1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያዉያን አይሁዳዉያን መብት

ሐሙስ፣ የካቲት 17 2008

እስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን አይሁዳዉያን የሚደርሰዉን የዘረኝነት ጥቃት የሚከታተል ግብረ ኃይል የመጀመሪያ ስብሰባ አካሄደ። የፍትህ ሚኒስቴር ያሰባሰበዉ ግብረ-ኃይል የሀገሪቱን የትምህርት ሚኒስቴር፣ አቃቤ ሕግ፣ በኤኮኖሚ እና ንግድ ሚኒስቴር በሥራ ቦታ ለዕኩልነት የሚከራከረዉ ዘርፍ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያዉያን አይሁዳዉያን ተሟጋቾችን ያካትታል።

https://p.dw.com/p/1I2NJ
Israel Tel Aviv Protestaktion äthiopische Juden Ausschreitungen
ምስል Reuters/Baz Ratner

[No title]

ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ ጠበቃ የተሰኘዉ የመብት ተኗጋች ድርጅት ሥራ አስኪያጅ እንደሚሉት ከዚህ ቀደምም በሌሎች መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችም የተቋቋሙ አንዳንድ ኮሚቴዎች አሉ። ዓላማቸዉ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባላት እስራኤል ዉስጥ ከዘረኝነት ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶች በሀገሪቱ ሕግ መሠረት ፍትሃዊ ዉሳኔ እንዲያገኙ ለማስቻል መሠራት ያለበትን በየደረጃዉ መከታተል ነዉ።

እንደሀገር ዳግም ከተመሠረተች ዘንድሮ 68ኛ ዓመት በሚሞላት እስራኤል ዉስጥ ከአርባ ዓመታት በላይ የኖሩ ኢትዮጵያዉያን አይሁዳዉን መኖራቸዉ ይነገራል። በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከፍ ካለ ደረጃ የደረሱም አልጠፉም። ግን ደግሞ በየተሰማሩበት የሥራ መስክም ሆነ በተለያዩ የሕዝብ መሰብሰቢያና መገልገያ ስፍራዎች በቆዳቸዉ ቀለም ብቻ ተለይተዉ የዘረኝነት መንፈስ በተጠናወታቸዉ አንዳንዶች መገፋትና መገለላቸዉ ሊቋረጥ እንዳልቻለ አቶ ፋንታሁን አሰፋ ዳዊት የጠበቃ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ይናገራሉ።

እሳቸዉ እንደሚሉት ሕጉ ቢኖርም በቆዳቸዉ ቀለም ብቻ ተለይተዉ ለዘረኝነት መገለልና አድሎ መጋለጣቸዉን በማስመልከት ለሚመለከታቸዉ የእስራኤል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሁሉ አቤቱታቸዉን ያለመታከት በማቅረባቸዉ በኢትዮጵያዉያን ፈላሲያን ላይ የሚደርሰዉን ለመከላከል አንድ ግብረኃይል እንዲቋቋም ምክንያት ሆነዋል። ጥያቄያቸዉም በሀገሪቱ ሕግ መሠረት በአጥፊዎች ላይ የሚጣለዉ ቅጣት ጠንከሮ የዘረኝነት ድርጊት የሚፈፅሙ ግለሰቦች፤ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ሆኑ ድርጅቶች እንዲቆጠቡ እና ሌሎችም ከዚያ አይተዉ እንዲታረሙ ነዉ።

Benjamin Netanjahu und Damas Pakada
ጠ/ሚ ኔታንያሁና ኢትዮጵያዊ አይሁዳዊዉ ወታደርምስል picture-alliance/AA/Haim Zach

እስካሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ጨምሮ ከተለያዩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ጋር ያደረጓቸዉ ዉይይቶች አዎንታዊ ዉጤት ማስገኘታቸዉን የጠበቃ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ገልጸዋል። እንዲያም ሆኖ በተለይ ፖሊሶች ኢትዮጵያዉኑ ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት በተመለከተ የሚመረምረዉ አካል እስካሁን ምንም ርምጃ ሳይወስድ ማድበስበሱ አሳሳቢ መሆኑን አመልክተዉ መፍትሄ እንዲፈለግለት እንዳመለከቱም አስረድተዋል።

አቶ ፋንታሁን አክለዉም በእስራኤል የወጣቶች መታረሚያ ስፍራ ከሚገኙት ወጣት ጥፋተኞች አብዛኞቹ ኢትዮጵያዉያኑ መሆናቸዉ ጉዳዩ ይበልጥ አነጋጋሪ እንዳደረገዉ አመልክተዋል። ይህንና መሰል ሁኔታዎችን ለመለወጥ እንዲንቀሳቀስ የተሰየመዉና የመጀመሪያ ስብሰባዉን በዚህ ሳምንት ያካሄደዉ ግብረኃይል ቀጣይ እና ተከታታይ ዉይይቶችን የሚያደርግባቸዉ ስብሰባዎች ይኖሩታል። ኢትዮጵያዉያን ቤተእስራኤላዉያንን የሚመለከትበት ዓይኑ ችግር አለበት በተባለዉ በፖሊስ ዉስጥ ይህን ለመለወጥ እንዲቻል በርካታ ኢትዮጵያዉያን ቤተእስራኤሎች ፖሊሶች እንዲመለመሉ፤ ቀደም ብለዉ የገቡትም የማዕረግ እድገት አግኝተዉ ለማኅበረሰቡ ችግር መፍትሄ እንዲያፈላልጉ መታቀዱንም አቶ ፋንታሁን አሰፋ ዳዊት ገልጸዋል። ሌሎች የእስራኤል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶችም ከሠራተኞቻቸዉ ሁለት በመቶዉ ኢትዮጵያዉያን አይሁዶች እንዲሆኑ ለማድረግም እንቅስቃሴ መጀመሩን፤ ይህም እስከከተማ ከንቲባነት ደረጃ ይደርሳል። ይህ የመገለል እና የዘረኝነቱ ጥቃት በኢትዮጵያዉያን አይሁዳዉያኑ ላይ ይጥና እንጂ በሌሎቹ አናሳ በሆኑት ወገኖች ላይ የሚደርስ መሆኑን በማመልከትም አሁን የተጀመረዉ የለዉጥ እንቅስቃሴ በቅርቡ ሳይሆን በረዥም ጊዜ ፍሬ ሊያሳይ እንደሚችልም አመልክተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ