1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሙዚቃ

«ዳማከሴ» የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከምዕራብ አፍሪካ አዋህዷል

እሑድ፣ ጥቅምት 5 2010

የኢትዮጵያ እና የምዕራብ አፍሪካ ሙዚቃ ብዙ መመሳሰል እንዳላቸው የሙዚቃ አፍቃሪያንም ባለሙያዎችም ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ የማሊ ሙዚቃ በተለይ ዓለም አቀፍ እውቅናንን በተጎናጸፉ ኢትዮጵያውያን ድምጻውያን ላይ ጭምር ተጽእኖውን እንዳሳረፈም ይነገራል፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን የሁለቱ ሀገራት ሙዚቃዎች ተቀይጠው አሊያም ተዋህደው ሲቀርቡ እምብዛም አይሰማም፡፡

https://p.dw.com/p/2lqDR
Fatoumata Diawara
ምስል picture alliance / Photoshot

«ዳማከሴ» የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከምዕራብ አፍሪካ አዋህዷል

ወዳጆቿ፣ የቅርብ ሰዎቿ እና የሀገሯ ዜጎች ሲያቆላምጧት ፋጡ ይሏታል፡፡ የመዝገብ ስሟ ፋቱማታ ጄዋራ ይሰኛል፡፡ የተወለደችው ኮትዲቯር፣ ያደገችው በወላጆቿ ሀገር ማሊ፣ ወጣትነቷን ያሳለፈችው ደግሞ በፈረንሳይ ነው፡፡ ዕውቅ ድምጻዊ፣ የግጥም እና ዜማ ደራሲ ናት፡፡ ጊታርም አሳምራ ትጫወታለች፡፡ ሁለት የግሏ የሙዚቃ አልበሞች አሏት፡፡ በሌሎች ሙዚቀኞች ስምንት አልበሞች ላይም ተሳትፋለች፡፡ አልበሞቿ የዓለም ሙዚቃ ሰንጠረዥን ለወራት ከመቆጣጠራቸው ባሻገር ሽልማቶች አጎናጽፈዋታል፡፡

Fatoumata Diawara Musikerin aus Mali
ምስል Phil Sharp

ፋቱማታ በምትቀርባቸው የሙዚቃ ዝግጅቶች ላይ አፍሪካን ዘወትር ታነሳለች፡፡ አፍሪካውያን “በጋራ መቆም፣ እርስ በእርስ መተዋወቅ፣ መግባባት” አለብን ስትል በአፍ ብቻ አይደለም፡፡ በሙዚቃ ስራዋም ሆነ በግል ህይወቷ በተግባር  አስመስክራለች፡፡ ከሀገሯ ተሻግራ ኢትዮጵያ ደርሳለች፡፡ ፋቱማታ ስለ ኢትዮጵያ ሲነሳባት ፊቷ በደስታ ይበራል፡፡ ባለፈው መጋቢት ወር የዶይቼ ቬለ ራዲዮ ጣቢያ ወደሚገኝበት ቦን ከተማ የሙዚቃ ዝግጅቷን ለማቅረብ በመጣች ወቅት ከዶይቼ ቬለ የአማርኛው ክፍል አዘጋጆች ጋር ተገናኝታ ነበር፡፡ በጭውውታችን መሃል የጫጉላ ሽርሽሯን በኢትዮጵያ ማድረጓን አጫውታናለች፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ እንደምትወድ እና እንደምታደምጥ፣ የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ዘፈኖች በተለይ በእጅ ስልኳ ላይ እንዳሉ ሁሉ አሳይተናለች፡፡ የሁለቱ ሀገራት ሙዚቃዎች በጣም እንደሚመሳሰሉ እና ከኢትዮጵያ ዘፋኞች ጋር ሙዚቃዎች መስራት እንደምትፈልግ ነግራናለች፡፡ 

የምዕራብ አፍሪካ በተለይም የማሊ ሙዚቃ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትስስር ለማስረዳት ፋቱማታ ያነሳቻትን ጂጂን መጥቀስ በቂ ነው፡፡ በርካቶች ጂጂ የማሊ ሙዚቃ በተለይም የአንጋፋዋ ድምጻዊ ኡሞዎ ሳንጋሬ ተጽዕኖ አለባት ይላሉ፡፡ ጂጂም በአንድ ወቅት በሰጠችው ቃለ ምልልስ የማሊን ሙዚቃ እና ድምጻዊቷን እንደምትወድ ተናግራለች፡፡ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ምሩቅ እና የሙዚቃ ተጨዋቿ ብሌን ዮሴፍ በኢትዮጵያ እና ማሊ ሙዚቃዎች መካከል ካሉት መመሳሰሎች አንዱ የሙዚቃ ቅኝት ነው ትላለች፡፡ ጂጂን እና ኡሞዎ ሳንጋሬን በምሳሌነት በማንሳት ታነጻጽራለች፡፡

“በእኛም በእነሱም ሀገር የበለጠ ዲያቶኒክ አይደለም፡፡ በአምስት ድምጽ ያሉ (ፔንታቶኒክ) ቅኝቶችን ነው የምንጠቀመው፡፡ ስለዚህ ፔንታቶኒክ መሆኑ ብቻ ቃላቱ እንኳ ባይገባን አዜያዚያሙ የሚፈጥርብን ተመሳሳይ ስሜት ይኖራል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ እንርሱ ጋር የሚጠቀሟቸው የfolk የሆኑ ዜማዎች እና ግጥሞች አለ፡፡ እንደገና አሁን ለምሳሌ የኡሞዎ ሳንጋሬ ‘ዋሶሉ’ የሚባል የሙዚቃ ስልት ውስጥ ይመስለኛል ያለችው፡፡ እርሱ የበለጠ የማሊዎች የሙዚቃ ስልት ነው፡፡ አሁን ይህን የሙዚቃ ስልት እንኳ ብናየው በጣም ውስብስብ ከሆነ የዜማ አካሄድ ጋር ሳይሆን በጣም ቀላል የሆነ ዜማ ግን ያንን ዜማ በጣም ማስታመም ነው የሚባለው፡፡ እኛ ጋር እንዳለው ልክ በቅላጼዎች፣ ከውስጥህ ሲወጣ በጣም ጥልቅ የሆነ ስሜት ያለው እንደዚያ አይነት አዚያዜያም እናይበታለን፡፡ ከጂጂ ጋር ሁለቱን ብናስተያያቸው የጂጂ ዘፈን ላይ የምናገኘው ዜማዎቿ በጣም ቀላል ናቸው ግን እዚያ ውስጥ የምናገኘው ስሜት በጣም ጥልቅ ነው፡፡ ስሜቱ በጣም ይገዝፋል፡፡ 

Oumou Sangare
ምስል Nuzzcom

የምዕራብ አፍሪካ፣ የማሊዎች፣ የኡሞዎ  ሳንጋሬን የሙዚቃን ስልት ብናየው call and response በሚባለው ዓይነት ቅርጽ ነው የሚሰራውለ፡፡ ወይም ደግሞ verse, chorus እያለ የሚሄድ ነው፡፡ Chorus ማለት ይሄ ተደጋግሞ የሚመጣው ነገር ነው፡፡ ያው verse ደግሞ ዜማው አንድ ዓይነት ሆኖ ግጥሙ ብቻ እየተቀያየረ የሚሄደው ክፍል ማለት ነው፡፡ በሙዚቃ ውስጥ ይሄኛውን call and response ይሉታል፡፡ ይህንኑ ስሜት አምጥተን የጂጂ ላይ ብናነጻጽረው እናገኘዋለን፡፡ አሁን ለዚህ ምሳሌ መስጠት ካስፈለገ ከሙዚቃው በኋላ ተቀባዮች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ የጂጂን “ወፉ አይናማ” ሌሎች ይቀበሏታል፡፡ እርሷ ብቻዋን አይደለችም፡፡ አጋዥ አለ፡፡ ይሄኛው ስሜት የምዕራብ አፍሪካ ሙዚቃ ውስጥም አለ፡፡ የእኛም ደግሞ folk የሆነ ዘፈኖቻችን ውስጥም አለ፡፡  

ሁለቱን ደግሞ በሌላ ነገር ብናነጻጽራቸው የኡሞዎ ሳንጋሬን ምሳሌ ብሰጥህ የእርሷም ዘፈኖች ብታዳምጣቸው አንዳንዶቹ ላይ በትንሽዬ ዜማ ብዙ ቃላትን ስትደረድር እንሰማታለን፡፡ ይህንኑ ደግሞ ነገር የእኛዋ ጂጂ ጋር እናዳምጠዋለን፡፡ እንደገና ደግሞ ፈጣን በሆነ ምት ቃላቶችን ፈጠን የማድረግ አዚያዜያም አለ፡፡ ይህንን ወደ ምዕራብ አፍሪካ የምናገኘው ነው፤ ጂጂ ላይም የምናገኘው ነው፡፡ እዚሁ አልበም ላይ ያለውን ዞምዬ የሚለውን ብተሰማው በምት ደረጃ ፍጥን ያለ ነው፡፡ እኛ ከለመድነው ስልት ትንሽ ወጣ የሚለው ማለት ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ወደ ምዕራብ አፍሪካ፣ የኡሞዎ ሳንጋሬን ሙዚቃ ስልት አሰራር ውስጥ ይከተዋል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ በእኛ ሀገር የሙዚቃ ስልት እና በእነሱ መካከል ያለው ትልቁ መመሳሰል ብዬ የማስበው እነርሱም የfolk የሆኑ የተለያዩ ቆየት ያሉ ታሪኮችን አባባሎችን በሙዚቃዎቻቸው ውስጥ ይጠቀማሉ፡፡ ያ ነገር የራስ ስሜት፣ የማንነት ስሜት ስላለው በጣም ጥልቅ የሆነ ስሜት አለው፡፡ አሁን እኛም ጋር ስንመጣ አንድ ሰው ትዝታ ሲያዜም ወይም ደግሞ ባቲ፣ አንቺ ሆዬ እነዚህ ቅኝቶችን ተጠቅመው ያሉ folk የሆኑ ሙዚቃዎቻችንን ስንሰማ፣ ዘፋኙም ሲያዜመው የሚሰማው በጣም ጥልቅ የሆነ ስሜት አለ እና እነዚያ ነገሮች በጣም ያመሳስሉናል” ስትል ሰፋ አድርጋ አብራርታለች፡፡

እንዲህ ተመሳሳይነት አላቸው የሚባሉትን የኢትዮጵያ እና የማሊ ሙዚቃዎችን በመቀየጥ ለመስራት የደፈሩ ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች በቁጥር ትንሽ ናቸው፡፡ የኢትዮጃዝ አባት የሚባለው ሙላቱ አስታጥቄ አንዱ ነው፡፡ ከአራት ዓመት በፊት ባወጣው “የኢትዮጵያ ንድፎች” (Sketches of Ethiopia) በተሰኘው አልበሙ ማሊያዊቷ ፋቱማታ አብራው አንድ ሙዚቃ ተጫውታለች፡፡ ፋታሙታ “ሱርማ” የሚል ርዕስ ያለውን ይህን ዘፈን ከኢትዮጵያውያን ጋር መስራት እንደምትችል እና ፍላጎቷ ከፍተኛ መሆኑን ማሳያ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ 

እንድሪስ ሀሰን በዚህ አልበም ስራ ላይ ማሲንቆውን ይዞ ተሳትፏል፡፡ ከፋቱማታ ጋር ግን በአካል አልተገኘም፡፡ የእርሱ የማሲንቆ ጨዋታ ለብቻ ከተቀረጸ በኋላ ከሙላቱ ቅንብር፣ ከእርሷ ድምጽ እና ከሌሎች ሙዚቀኞች ጨዋታ ጋር እንደተዋሃደ ይናገራል፡፡ የማሊያዊቷ ሙዚቀኛ በሙላቱ አልበም ላይ ጣል ይደረግ እንጂ ሙሉ የአልበም ስራው በጃዝ ስልት የተሰራ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ “እንግዲህ እኔ ያው ጃዝ እንስራ ነው [የተባልኩት] እንጂ እርሱ ያን ጊዜም ቢሆን በምዕራብ አፍሪካ ላይ በእርግጠኝነት እቅዱ አለው፡፡ ስለዚህ ያንን ቅንብሩን ሲያዘጋጀው ያ ስሜት እንዲመጣ ብሎ ነው፡፡ እኔ ደግሞ በዚያን ወቅት የምዕራብ አፍሪካ ሙዚቃ በጣም እስማ ነበር፡፡ እና ለዚህ አሁን ለምታዳምጠው ነገር አስተዋጽኦው ያ ነው፡፡ ጥሩ ነው” ይላል የማሲንቆ ተጨዋቹ፡፡ 

Äthiopien Jazz Musiker Mulatu Astatke
ምስል Mario Di Bari

እንድሪስ “ለዚህ ለምታዳምጠው ነገር” ያለው ባለፈው ዓመት አድማጭ ዘንድ የደረሰ የኢትዮጵያን እና የምዕራብ አፍሪካ (ማሊ) ሙዚቃን ያዋሃደ አልበም ማለቱ ነው፡፡ እንድሪስ “ጉንፋን የለም” የሚል ስያሜ ያለውን ይህን አልበም እውን ለማድረግ ጉልህ ሚና ከተጫወቱ አራት ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ከከበሮ እና ፐርከሽንን ተጫዋቹ ምሳሌ ለገሰ፣ ኮሪ ሴዝኔክ እና ካስ ሆርስፎል ከተባሉ ጊታር ተጫዋቾች ጋር በመሆን የመሰረቱት “ዳማከሴ” ባንድ ነው አልበሙን የሰራው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከውጭ ሀገር ሙዚቀኞች ጋር ሆነው ባንድ መመስረት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ሆኖም ብዙዎቹ ባንዶች የኢትዮጵያን ሙዚቃ በጃዝ ስልት መጫወት አሊያም ባህላዊ ሙዚቃዎችን የማዋሃድ አካሄድ ይከተላሉ፡፡ እንድሪስ እና ምሳሌ አባል የነበሩባቸው ሌሎች ባንዶችም በተመሳሳይ መልኩ የሚሰሩ ነበሩ፡፡ የ“ዳማከሴ” አባላት ሲሰባሰቡ በሁሉም ውስጥ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከምዕራብ አፍሪካ ጋር የመቀየጥ ፍላጎት እንደነበር ምሳሌ ይገልጻል፡፡ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪካዊ ዳራ ይንደረደራል፡፡  

“ሙዚቃው ሲጀመር ለመስራት የታሰበው ምንድነው? የኢትዮጵያ ሙዚቃ እና የኢትዮጵያ ዜማ (ሜሎዲ) ከምዕራብ አፍሪካ ከተለያዩ ቦታዎች ቢደባለቅ ምን ዓይነት ድምጽ ያመጣል የሚለው ነገር ከበፊትም ጀምሮ በነበሩ ዘፈኖች ላይ ነበር፡፡ ለምሳሌ እኛ ሀገር ብናስባቸው መስፍን አበበ ሲጫወት በነበረበት ጊዜ በጊታር የሚጫወቱትን፣ የድሮ የኦሮምኛ ዘፋኞች እነ አብተው ከበደ እነዚህ እነዚህ ሲጫወቱ ስታየው በጣም የመቀራረብ ነገር አለው፡፡  እንደገና ደግሞ ‘ፔንታቶኒክ ስኬል’ ነው የምንጫወተው፡፡ ተመሳሳይ የሙዚቃ መሳሪያዎችም አሉን፡፡ ከበሮን ብትል የእነሱም የእኛም ተመሳሳይነት አለው፡፡ እነሱ በብዛት የሚጠቀሙት ጃምቤ ነው፡፡ እንደገና ደግሞ መሰንቆ የምትመስል [የሙዚቃ መሳሪያ] አለቻቸው፡፡ ልክ የመሰንቆ ዓየነት ድምጽ ያለው ግን አያያዙ፣ አጨዋወቱ ላይ ትንሽ ለየት የሚል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ለረጅም ጊዜ በሀሳብ ደረጃ እኛ ጋር ስለነበሩ እስቲ እንዲህ አይነት ነገር ብናደርግ ብለን አሰብን እና መጀመሪያ አንድ ሁለት ሙዚቃዎች ከኢትዮጵያ ወስድን፡፡ እነርሱን እንደ ኢትዮጵያ ሙዚቃ አድርገን እየተጫወትን improvise በምናደርግበት ጊዜ ላይ፣ ሙዚቀኞች አንዳንድ ሶሎ በሚያደርጉበት ጊዜ ላይ በዚያኛው አይነት አጨዋወት ሲሞከር የሚሰማው ጥሩ እየሆነ መጣ፡፡ ከዚያ ቀስ በቀስ እየጨመርን ከእነቅንብሮቹ፣ አጠቃላይ ማዕቀፉን ስንሰራው ሁሉ ወደዚያ ላይ እያደርግን መጣን፡፡ እንዲህ አድርገን ነው ባንዱን የጀመርነው” ይላል ምሳሌ፡፡  ባንዱ በሙዚቃ መሳሪያ ብቻ የተቀናበሩ ስምንት ዘፈኖች የያዘውን የሙዚቃ አልበም በኢንተርኔት ለሽያጭ ያቀረበ ሲሆን በሲዲ አሳትሞም ገበያ ላይ አውሏል፡፡ አልበማቸው በኢትዮጵያ እንዲሰራጭ ከአንድ ሁለት ሙዚቃ ቤቶች ጋር ተነጋግረው እንደነበር የሚናገረው ምሳሌ “ለኢትዮጵያ ገበያ አይሆንም” የሚል ምላሽ በማግኘታቸው ሊከፋፈል እንዳልቻለ ይናገራል፡፡ እንዲህ አይነት የተቀየጡ ሙዚቃዎችን የማስደመጥ ፍላጎት ማጣት የሚታየው በሻጮች ዘንድ ብቻ እንዳልሆነ ምሳሌ ያስረዳል፡፡ ጭራሹኑ ተሰባስቦ ሙዚቃውንም ለመጫወት በብዙ ሙዚቀኞች ዘንድ ፍላጎት እንደማይስተዋል ይገልጻል፡፡ ይህም እንደዚህ አይነት ሙዚቃዎች በመስራት ለህዝብ ለማድረስ አንድ እንቅፋት ነው ይላል፡፡ የእነርሱ የአልበም ስራ እንኳ የሚፈላለጉ ሰዎች በአጋጣሚ በመገናኘታቸው የመጣ እንደሆነ ያብራራል፡፡

Äthiopien, Addis Ababa, Damakase band
ምስል Damakase

“በእንደዚህ አይነት አድርገን ብንሰራው፣ ሙዚቃችንን በእንደዚህ አይነት የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ በእንደዚህ አይነት ቅንብር ብናደርገው ይስማማናል የሚሉ ሙዚቀኞች እስካሁን አልተገኙም፡፡ ይሄ አልበም ራሱ “ጉንፋን የለም” ዘፋኞች እንዲኖሩበት ፍላጎት ነበረን፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሀገርኛ የሆኑ ዜማዎች ስለነበሩን እነርሱን በቆንጆ ድምጻዊ ተደርጎ፣ ከዚያ ቅንብሩ ወይም የብቻ የሙዚቃ ጨዋታዎቹ በምዕራብ አፍሪካ ቢሆኑ ምኞታችን ነበር፡፡ ግን እስካሁን ፍላጎቱን ያሳየን ወይም እንደዚህ አብሬያችሁ [ሆኜ] ሙዚቃ ብትሰሩልኝ ብሎ የጠየቀን ሰው አላገኝንም” ሲል የገጠማቸውን ችግሮች ያስረዳል፡፡

ብሌንም ሆነች ምሳሌ የኢትዮጵያ ሙዚቃ በዓለም ሙዚቃ ዘውግ ዝና ካለው የምዕራብ አፍሪካ ሙዚቃ ጋር መቀየጡ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለመግባት አንድ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃዎች፣ በኢትዮጵያዊ ቅኝት እና የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ጥራት መስራት ዋናው መፍትሄ ነው ይላሉ፡፡    

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ