregzihabher

የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው "የኢሬቻ በዓል አከባበር በሰላም ተጠናቋል" ሲሉ በዘንድሮው በዓል ችግር እንዳልነበር አስታውቀዋል። የበዓሉን ተሳታፊም አመስግነዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች ወደ ሆራ አርሰዲ ሀይቅ መትመም የጀመሩት ከለሊቱ 9.30 ሰአት ጀምሮ ነበር። በቢሾፍቱ ጠዋት ኃይለኛ ዝናብ ቢጥልም ወደ ሆራ ሃይቅ የሚጎርፈውን ህዝብ አላገደውም። ወደ በዓሉ ስፍራ በሚወስደው መንገድ ላይ የክልሉ ፖሊሶች እና ጸጥታ ለማስጠበቅ የተሰማሩ ወጣቶች ታዳሚዎችን እየፈተሹ ሲያሳልፉ ነበር። ወደ ሆራ ሀይቅ ከሚወስደው አደባባይ እስከ መከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ድረስ በየጥጉ የክልሉን ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ የጸጥታ ኃይሎች ጥይት እና አስለቃሽ ጭስ የሚተኩሱ መሳሪያዎች ታጥቀው በተጠንቀቅ ሲጠብቁ ዘጋቢያችን ተመልክቷል።

Äthiopien Irreecha Feierlichkeiten
ምስል DW/Y. Gebregzihabher

በዝግጅቱ ላይ ቀደም ሲል ቃል እንደተገባው በባለስልጣናትም ሆነ በሌላ ወገን ንግግሮች አልተደረጉም። በአባ ገዳዎች የተደረገው የምርቃት ስነ ስርዓትም በቀደምት ዓመታት ከነበረው አጠር ያለ ነበር። በክብረ በዓሉ ላይ ፖለቲካዊ መልዕክቶች በክልሉ አሊያም በፌደራል መንግስት በኩል አይተላለፉ እንጂ በበዓሉ ስፍራ የነበሩ ወጣቶች በከፍተኛ ድምጽ የተቃውሞ መፈክሮች አሰምተዋል። ከመፈክሮቻቸው ውስጥ "ዶ/ር መረራ፣ በቀለ ገርባ ይፈቱ" ፣ "ኦሮሞዎችን መግደል ይቁም" የሚሉ ይገኙበታል። "ጭቆና በቃን፣ ለኦሮሞዎች ከሶማሌ ክልል መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ለፍርድ ይቅረቡ፣ ነፃነት ለኦሮሚያ" የሚሉም ነበሩበት።

የበዓሉ ታዳሚ ወጣቶች ተቃውሟቸውን በመፈክር እና በዘፈን ከማሰማታቸው ባሻገር ባለፈው ዓመት ህይወታቸውን ያጡ ዜጎችን ለማስታወስ ተንበርክከው፣ እጃቸውን በ"X" ምልክት በማጣመር አሳይተዋል። በስፍራው የነበሩ የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች ተቃውሞውን በዝምታ አልፈውታል። ጸጥታ ለማስጠበቅ ከተሰማሩ ወጣቶች ጋር በመሆንም ሁኔታውን ለማረጋጋት እና በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ በድምጽ ማጉያ መልዕክት ሲያስተላልፉ ታይተዋል። "በዓሉን የሰላም ያድርግልን፣ ግጭት ለማንም አይጠቅምም" ሲሉ ተደምጠዋል።

ተቃውሞቸውን ሲያሰሙ ከነበሩት ውስጥ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው "በሀገራችን ስደተኛ ሆንን፣ እንደ ሁለተኛ ዜጋ እየታየን ነው፣ ጭቆና መሮናል" ብለዋል። በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እንዲወርድ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል። 

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር / ተስፋለም ወልደየስ

እሸቴ በቀለ