1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ቡና ስያሜዎችና የንግድ ምልክቶች

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 27 2006

ኢትዮጵያ በ2005 ዓ.ም. የጀመረችውን የቡና ስያሜዎችና የንግድ ምልክቶች የማስመዝገብ ሂደት እንደገና አነቃቃች። የኢትዮጵያን አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በበላይነት በሚመራውና ህገወጥ የቡና ንግድንና አላግባብ የሚጣል የቡና ዋጋ ተመንን ለመከላከል፣

https://p.dw.com/p/1D5SX
Äthiopien kaffeebaum
ምስል DW/A. Hahn

እንዲሁም፣ የአገሪቱን የቡና የንግድ ምልክቶች በመጠቀም ትርፋማነትን የማሳደግ ዓላማ አለው የተባለው ይህ ፕሮጀክት ሲጀመር የኢትዮጵያ የቡና ገበሬ ለምርቱ ፍትሃዊ ገቢ እንዲያገኝ ያስችላል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።
እ.ኤ.አ. በ 2006 በተጀመረው የኢትዮጵያ የቡና ስያሜዎችና የንግድ ምልክቶችን የማስመዝገብ ሂደት የይርጋጨፌ፤ ሐረርና ሲዳሞ ቡናዎች ስያሜና የንግድ ምክልቶች በ34 ሃገራት መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የንግድ ምልክት ባለሙያ የሆኑት አቶ አበበ ተስፋዬ ተናግረዋል። 15 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከሚሳተፉበት ቡና የማምረት ሂደት የሚያገኙት የምርታቸውን 10 ከመቶ ዋጋ ብቻ መሆኑን ይነገራል።ይህን ኢ-ፍትሃዊነት ያስቀራል ተብሎ በኢትዮጵያ መንግስት ተስፋ የተጣለበት የቡና ስያሜዎችና የንግድ ምልክቶችን የማስመዝገብ ሂደት እንደገና መጀመሩን በየኢትዮጵያ አዕምሮዋዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የንግድ ምልክት ባለሙያ የሆኑት አቶ አበበ ተስፋዬ ይናገራሉ። «በዚህ ፕሮጀክት በውጭ ሃገር ያሉ የቡና ገዢዎችን የማፈላለግ፤ቡናውን እንዲገዙና በፈቃድ ውል ስምምነት ውስጥ እንዲገቡ የማሳመን ስራዎች ይከናወናሉ።በተለያዩ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ የቆየው የቡና ስያሜዎችና የንግድ ምልክቶችን የማስመዝገብ ሂደት አብዛኛው ስራ በውጭ ሃገራት የሚከወን እንደመሆኑ ከፍተኛ የገንዘብ አቅምና የሰለጠነ የሰው ሃይል ይጠይቃል። ከኢትዮጵያን አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በተጨማሪ የንግድና ግብርና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በጋራ የተፈረሙ የፈቃድ ውል ስምምነቶችን በማደስ፤ተጨማሪ የቡና ገዢዎችን በማፈላለግ፤ቡናዎችን በአለም ገበያ በማስተዋወቅ ና እውቀት ያለው አማካሪ ድርጅት በመቅጠር የቡና ስያሜዎችና የንግድ ምልክቶችን የማስመዝገብ ሂደት እንደገና እንደሚቀጥል አቶ አበበ ተስፋዬ አስረድተዋል»
«የኢትዮጵያ የቡና ስያሜዎችና የንግድ ምልክቶችን በብራዚል ለማስመዝገብ ሙከራ ቢደረግም እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አለመገኘቱን የገለጹት አቶ አበበ ለእንዲህ አይነት ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት አለም አቀፍ አማካሪዎች መቀጠራቸውን ተናግረዋል።» የአለም ባንክ በያዝነው አመት ሰኔ ወር ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከምትልከው ምርት 13 ከመቶውን ይሸፍናል የተባለው ቡና ከስያሜዎችና የንግድ ምልክቶች ምዝገባ በኋላም ለአምራቹ ገበሬ ፋይዳ ያለው ጥቅም አላመጣም ሲሉ ግብይቱን በቅርበት የሚያውቁ ባለሙያዎች ይተቻሉ።

Kaffeeland Brasilien
ምስል picture-alliance/ ZB

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ