1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮዽያና የግብጽ ፍጥጫ

ረቡዕ፣ ኅዳር 15 2003

የኢትዮዽያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ግብጽ በአባይ ጉዳይ ጦርነት ብትገጥም ኢትዮዽያን አታሸንፍም ሲሉ ትላንት አስታወቁ።ግብጽ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን መግለጪያ አስገራሚ ብላዋለች።

https://p.dw.com/p/QH1o
ጠ/ሚር መለስ ዜናዊምስል AP

የሀገር አድባር የአገር ሲሳይ እየተባለ የተዜመለት አባይ ለኢትዮዽያ ጦርነትን ያመጣባት ይሆን? ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ትላንት አባይንና ጦርነትን አንድ ላይ አንስተዋል። አንስተውም ግብጽ እንዳትሞክረው አስጠንቅቀዋል። ለሮይተርስ የዜና ወኪል ቃለመጠይቅ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ትላንት ያስተላለፉት ማስጠንቀቂያ በእርግጥ ከወትሮው ጠንከር ከረር ያለ ነው። ግብጽ ድንገት ተነስታ ትወረናለች ብዬ አልሰጋም። ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሞከረችም ታሪካችን እንሚያሳየው እሷም ተመሳሳይ ዕጣ ይገጥማታል እንደ ማስጠንቀቂያም። እንደ ስጋትም። በዚህን ወቅት ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን መሰል መግለጪያ መሰማቱ ለምን አልናቸው የምስራቅ አፍሪካውን የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ዩሱፍ ያሲንን።

ጠቅላይ ስትር መለስ ዜናዊ ግብጽን ኢትዮዽያን ለማተራመስ ታሴራለችም ሲሉ ከሰዋል። የተለያዩ አማጺያንን በመደገፍ ኢትዮዽያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋቱ እንዲደፈረስ ታደርጋለችም ነበር ያሉት ትላንትና። ለፖለቲካው ተንታኝ አቶ ዩሱፍ ያሲን ግብጽ ኢትዮዽያን የሚወጉ አማጺያንን ትደግፋለች መባሉን እንዴት አዩት ላልናቸው ሲመልሱ

የአባይ ወንዝ ጉዳይ ግብጽንና ኢትዮዽያን አፋጧል። የተፋሰሱ ዘጠኝ ሀገራት ለሁለት ተከፍለዋል። ኢትዮዽያ አምስት ሀገራትን ይዛ አዲሱ ስምምነት ወደ ተግባር እንዲቀየር ጫና እየፈጠረች ነው። ግብጽና ሱዳን አሮጌው የቅኝ ግዛት ስምምነቱ አንዳለ እንዲቆይ ይፈልጋሉ። ቡሩንዲና ዲሞክራቲክ ኮንጎ እስከአሁን በአዲሱ ስምምነት ላይ ፊርማቸውን ከማኖር ተቆጥበዋል። በኢትዮዽያ ቀዳሚነት የተሰለፉት ስድስቱ የአዲሱ ስምምነት ፈራሚዎች ላልፈረሙት የአንድ ዓመት የጊዜ ገደብ ሰጥተዋቸዋል። ገደቡ በመጪው ግንቦት ወር ላይ ያበቃል። ኢትዮዽያ የአንድ ዓመቱ ገደብ ግማሽ ያህል ጊዜ ሲቀረው ነው እንግዲህ ጦርነት ከመጣም እመክታለሁ እያለች ያለችው። የግብጽ ባለስልጣናት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን የትላንቱን መግለጪያ አስገራሚ ብለውታል። አቶ ዩሱፍ ያሲን

የአባይ ወንዝ በዓመት 84 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ያፈሳል። ከዚህ ውስጥ ግብጽ በበላይነት 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትሩ ወደ እሷ ሆኗል። ኢትዮዽያ የአባይ ወንዝ 85 በመቶው ገባር ሆና ግን የምታገኘው ድርሻ ግን በጣም አናሳ ነው። አዲሱ ስምምነት ድርሻዋን ስለሚያሰፋ አጥብቃ እየተሟገተች ነው። ከግብጽ የገጠማት ፈተና በእርግጥ ወደ ጦርነት ያመራ ይሆን? ብዙዎች ጥያቄውን ያነሳሉ። የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ተንታኝ አቶ የሱፍ ያሲን ግን ጦርነት የማይታሰብ ነው ይላሉ።