1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያውያኑ አፕሊኬሽን

ረቡዕ፣ የካቲት 30 2008

ሁለቱም የከፍተኛ ትምህርታቸውን ያጠናቀቀት በጀርመን መዲና በርሊን ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ነው። የዛሬ ሁለት ዓመት «አሃዱ ቴክ» የተሰኘው ድርጅታቸውን ሲያቋቁሙ ከንግድ ባሻገርም የማኅበራዊ አገልግሎት ለማበርከት በመወሰን ነበር።

https://p.dw.com/p/1IA2q
Bildergalerie Spielkonsolen - Tetris Ipad
ምስል imago/Jochen Tack

የኢትዮጵያውያኑ አፕሊኬሽን

ሁለቱ ወጣቶች ለትምህርት አጋዥ ይኾናል ያሉትን፤ በተንቀሳቃሽ ስልኮች እና ታብሌቶች እንዲሁም በኮምፒውተሮች ላይ የሚሠራ «ፊደል» የተሠኘ ማስተናበሪ (Application) ነድፈው በመሥራት ለነፃ አገልግሎት አበርክተዋል።

ወጣቶቹ የትምህርት አጋዥ የኢንተርኔት መድረክ አሰናድተው በነፃ አገልግሎት ላይ ማዋል ከጀመሩ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል። ድርጅታቸውን ሲያቋቋሙ ለሂሳብ የትምህርት አይነት ብቻ ያሰናዱትን የትምህርት አጋዥ አሁን ወደ ወደ ስምንት በማሳደግ አፕሊኬሽን ወይንም የማስተናበሪያ ስልትም ሠርተውለታል። አፕሊኬሽኑ በኮምፒውተሮች፤ በዘመናዊ ስልኮች እንዲሁም በታብሌቶች ላይ ሲጫን አገልግሎት ይሰጣል።

ከአሃዱ ቴክ መሥራቾች አንዱ የኾነው አማኑኤል አማረ ድርጅታቸው «ፊደል» በሚል ስያሜ ያሰናዳው አፕሊኬሽን በሂሳብ የትምህርት ዘርፍ ብቻ አለመወሰኑንም ተናግሯል። አፕሊኬሽኑ በአኹኑ ወቅት ለእንግሊዝኛ ቋንቋ፣ ለፊዚክስ፣ ለኬሞስትሪ፣ ለባዮሎጂ፣ ለጂኦግራፊ፣ ለሲቪክስ እና ለታሪክ የትምህርት ዘርፎች እንዲያገለግል ሰፋ ተደርጓል። እስክንድር ተስፋዬ ማሞ የአሃዱ ቴክ ሌላኛው መሥራች ነው። «ፊደል» የተሠኘውን ማስተናበሪ በተለይ ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለምን እንዳዘጋጁት ያብራራል።

«ፊደል» የትምህርት አጋዥ አፕሊኬሽን የተሠራው ሦስት አበይት ጉዳዮች ላይ በማተኮር ነው። አጠር ባለ መልኩ በጥያቄ እና መልስ እውቀትን ማሸጋገር ቀዳሚው ግብ ነው። አፕሊኬሽኑ ተማሪዎች አቻዎቻቸው የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እና መሻሻል በመከታተል ማኅበራዊ ጉድኝት እንዲፈጥሩም ያስችላል። በጨዋታ መልክ እየተዝናኑ በመወዳደር እንዲማሩ ማድረግ ደግሞ ሌላኛው ግብ ነው። ተማሪዎች አፕሊኬሽኑን በነፃ እንዲጠቀሙበት ነው የተሠራው።

ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በመጠቀም ተማሪዎች ትምህርትን እየተዝናኑ እና ከአቻዎቻቸው ጋር እየተወዳደሩ መማራቸው ጀርመንን ጨምሮ በምዕራቡ ዓለም የተለመደ ተግባር ነው። የኢንተርኔቱ እና የዘመናዊ ስልኮች ወይንም ስማርት ፎን በስፋት መገኘት ሒደቱ በምዕራቡ ዓለም የተቀላጠፈ እና በቀላሉ የሚገኝ እንዲሆን አድርጎታል። ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነት እና ውሱንነት የትምህርት አጋዡ አፕሊኬሽን ዋነኛ ተግዳሮት መኾኑ አልቀረም። ይህን ተግዳሮት ለመቋቋም ግን ወጣቶቹ መላ ዘይደዋል።

በዓለማችን በአሁኑ ወቅት ከ2 ቢሊዮን በላይ ዘመናዊ ስልኮች ወይንም ስማርትፎን እንደሚገኙ ዋና መሥሪያ ቤቱን ሐምቡርግ ከተማ ጀርመን ያደረገው ስታቲስታ የተሰኘው የመረጃ ተቋም ይገልጣል። የታብሌት ተጠቃሚዎች ደግሞ ከ1 ቢሊዮን በላይ ናቸው ይላል። የቁጥሮቹን መብዛት ተከትሎ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ ያተኮሩ እጅግ በርካታ አፕሊኬሽኖች በዓለማችን በስፋት እየተሠሩ ለተጠቃሚዎች ይቀርባሉ።

ሚሎጂክ የተሰኘው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አማካሪ ድርጅት መሥራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አያና ዓለሙ ከአሃዱ ቴክ መሥራቾች ጋር በጋራ ይሠራሉ።

ሚሎጂክ ዋና መሥሪያ ቤቱ በጀርመን ሀገር በርሊን ከተማ ሲገኝ፤ ከለን ከተማ እና ፖላንድ ውስጥም መሥሪያ ቤቶች አሉት። ከተቋቋመ አምስት ዓመት ያስቆጠረው ይኽ ድርጅት ሠራተኞቹ 150 ደርሰዋል። ከአሃዱ ቴክ ጋር በመተባበር 20 የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤት አፕሊኬሽኖችን ሠርተዋል።

ሁለቱ ወጣቶች መጀመሪያ ላይ ሊሠሩ ያሰቡት አፕሊኬሽን በግብርና ላይ የሚያተኩር ነበር። ገበሬዎች የምርት ውጤታቸው ገበያ ላይ ዋጋው ስንት ደረሰ የሚል የገበያ አሠሣ የሚያደርግ አፕሊኬሽን። የእዚያ አይነት አፕሊኬሽን ግን ቀደም ሲል በሌሎች የተሠራ በመኖሩ ሐሳባቸውን ወደ ሌሎች አፕሊኬሽኖች አዙረዋል። ከዚያም ባሻገር ኢትዮጵያውያን የአፕሊኬሽን ነዳፊዎች እና አበልጻጊዎች ሥራዎቻቸውን የሚያኖሩበት የጋራ የኢንተርኔት ቋትም አዘጋጅተዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ምን ያኽል ዘመናዊ ስልኮች እና ታብሌት ተጠቃሚዎች እንዳሉ በውል አይታወቅም። ኾኖም የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በድረ-ገጹ ባሰፈረው የጎርጎሪዮሱ 2014 ሠነድ መሠረት 27,795,615 የሞባይል ተጠቃሚዎች እንዳሉ ይጠቅሳል። ምን ያኽሉ የዘመናዊ ስልኮች እናዳላቸው ግን አልተገለጠም። የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ብዛት 6,168,048 እንደኾነም በድረ-ገጹ ሰፍሯል።

ይኽ ወጣቶቹ ያዘጋጁት የትምህርት አጋዥ አፕሊኬሽንም ሆነ ሃያዎቹ አፕሊኬሽኖች በስፋት ለመዳረስ ዕድል ይፈጥራል፤ በእርግጥ የኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነቱ እና አቅርቦቱ ደካማ መኾን የሚፈጥረው ተግዳሮት እንዳለ ማለት ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ



እስክንድር ማሞ እና አማኑኤል አማረ
እስክንድር ማሞ እና አማኑኤል አማረምስል Ahadoo Tec
የአሃዱ ቴክ ድርጅት ሠራተኞች
የአሃዱ ቴክ ድርጅት ሠራተኞችምስል Ahadoo Tec