1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ

ረቡዕ፣ ጥር 28 2006

በመንግስት መግለጫዎች መሰረት ካለፉት 10 ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ በየዓመቱ በሁለት ዓኃዝ ወይንም በእንግሊዝኛው ኣገላለጽ «ዳብል ዲጂት» የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች። ይህ ማለት ባለስልጣናቱ እንደሚሉት ኢትዮጵያ በእነዚህ ዓመታት 11 ከመቶ እና ከዚያም በላይ እያደገች ነው።

https://p.dw.com/p/1B3A8
Logo der Weltbank in Washington USA
ምስል picture-alliance/dpa

የተመድ ጨምሮ የዓለም ባንክ እና ዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ተቋም «አ ኤም ኤፍ» ም ቢሆኑ በእርግጥ ከመንግስት ዓኃዝ በጥቂቱ ዝቅ ይሉና ኢትዮጵያ ከ 7 – 9 ከመቶ እድገት እያስመዘገበች መሆኗን ይመሰክራሉ። በዓለማችን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙት ጥቂት ኣገሮች ተርታም ይመድቧታል። ከዚሁ በመንደርደርም ይመስላል የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ኣገሪቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ኣገሮች ተርታ ትሰለፋለች የሚለውን የተስፋ ብስራት መሪ መፈክራቸው ኣድርገውታል ማለት ይቻላል። መካከለኛ ገቢ ያላቸው ኣገሮች የሚባሉት እራሳቸው ከሶስት ቢከፈሉም በጥቅሉ ግን ቻይናን ጨምሮ እነ ህንድን፣ ብራዚልን ኢንዶኔዢያን፣ ናይጄሪያን ደቡብ ኣፍሪካን እና አርጀንቲናን የመሳሰሉ ኣገሮችን ያጠቃልላል። በመንግስት መልካም ምኞት መሰረት እንግዲህ ኢትዮጵያን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከእነዚህ ኣገሮች ተርታ ለማሰለፍ ነው ጥረቱ። ኣንዳንድ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በቅርበት የሚከታተሉ ስመ ጥር የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች እንደሚሉት ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው የሚመስለው።

የ ተመድ ከቀናት በፊት ይፋ ባደረገው እና የመጪውን ጊዜ የዓለም ኢኮኖሚ ይዞታን በቃኘበት የ 2014 ዓመታዊ ሪፖርቱ ላይ ኢንዳመለከተው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ባለሁለት ዓኃዝ መሆኑ ቀርቶ ባለ ኣንድ ዓኃዝ ሆኖ እንደሚቀጥል ተመልክቷል። በሪፖርቱ መሰረት ኢትዮጵያ ምንም እንኩዋን የኢኮኖሚዋ እድገት ኣሁንም ቢሆን ትልልቅ ከሚባሉት ጎራ ቢሰለፍም በመንግስት የታቀደውን መጠን ያህል ሆኖ ግን ኣልተገኘም። የኢኮኖሚው እድገት ሁለት ዓኃዝ መሆኑ ቀርቶ በኣንድ ዓኃዝ ተወስኖ ከስድስት ዓመታት በፊት ከነበረበት የ 12 በመቶ ዕድገት በግማሽ ያህል እየወረደ መምጣቱንና ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በዚሁ መጠን እንደሚቀጥልም ትንበያው ይጠቁማል። በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ከ 6,4 ከመቶ ያልበለጠ ዕድገት እንደሚኖርም ይጠበቃል።

በኣንጻሩ ደግሞ ምርትና አገልግሎቶች በኣጠቃላይ የሚያሳዩት የዋጋ ጭማሪ እያንሰራራ እንደሚቀጥልና የዋጋ ግሽበትም ወደ ሁለት ዓኃዝ እንደሚጠጋ ተመድ ይፋ ኣድርገዋል። በዚሁ መሰረት ይላል ሪፖርቱ በዚህ ዓመት የዋጋ ግሽበቱ 9,5 በመቶ እንደሚደርስ ተሰግቷል። መንግስት በእድገትና ትራንስፎርሜሺን ዕቅዱ መሰረት የሚጠበቀው የኣገሪቱ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ከጠቅላላው የኣገር ውስጥ ምርት አኩዋያ በዝቅተኛ እርከን 11 ከመቶ እና በከፍተኛው የዕድገት ጣሪያ ደግሞ 14 በመቶ እየረገጠ እንደሚጘዝ ሲገልጽ ቆይቷል።

ተመድ ባስቀመጠው ትንበያ መሰረት በኢትዮጵያ የሚኖረው የኢኮኖሚ ዕድገት ዓምና ከነበረበት 6,9 ከመቶ ዘንድሮ ወደ 6,5 በመቶ ዝቅ እንደሚል ይጠበቃል። መጪው ዓመት የኣገሪቱ የአምስት ዓመት ዕቅድ የሚያበቃበት ጊዜ ሲሆን ዕድገቱ ግን 6,4 በመቶ ብቻ ይሆናል።«ዘ አፍሪካን ኤኮኖሚክ አውትሉክ» የተባለው ሪፖርት እንዲያውም ወደ 6,3 ከመቶ ዝቅ ያደርገዋል። ለመሆኑ የኣንድ ኣገር የኢኮኖሚ እድገት ሲባል ምንድነው? መለኪያዎቹስ ምንድናቸው? ፕሮፌሰር ብርኃኑ አበጋዝ ሙያዊ ምላሽ ኣላቸው።

የዕድገት መለኪያ መስፈርቶችን በተመለከተ እንደሚታወቀው ተመድ ጨምሮ የዓለም ባንክ እና ዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ተቐም እያንዳንዱ ኣገር መረጃዎችን ኣሰባስቦ የሚያቀርብበትን ወጥ መመሪያ ያዘጋጃሉ። በመመሪያው መሰረትም መረጃዎችን ኣሰባስቦ ማቅረቡ የመንግስታቱ ፈንታ ሲሆን ኣንዳንድ መንግስታት በእርግጥ በሚመቻቸው መልኩ መረጃዎችን እያጋነኑ ማቅረባቸውም የተለመደ ነው። ዓለም ዓቀፉ ተቐማትም እነዚህኑ የተዛቡ መረጀዎችን እየተቀበሉ መልሰው ሲያስተጋቡ ይስተዋላል። የኢትዮጵያም ሁኔታ ፕሮፌሰር ብርኃኑ አበጋዝ እንደሚሉት ከዚህ የተለየ ኣይደለም።

ከቀናት በፊት ይፋ በሆነው የ ተመድ ዓመታዊ ዘገባ ላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት መንግስት እንደሚለው 11 በመቶ መሆኑ ቀርቶ ወደ 6,4 ከመቶ እንደሚወርድ ተመልክቷል። በእርግጥ የዓለም የገንዘብ ድርጅት «አይ ኤም ኤፍ» ወደ 7,5 ሊደርስ እንደሚችል ቢገምትም «ዘ አፍሪካን ኤኮኖሚክ አውትሉክ» የተሰኘው ሪፖርት ደግሞ ይብሱኑ ከ 6,3 ከመቶ በላይ ሊሆን ኣይችልም ሲል ይከራከራል። ለመሆኑ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋና የእድገቱ ሞተር መጋቢዎች ምንድናቸው? ፕሮፌሰር ብርኃኑ አበጋዝ።

Logo Internationaler Währungsfonds
ምስል picture-alliance/dpa

ሌላው ለፕሮፌሰር ብርኃኑ አበጋዝ ያቀረብኩላቸው ጥያቄ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት በተመለከተ የተባለው እድገት ከወረቀት ኣልፎ መሬት ላይ የሚታይ ነገር የለም የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ኣንዳንድ የመሰረተ ልማት ኣውታሮች መሬት ላይ ቢታዩም በህብረተሰቡ ኑሮ ላይ ግን እየተባባሰ የሚሄድ እንጂ እየተሻሻለ የሚመጣ ለውጥ የለም የሚሉ ወገኖችም ስላሉ ከሙያ አንጻር እንዴት ይገመግሙታል የሚል ነበር።

በኢትዮጵያ የነበረውም ሆነ ኣሁን ከ 11 በመቶ ወደ 6,4 ከመቶ ወርዷል የተባለው የኢኮኖሚ ዕድገትም ቢሆን በምስራቅ ኣፍሪካ ከፍተኛው የኢኮኖሚ ዕድገት መሆኑ ተመስክሮለታል። በምስራቅ ኣፍሪካ ኣገሮች ዘንድሮ የሚጠበቀው ዓመታዊ ዕድገት 6,4 ሲሆን ዓምና በቀጠናው የተመዘገበው ዕድገት 6 በመቶ ነው የነበረው። 6 ከመቶም ሆነ በተለይም 7 እና 8 ከመቶ የሚባሉት የዕድገት እርከኖች የኢኮኖሚ ባለሙያው ፕሮፌሰር ብርኃኑ አበጋዝ እንደሚሉት ቀላል የሚባል ኣይደለም። ክፍል ሁለት ይቀጥላል።

ጃፈር ዓሊ

ተክሌ የኃላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ