1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢቦላ መከላከያ ክትባት ተስፋ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 13 2007

ክትባቶቹን ለማምረትና ለማሰራጨት የሚያስፈልገዉን በቢሊዮን የሚቆጠር ወጪ ያስፈልጋል።ወጪዉን የሚሽፍነዉ ወገን እስካሁን በግልፅ አልታወቀም።ጥረቱ በብዙዎች እምነት የዘገየ ያም ሆኖ ገዳዩን በሽታ ድል ለማድረግ ተስፋ ሰጪ ነዉ።ተስፋዉ ግን የዓለም ጤና ድርጅት ባለሥልጣን እንደሚሉት አሁንም በብዙ ጥያቄዎች የተከበበ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1DayZ
ምስል Getty Images

የኢቦላ ተሕዋሲን ስርጭት የሚገታ ክትባት ለማግኘት የሚደረገዉ ጥናትና ምርምር ተስፋ ሰጪ ምልክት ማሳየቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) እንዳስታወቀዉ የተለያዩ መድሐኒት አምራች ኩባንዮች ገዳዩን ተሕዋሲ ይከላከላሉ የተባሉ ክትባቶችን እየሞከሩ ነዉ።ወይም ለመሞከር ተዘጋጅተዋል።የድርጅቱ የሕክምና ጉዳይ ምክትል ሐላፊ ዶክተር ማሪ ፓዉለ ኬኔይ እንደሚሉት ክትባቶቹ እስከመጪዉ ታሕሳስ ማብቂያ ድረስ ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ በሰዉ ላይ ይሞከራሉ።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ

የመድሐኒት ኩባንዮች-ጠቀም ያለ ገንዘብ ለማጋበስ፤ሥም ዝና በመሸመት ይሁን የመንግሥታትና የድርጅቶችን ፍላጎት ለማርካት፤ መድሐኒት ለማግኝት እየተራኮቱ፤ እርስ በርስ እየተሻኮቱ እየተሽቀዳደሙም ነዉ።ገዳዩ ተሕዋሲ ከአፍሪቃ አልፎ የአዉሮጳና የዩናይትድ ስቴትስን በሮችን ማንኳኳቱ ደግሞ በሐያላኑ መንግሥታትና ድርጅቶች ዘንድ በፍራት-ላይ ድንጋጤን፤ በጥያቄ ላይ ጫናን አሳድሯል።

መንግሥታቱና ድርጅቶቹ በፋንታቸዉ መድሐኒት አምራቾችን በማጓጓትም፤በማግባባት-በመጫንም ከሚፈለገዉ ለመድረስ እያሮጧቸዉ ነዉ። ተሕዋሲዉን የሚገታ ክትባት ለማግኘት ለሚደረገዉ ምርምር ሁለት መቶ ሚሊዮን ዶላር የመደበዉ የዩናይትድ ስቴትሱ ጆንሰንና ጆንሰን ኩባንያ በሩጫዉ የመጀመሪያዉን ደረጃ የያዘ መስሏል።GSK የሚባለዉ የብሪታንያ ኩባንያ እና አንድ የፈረንሳይ ኩባንያም ሲሆን ለመቅደም ካልሆነም ዉጤት ለመጋራት እየተፎካከሩ ነዉ።ሌሎችም አሉ።ዉድድሩን በቅርብ የሚከታተለዉ የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀዉ ኩባንዮች እስካሁን የምርምር ዉጤታቸዉን በየ ቤተ-ሙከራዉ እየፈተሹ፤ አለያም ለመሞከር ተዘጋጅተዋል።የድርጅቱ የሕክምና ጉዳይ ምክትል ሐላፊ ዶክተር ማሪ ፓዉለ ኪኔይ እንደሚሉት ክትባቱን በሽታዉ ባየለበት ምዕራብ አፍሪቃ ለመመኮርም ዝግጅቶችና ስምምነት ተደረገዋል።

Symbolbild - Ebola Virus
ምስል picture-alliance/dpa

«ክትባቱንና ክትባቱ የሚመኮርባቸዉን ሁኔታዎች በተመለከተ ከሠወስቱ ሐገራት ጋር የትብብር ሥምምነት የማድረጉ ጥረት ቀጥሏል።የደም ንጥረ-ነገር በጥንቃቄ ተሰብስቦ ክትባቱ በተሕዋሲዉ የተለከፉ ሰዎችን መርዳት አለመርዳቱ ይሞከራል።»

የአሜሪካዉ ጆንሰንና ጆንሰን ኩባንያ በሁለት ደረጃ እንዲስጥ ላሰበዉ ክትባት እስከ ታሕሳስ ማብቂያ ድረስ ለአንድ ሚሊዮን ሰዎች የሚሰጥ ምጥን-ክትባት ማዘጋጀቱን አስታዉቋል።ኩባንያዉ ከብሪታንያዉ ተፎካካሪዉ ከGSK ጋር ክትባቱን በጋራ ለማምረትና ለመሞከር እየተደራደረ ነዉ።

የዓለም ጤና ድርጅት ባለስልጣን ዶከተር ኪኔይ እንደሚሉት በድርጅታቸዉ አስተባባሪነት ክትባቶቹን ከሰዉ በሚወሰድ የደም ንጥረ ነገር ወይም በኢቦላ ተሕዋሲ በተለከፉ ሰዎች ላይ ለመሞከር ከሰወስቱ የአፍሪቃ ሐገራት ላይቤሪያ ቀዳሚዉን ሥፍራ ይዛለች ።

«ሥምምነቱን በማድረጉ ሒደት ላይቤሪያ ፈጠን ብላለች።በሚቀጥሉት ሳምንታት ደም መሰብሰና ለሙከራ ማዘጋጀት ይጀመራል የሚል ተስፋ አለን።ከሴራሊዮንና ከጊኒም ጋር ሥምምነት ለማድረግ ዉይይቱ ቀጥሏል።ጊኒ ዉስጥ ሙከራዉን ለማድረግ የሚረዳዉን ስምምነት የሚመራዉ ኢታቢስሞስ ፍራንሴ የተሰኘዉ የፈረንሳይ ተቋም ነዉ።»

ክትባቶቹን ለማምረትና ለማሰራጨት የሚያስፈልገዉን በቢሊዮን የሚቆጠር ወጪ ያስፈልጋል።ወጪዉን የሚሽፍነዉ ወገን እስካሁን በግልፅ አልታወቀም።ጥረቱ በብዙዎች እምነት የዘገየ ያም ሆኖ ገዳዩን በሽታ ድል ለማድረግ ተስፋ ሰጪ ነዉ።ተስፋዉ ግን የዓለም ጤና ድርጅት ባለሥልጣን እንደሚሉት አሁንም በብዙ ጥያቄዎች የተከበበ ነዉ።

Ebola Impfung in Mali
ምስል picture-alliance/dpa/Alex Duval Smith

«ብዙ ጥያቄዎች ገና አልተመለሱም።አሁን ባለንበት ደረጃ ክትባቶቹ አደጋ ላላማስከተላቸዉ ምንም ማረጋገጪያ የለንም።ጠቃሚነታቸዉንም አናዉቅም።ቢጠቅሙ እንኳን ምን ያሕል ዉጤታማ እንደሆኑ አናዉቅም።መቶበመቶ በሽታዉን ይከላከላሉ?-ይሕ የመሆኑ እድልም ብዙ አልተለመደም።»

ኢቦላ በተለይ በሰወስቱ የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት በሰባት ወር እድሜ አራት ሺሕ ስድስት መቶ ሰዉ ገድላል። ከአስር ሺሕ በላይ ለክፏል።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ