1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያዉያን ስቃይ በግብፅ

ዓርብ፣ ግንቦት 25 2009

በግብፅ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ስቃይ ላይ ነን ሲሉ ጥሪ አቀረቡ። ስደተኞቹ ለዶይቼ ቬለ ባስተላፉት መልዕክት እንደገለፁት በሽዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ታስረዋል። ካይሮ ለሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አሳዉቀን ነበር፤ በባህር ለማለፍ የፈለጋችሁ ናችሁ፤ ምንም ዓይነት ወረቀት የላችሁም ብለዉ የፈየዱልን ነገር የለም ሲሉም ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/2e2QO
IOM warnt vor neuer Flüchtlingswelle Fischerboote im Hafen von Alexandria
ምስል DW/T.Rollins

Unterwegs nach Europa_äthiopische Illegale Flüchtlinge leiden in Alexandria_MMT - MP3-Stereo

 

ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በሕገ ወጥ አመላላሽ ግብጻዉያን ገንዘባቸዉ ተወስዶ አሁንም ገንዘብ ካላመጣችሁ ወደምትፈልጉበት አትሄዱም ተብለዉ በአንድ ቤት ታጉረዉ ነዉ የሚገኙት። የሚጠጣ ዉኃና የሚበላ ምግብ እንኳን አጥተን በስቃይ ላይ ነን የሚሉት ኢትዮጵያዉያኑ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሊረዳን አልቻለም ብለዋል።   

ኢትዮጵያዉያኑ በደላሎች ከግብጽ መዲና ካይሮ ወደ አሌክሳንድርያ ለመሻገር ችለን ነበር ይላሉ። አሌክሳንድርያ ከመጣን በኋላ ደግሞ ግብፃዉያን  ወደ አዉሮጳ በመርከብ እንድንጓዝ ከእያንዳንዳንችን 2000 ዶላር ተቀብለዉን ከዛሬ ነገ እንሄዳለን ብለን ስንጠብቅ ወራቶች አለፈን ። አሁን ደግሞ ሌላ ብር ካላመጣችሁ አትሄዱም እያሉን ነዉ ብለዋል። የድረሱልን ጥሪ ከአሌክሳንድርያ ግብፅ በስልክ ያስተላለፉት ኢትዮጵያዊ  ለደህንነታቸዉ ሲሉ ስማቸዉ እንዲገለጽ አልፈለጉም።   

ካይሮ ለሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አሳዉቀን ነበር፤ በባህር ለማለፍ የፈለጋችሁ ናችሁ፤ ምንም ዓይነት ወረቀት የላችሁም ብለዉ የፈየዱልን ነገር የለም ሲሉ ኢትዮጵያዊትዋ ተናግረዋል።  በርካታ ኢትዮጵያዉያን በእስር ቤት ይገኛሉ፤ እዚህ ያለዉ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ሊተባበረን ስላልቻለ፤ መንግስት ስሞታችንን ሰምቶ ወደ ሃገራችን ይመልሰን ያለን ሌላዉ ለደላሎች ሁለት ሺህ ዶላር የከፈለ ኢትዮጵያዊ  ነዉ። ስለጉዳዩ በካይሮ የኢትዮጵያ ኤምባሲን ሃላፊዎች ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ