1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢስማይል መስዋት/ኢድ አልአዳ

እሑድ፣ ኅዳር 20 2002

ዘንድሮ ለ1430ኛ ግዜ የተከበረዉ የኢድ አልአዳ በአል በአለም በሚገኙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በከፍተኛ ድምቀት ተከብሮአል። ጀርመናዉያን በቋንቋቸዉ Das islamische Opferfest የሚሉት የኢድ አላዳህ በአል፣ ለአማኞች በአሉ ዋንኛ መሆኑን እና መስዋእት የሚሰጡበት ቀንም እንደሆነ ጽፈዋል።

https://p.dw.com/p/Kk8c
ምስል picture-alliance/dpa

ኢድ አልአዳ በአል ምን ይሆን ባህላዊ አከባበሩ ወጉን እንዲጫዉቱን አንድ የሃይማኖት አባት ጋብዘናል።
የኢድ አልአዳ በአል በጀርመን አገር በሚገኙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮአል። ኢድ አላዳህ የእርድ ቀን ነዉ። በጀርመን ለብዙ ግዜ የእንስሳትን ሁኔታ ለመጠበቅ ሲባል ማረድ በህግ የተከለከለ ሆኖ ለብዙ አመታት ቆይት የዛሪ ሶስት አመት ህጉ የተለያዩ ሁኔታዎች እንዲሟላ በመጠየቅ የማረድ ፈቃድ እንዲሰጥ መደረጉ ተጠቅሶአል። ይኸዉም ከመንግስት ፈቃድ ወስዶ የትኛዉ ከብትን ማረድ እንደሚፈልግ ተናግሮ አራጅም ሆነ ገፋፊ እንዳለ አስታዉቆ ፈቃድ እንደሚሰጥ ዘገባዉ ይጠቁማል። ይህ የረቀቀ ህግ እንዲወጣ የሆነዉ ይላል ዘገባዉ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን ለመቆጣተር እና የእንስሶችን ህይወት ለመጠበቅ እንደሆነ ተገልጾአል። በአገራችን የኢድ አልአዳ አከባበር እንዴት ነዉ? የኢድ አልአዳ በአልስ መነሻዉ ምን ይሆን? በአዲስ አበባ ከተማ ሳሪስ አቦ ቤተስኪያን አካባቢ የሚገኘዉ የሳሊህ መስጊድ ዋና ኢማም የሆኑት ሃጂ ሞሃመድ አደም ይገልጹልናል።
ኢማም ሃጂ ሞሃመድ አደም ኢድ አመጣቱ ይላሉ « አባታችን ነብዩ ኢብራሂም ትእዛዝ አይታዘዝም ለኔ በማለት ኢስማይል የሚባለዉን ልጃቸዉን እረድ አለና ሊፈትናቸዉ አዘዛቸዉ ከመካ ወጣ ብሉ ሚና የሚባል ቦታ ላይ አሉዝቢላሂ እያሉ ድንጋይ እየወረወሩ ሰባት ቀን ከቆዩ በኻላ በስምንተኛዉ ቀን ትክክለኛ መሆኑን አዉቀዉ ልጃቸዉን ሲጠይቁት፣ አባቴ ከአላህ ትእዛዝ ከሆነ የሱን ትእዛዝ የማትፈጽምበት ጉዳይ የለህም የታዘዘከዉን መፈጸም አለብህ አላቸዉ። ነብዩ ኢብራሂምም እርዱን ሊፈጽሙ ሲዘጋጁ ቢላዉን ልጃቸዉ አንገት ላይ አድርገዉ ሊያርዱ ሲዘጋጁ አላህ ስለታዘዝክ ብሎ ከሰማይ አርባ አመት የተቀለበ ሙክት በግ በጅብሪል በኩል አወረደላቸዉ፣ ያንን አይቶ ሊታረድ የቀረበዉ ኢስማኤል አሉሃክበር አለ፣ ነብዩ ኢብራሂምም ቀና ብለዉ አዩ፣ ከዝያን ግዜ ጀምሮ በዚህ ቀን በግን በማረድ የዚህ ቀን መታሰብያ ሆኖ ቀረ» ሲሉ ኢማም ጃጂ ሞሃመድ አደም ይገልጻሉ።
በህጅሪ አቆጣጠር 1430ኛዉ በአል መከበሩ ተገልጾአል፣ ይህ አቆጣጠር ከየት መጣ ለሚለዉ ጥያቄ ኢማም ሃጂ ሞሃመድ አደም ሲመልሱ «በቀድሞ ግዜ ይላሉ የቀን አቆጣተር የአንድ ነገር ክስተትን ተከትሎ ወይም አስታኮ ነበር የሚወሳዉ። ይህም ነብዩ መሃመድ ከመጡ በኻላ አርባ አመት ነብይ ሳይሆኑ ከአርባ አመት በኻላ በመካ ለአስራ ሶስት አመታት ነብይ ሆነዉ የእስልምና ሃይማኖትን ሲያስተምሩ፣ የሃይማኖቱ ተከታዮች አልቀበል ብለዋቸዉ፣ አላህ ከአስራ ሶስት አመት በኻላ፣ ከመካ ተነስተህ ወደ መዲና መሄድ አለብህ ብሎ ከአላህ ትእዛዝ ከደረሳቸዉ ወዲህ ወደ መዲና የሄዱበት ሁኔታ ህጅሪ ይባላል» «ህጅሪ ማለት መሰደድ ማለት ነዉ» ሲሉ ይገልጻሉ። «ከዝያን ግዜ ጀምሮ ነዉ አመታቱ ተቆጥረዉ ዛሪ 1430ኛዉን ክብረ በአል የምናስበዉ ሲሉ ያስረዳሉ» ነብዩ መሃመድ በመዲና በርካታ ተከታዮችን ያገኙበት እስልምና በትክክል ማስተማር የቻሉበት ሁኔታ ነበር።

Opferlämmer
ምስል UNI

በአገራችን የኢድ አላዳህ በአል አከባበር ምን ይመስላል? ላልናቸዉ በአገራችን ይላሉ ኢማም ሃጂ ሞሃመድ አደም የኛ አገር ህዝብ በባህሉ ይዋደዳል፣ ይፋቀራል፣ እስልናዉም በአጋጣሚ ይህን እድል የታደለ ስለሆነ የሚዋደድ፣ የሚፋቀር፣ ደሃን የሚረዳ፣ የታረዘን የሚያለብስ ስለሆነ፣ እስልምና እና ባህሉ ተጣጥሞ ሲሄድ ይታያል። በዚህ በአል እለት የታረደዉ፣ ማረድ ለማይችሉ ለዛዉንቶች ለችግረኞች ቤተሰብ ለሌላቸዉ ረዳት ለሌላቸዉ እንዲሰጥ የሚል ነዉ። እንደሚታወቀዉም ባህላችን በዚህ የተዋበ በመሆኑ ከሃይማኖቱ ጋር ተጣጥሞ እና ተዛምዶ እየሄደ ያለ ነዉ ሲሉ ይገልጻሉ። መልካም የተቀደሰ በአል ይሁንልን፣ አመት አመት ያድርሰን!


አዜብ ታደሰ