1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያዉያን ስደት ወደ ደቡብ አፍሪቃ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 28 2007

ከተለያዩ የሃገራት ወደ አዉሮጳ የሚፈልሰዉ ስደተኛ እጅግ በጨመረበት በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚሰደዱ አፍሪቃዉያን ቁጥርም ጨምሯል። በሳምንቱ መጀመርያ ወደ 100 የሚጠጉ ኢትዮጵያን በአንድ የጭነት ማመላለሻ ታጭቀዉ ወደ ደቡብ አፍሪቃ በማምራት ላይ ሳሉ በዛምቢያ ፖሊስ መያዛቸዉ ተዘግበዋል።

https://p.dw.com/p/1GQm0
Xenophobie in Südafrika
ምስል Reuters/R. Ward

[No title]


የተለያዩ ሃገራትን አቋርጠዉ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ከሚያመሩ ኢትዮጵያዉያን አብዛኞቹ በየአፍሪቃ ሃገራቱ ወህኒዎች ያለ ተመልካች ታስረዉ እንደሚገኙ ነዉ የተሰማዉ። ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ድርጅት እንደሚለዉ ከሆነ ደግሞ ከእስር፣ በአዉሬ ከመበላት አልያም በቪክቶሪያ ሐይቅ የዉኃ ሲሳይ ከመሆን ተርፈዉ ደቡብ አፍሪቃ የገቡትም ቢሆኑ በስቃይ ዉስጥ ነዉ የሚኖሩት።

Südafrika Johannesburg Ausländer Rassismus Übergriffe Flüchtlinge
ምስል AFP/Getty Images/M. Longari


ሥራና ጥሩ ኑሮ የሚገኝባት ሀገር ናት ብለዉ ኢትዮጵያዉያንም ሆኑ ሌሎች አፍሪቃዉያን በሕገ-ወጥ ሰዉ አመላላሾች፤ በመታለል ያላቸዉን ገንዘብ በሙሉ በመስጠት ነዉ ደቡብ አፍሪቃ ለመግባት ሙከራ የሚያደርጉት። ስለደቡብ አፍሪቃ ሕይወት የሚሰበከዉ ሀገሪቱ ዉስጥ ካለዉ ሁኔታ ጋር በምንም የተገናኘ አይደለም ያሉን በደቡብ አፍሪቃ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ዋና ፀሐፊ አቶ ደረጀ መኮንን፤
« ደቡብ አፍሪቃ ከመጣሁ 18 ዓመት ሆነኝ ለአብዛኛዉ ወገኖቻችን የሚሰበከዉ ነገርና እዚህ አገር ያለዉ እዉነታ የተለያየ ነዉ። ደቡብ አፍሪቃ መጥተዉ ወርቅ የሚታፈስ አልማዝ የሚገኝ ተደርጎ እየተሰበከ አብዛኛዉ ወጣት ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመሰደድ ይዳረጋል። ሆlም ግን እዚህ ያለዉ እዉነታ ፈፅሞ የተለየ እና እዚህ አገር ያሉ በርካታ ኢትዮጵያዉያን እንዴት አድርጌ ነዉ ወደ ሀገሪ የምመለሰዉ ብለዉ ግራ የገባቸዉ አሉ። ለምሳሌ በደቡብ አፍሪቃ የጎዳና ተዳዳሪ ኢትዮጵያዊ አለ የእዕምሮ ህመም የደረሰባቸዉ ወገኖችም አሉ። እና የሚወራዉ ወሪ ሁሉ አንድ አይነት አይደለም። እንደዉም ኑሮዉ በፊት ትንሽ ይሻል ነበር። አሁን ግን ከስደተኛዉ መብዛት የተነሳ አንድኛ የሀገሪዉ ሰዉ ስደተኛ እየጠላ ነዉ ሁለተኛ በሀገሪቱ ሰርቶ ለመኖር አዳጋች ሆንዋል።»


አቶ ደረጀ መኮንን እንደሚሉት ኢትዮጵያዉያኑ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመሻገር ለሕገ-ገወጥ አመላላሾች ምን ያህል ብር እንደሚሰጥዋቸዉ በርግጥ አይታወቅም። ሆኖም ግን ከኢትዮጵያ ተነስቶ ደቡብ አፍሪቃ እገባለሁ የሚል ኬንያ፤ ታንዛንያ፤ ዚምባቡዌና ሞዛንቢክ ዉስጥ እንደሰንሰለት ተቀጣጥለዉ በሚገኙት ሕገ ወጥ አመላላሾች ምክንያት በየሀገራቱ እስር ቤቶች የታጎረዉ፤ ጥቃት የደረሰበት፤ በአዉሬ የተበላ ብሎም የቪክቶርያ ኃይቅ ሲሳይ የሆነዉ ኢትዮጵያዊ ቁጥር ጥቂት አይደለም።
«በሕገ-ወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎቹ ኢትዮጵያዉያኑን ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመግባት ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስከፍሉዋቸዉ በርግጥ የተረጋገጠ መረጃ የለኝም። ግን እነዚህ የሕገ -ወጥ አዘዋዋሪዎች ከኢትዮጵያ ጀምሮ እስከታች ደቡብ አፍሪቃ ድረስ ሰዎች አሏቸዉ። አብዛኞቹ ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚመጡት ኢትዮጵያዉያን ደግሞ ከደቡብ ክልል ከሀድያ የመጡ ናቸዉ። እነዚህ ማኅበረሰቦች ደግሞ tግብርና ይተዳደሩ የነበሩ የከተማ ኑሮን ያልቀመሱ በመሆናቸዉ እነዚህ ሰዎች ደቡብ አፍሪቃ ሲገቡ ከፍተኛ ችግር ሲገጥማቸዉ ይታያል።»
56 ሺህ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ እንደሚኖር የተናገሩት በደቡብ አፍሪቃ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ዋና ፀሐፊ አቶ ደረጀ መኮንን፤ በከፍተኛ ልፋትና ድካም ቀንቶአቸዉ እዚያ ከገቡ በኋላ ኑሮዉ አንገሽግሾአቸዉ በፈቃደኝነት እየተመለሱ ያሉትም ጥቂት አለመሆናቸዉን ተናግረዋል።
« አብዛኞቻችን ንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተን ነዉ የምንሰራዉ ። አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ ደግሞ እጅግ ገጠራማ በሆነ አካባቢ ሱቅ ከፍቶ አልያም ተቀጥሮ ነዉ የሚሰራዉ። ታድያ አብዛኞቹ ኢትዮጵያዉያን ለጥቃት ተጋልጠዉ ይገኛሉ። ማኅበራችን በሐይማኖት ተቋማት በኩል እገዛ ለማድረግ ጥረት ቢደረግም ያን ያህል ተፅኖ መፍጠር አልቻልንም።»
እንደ አቶ ደረጀ መኮንን በደቡብ አፍሪቃ በተቀሰቀሰዉ የዉጭ ሀገር ዜጎች ጥላቻ ሁለት ኢትዮጵያዉያን በቃጠሎ ተገድለዋል በርካቶችም ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

አዜብ ታደሰ

Xenophobie in Südafrika
ምስል AP


ሸዋዬ ለገሰ