1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ምርጫ ዝግጅት

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 15 2007

የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ምርጫ በመጪው ግንቦት ወር ይካሄዳል። ምርጫውን በበላይነት የሚያስፈጽመው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/1E9ot
Büro des National Electoral Board of Ethiopia NEBE
ምስል DW


የኢትዮጵያ አምስተኛ አገር አቅፍ ምርጫ ሊካሄድ አምስት ወራት ያህል ወራት ይቀሩታል። ምርጫው ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ሊካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለታል። በአራተኛው አገራዊ ምርጫ ገዢው ፓርቲ እና አጋሮቹ 545 መቀመጫዎች ላሸነፉበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘንድሮ 60 የፖለቲካ ፓርቲዎች ይወዳደራሉ። አቶ ወንድሙ ጎላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ምክትል ሃላፊ ተናግረዋል።
«አጠቃላይ 75 የፖለቲካ ፓርቲዎች ነው ያሉን። ከእነዚህ 23ቱ ሐገር አቀፍ ናቸው። ሌሎቹ ክልላዊ ፓርቲዎች ናቸው። አሁን የምርጫ ምልክት የወሰዱት ከ75ቱ 60 ናቸው። ምልክታቸውን የወሰዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለት ለውድድር የተዘጋጁ ናቸው ብለን ነው እኛ የምንወስዳቸው።»
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫው ተሳትፎ ለሚኖራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ሲቪክ ማህበራት፤ የመገናኛ ብዙሃንና የፍትህ አካላት ስልጠናዎች መስጠቱን አቶ ወንድሙ ጎላ ተናግረዋል። እንደ አቶ ወንድሙ ከሆነ ለምርጫው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን የማሰናዳት እና የማከፋፈል ስራው አሁን በመከወን ላይ ነው።
«የእጩዎችና የመራጮች ምዝገባ የሚካሄድበትና መረጃ የምንለዋወጥባቸው ቁሶችና ሰነዶች የማዘጋጀት ስራ ነበረ እሱን አጠናቀን በአሁኑ ሰዓት ወደ ምርጫ ጣቢያ በመሰናደት ላይ ነው የሚገኘው። ቀደም ብለን ለእጩዎች ምዝገባ የሚያስፈልጉ ሰነዶችና ቁሳቁሶች አሰራጭተናል። »
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ የምርጫ ታዛቢዎችን ማስመረጡን ቢያሳውቅም በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። በኢትዮጵያ እንዲህ ምርጫ ሲቃረብ የምርጫ ታዛቢዎች ገለልተኝነትን ጨምሮ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአባላቶቻችን ላይ እስር እና እንግልት ይደርስብናል፤ ቦርዱ ገለልተኛ አይደለም፤ ገዢው ፓርቲ የመንግስት ሃብትን አላግባብ ይጠቀማል የሚሉ ክሶች ያቀርባሉ። አቶ ወንድሙ ምርጫ ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቅሬታዎች በገለልተኝነት የማጣራት ኃላፊነት እና ዝግጁነት አለው ይላሉ።
«የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማንኛውም አይነት ቅሬታ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ሲመጣ በገለልተኝነት አጣርቶ እርምጃ የመውሰድ ሃላፊነትም አለው ዝግጁነትም አለው። እስካሁን ድረስ ቅሬታዎችም ይመጣሉ።እያጣራን የደረስንበትን ጉዳይ ለፓርቲዎችም እያሳወቅን ነው እያሳወቅን ነው የምንገኘው።»
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ

Wähleraufklärung durch die Wahlkommission Äthiopiens
የ2002 ምርጫን የድምፅ አሰጣጥ ሂደት የሚያሳይ ሥዕላዊ መግለጫምስል DW
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ