1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ቡድን እና የአፍሪቃ ዋንጫ

ሰኞ፣ ጥር 13 2005

በደቡብ አፍሪቃ ባለፈው ቅዳሜ በተጀመረው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአምና ሻምፒዮና ከሆነው የዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ባካሄዱት ጨዋት አንድ ለአንድ ተለያዩ።

https://p.dw.com/p/17O9J
Tittle: 21 01 2013 Africa cup Ethiopian Team in Mbombela, Nelspruit Autor: DW/Haimanot Turuneh
ምስል DW

ዛምቢያ በአርባ አምስተኛው ደቂቃ አንድ ግብ ስታስቆጥር ፣  ለኢትዮጵያ ደግሞ እኩል ለእኩል ያደረገውን ግብ   በስድሳ አምስተኛው ደቂቃ ያስቆጠረው አዳነ ግርማ ነው። በኔልስፕሩት ዛሬ የተካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በምድብ ሐ ውስጥ የመጀመሪያው ግጥሚያ መሆኑ ነው። 

እንደሚታወቀው  29ኛው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ባለፈው ቅዳሜ ነበር  ጆሃንስበርግ ላይ በደማቅ ትርዒት የተከፈተው።


epa03544459 Artists perform during the opening ceremony of the African Cup of Nations soccer tournament at Soccer City in Johannesburg, South Africa, 19 January 2013. EPA/KIM LUDBROOK +++(c) dpa - Bildfunk+++
ምስል picture-alliance/dpa

29ኛው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ባለፈው ቅዳሜ ጆሃንስበርግ ላይ በተካሄደ ደማቅ ትርዒት ተከፍቷል። ደቡብ አፍሪቃ የምታስተናግደው ይሄው ውድድር በተለይም በዓለም ዋንጫ ስታዲዮሞቿ ዘመናዊነት፣ በሆቴሎችና በማመላለሻ አገልግሎት ብቃት፤ እንዲሁም ዓለምአቀፍ ትኩረትን በመሳብ ረገድ በክፍለ-ዓለሚቱ እስካሁን አቻ ያልታየለት ነው። በአፍሪቃ አህጉራዊ የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር አዲስ የታሪክ ምዕራፍ፤ አዲስ ዘመን ተከፍቷል ለማለት ይቻላል።

የደቡብ አፍሪቃው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ለኢትዮጵያም ትንሣዔ ሲሆን ብሄራዊው ቡድን አሁን በስርጭታችን ወቅት ካለፈው ዋንጫ ባለቤት ከዛምቢያ ጋር በመጋጠም ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ለውድድሩ ተሳትፎ ለመብቃት ከሰላሣ ዓመታት በላይ ይፍጅባት እንጂ አንዴ ቀደምት ከሚባሉት የአፍሪቃ ሃገራት መካከል አንዷ ነበረች። ብሄራዊ ቡድኗ ከጎርጎሪሮሳውያኑ 1957 ዓ-ም አንስቶ ገና ከጅምሩ የውድድሩ ተሳታፊ ሲሆን የሶሥተኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ባለቤት እንደነበርም ይታወሳል።

ይህ እርግጥ ያለፈ ታሪክ ነው። የወቅቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አዲስ ታሪክ ለማስመዝገብ ነው ወደ ደቡብ አፍሪቃ የተጓዘው። ሕልሙ ዕውን ይሆንለት ይሆን? በስልክ ከጆሃንስበርግ ያነጋገርኩት ተባባሪያችን መላኩ አየለ እንደገለጸልኝ ከሆነ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በጥሩ ውጤት አፍቃሪዎቹን ለማርካት ቆርጦ የተነሣ ነው። ያድምጡ!

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሰ