1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢቦላ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገዉ ጥረት

ሰኞ፣ ሐምሌ 28 2006

ከበርካታ አፍሪቃ ሃገራት ተጓዦችን በአየር መንገዷ የምታስተናግደው ምሥራቅ አፍሪቃዊቷ ሀገር ኢትዮጵያ እንዲሁም ወረርሽኙ ጉዳት ካደረሰባቸዉ ካሃገራት ብዙም ሳትርቅ የምትገኘው ጊኒ ቢሳው የኤቦላ ወረርሽኝ ወደየሀገራቸው እንዳይገባ ምን እያደረጉ ይሆን?

https://p.dw.com/p/1Cokc
Ebola Westafrika Liberia
ምስል Reuters

የኤቦላ ተሕዋሲ የሚያደርሰዉን ጉዳት ለመቀነስ የሴራሊዮን ፕሬዚዳንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲያዉጁ የላይቤሪያዋ ፕሬዚዳንት ደግሞ መሥሪያ ቤቶችን በመዝጋት የመድሃኒት መርጨት ተግባራት እንዲከናወኑ አድርገዋል። ተሕዋሲዉ አሁን ተጎጂ የሆኑትን የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ብቻ ሳይሆን መላው አፍሪቃን ብሎም ዓለምን ስጋት ላይ የጣለ ሆኗል።

በአራት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት 826 ሰዎችን ለህልፈተ ሕይወት የዳረገው የኤቦላ ተህዋሲ በታሪክ እንዲህ ያለ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ አያውቅም። ተህዋሲው ወደ ሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት እና አህጉሮች ስለአለመሠራጨቱ ብዙም ርግጠኛ መሆን አይቻልም። ለምሳሌ በምዕራብ አፍሪቃ የምትገኘው ጊኒ ቢሳው ዉስጥ እስካሁን በበሽታው የተያዘ ሰው አልተመዘገበም። ይሁንና ብዙም ሳይርቅ በጎረቤት ሀገር ጊኒ-ኮናክሪ ድንበር ላይ በምትገኝ መንደር አንድ ሰው መሞቱ ተሰምቷል። እናም ጊኒ ቢሳው ቅድመ ዝግጅት መጀመሯን የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት በምህፃሩ UNICEF ተጠሪ አቡባክር ሱልጣን ይናገራሉ።« ጊኒ ቢሳውን በሚያዋስነው የጊኒ ኮናክሪ ድንበር አካባቢ በተሕዋሲዉ ሕወቱን ያጣ አንድ ሰለባ በመኖሩ አካባቢዉ ይህ የሚያሰጋዉ ስፍራ ሆኗል ማለት ይቻላል። በጎረቤት ሃገራት የሚሆነዉን ስንመለከት ደግሞ ስጋት እንዲገባን የሚያደርጉ በቂ ምክንያቶች አሉን። ኅብረተሰቡን የመከላከሉ ተግባር ቀላል አይደለም። አስተሳሰብ እና ልምዳችንንም መቀየር ወሳኝ ነው። ለዚህም የመገናኛ ብዙኃን እንዲተባበሩን ጥሪ እናደርጋለን። »

Ebola Westafrika Liberia Monrovia
ምስል Reuters

እጅ ለእጅ በመጨባበጥ ሰላምታ በሚሰጥባቸዉ ሃገራት አንድን ሰው እጅ መንሳት መናቅ ቢያስመስልም ተሕዋሲዉ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ ሚና እንደሚጫወት የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ። አቡ በክር ሱልጣን እንደሚሉት ልምዶችን ከመቀየር ባሻገር በኤቦላ ተህዋሲ የሚሞቱ ሰዎች በአንድ አካባቢ ቢቀበሩ አደጋውን ይቀንሳል።

በምዕራብ አፍሪቃ በኤቦላ በሽታ የሚሞተው ሰው ቁጥር ያሳሰባቸው የጊኒ ቢሳው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶሚኒጎስ ሲሞስ ፔሪራም እንዲሁ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል። ይህም ስለተሕዋሲዉ የግንዛቤ ማብራሪያ ለማግኘት ብቻ ሳይሆን የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍንም የሚጨምር ነው።«ዓለም ዓቀፉን ማህበረሰብ በምዕራብ አፍሪቃ ያለውን የኤቦላ ወረርሽኝ በአደጋ ጊዜ ለመዋጋት የሚያስችል የሕክምና ቁሳቁስ እንዲያቀርብልን ጠይቀናል። የፖርቱጋል መንግሥት በቀጣይ ቀናት እዚህ የሚደርስ 15 ቶን የሕክምና ግብዓት ሊሰጠን ፈቅዷል።»

Ebola Westafrika Guinea
ምስል Getty Images/Afp/Seyllou

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚበርበት የምዕራብ አፍሪቃ መዳረሻዎች መካከል ዛሬ በኤቦላ ተሕዋሲ ስጋት ላይ የወደቁት ጊኒ እና ናይጄሪያ ይገኙበታል። በጊኒ 339 ሰዎች ሲሞቱ ዜግነቱ ላይቤሪያዊ የሆነ አንድ በሽተኛ ደግሞ ወደሌላ ሀገር በመጓዝ ላይ ሳለ ናይጄሪያ ውስጥ በዚሁ ምክንያት ሕይወቱ አልፏል። ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ የሚጓዙ ሰዎች እስካሉ ድረስ በሽታው ኢትዮጵያም የማይደርስበት ምንም ምክንያት የለም። ስለሆነም ሀገሪቱ የተሕዋሲዉን መዛመት ለመከላከል ምን ዓይነት ቅድመ ዝግጅት እየወሰደች ነው? የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ተቋም የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አቤል የሻነህ ስለሚደረገዉ ጥንቃቄ ጠይቀናቸው መልስ ሰጥተውናል።

ኢትዮጵያ እና ጊኒ ቢሳው የኤቦላ ወረርሽኝ ወደየሀገራቸው እንዳይገባ የሚያደርጉት ከድምፅ ዘገባው ያገኙታል።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ