1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ኅብረት ኃይል በሶማሊያ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 12 2008

ሶማሊያ የዘመተው የአፍሪቃ ኅብረት ኃይል በምህፃሩ«አሚሶም» ከትናንት በስተያ ደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ውስጥ በሚገኝ አንድ መንደር ውስጥ በኢትዮጵያ ጦር ፣ በ 14 ሰላማዊ ሰዎች ላይ ተፈፀመ የተባለውን ግድያ በማጣራት ላይ መሆኑን አስታወቀ ።

https://p.dw.com/p/1JSCP
Äthiopien Soldaten
ምስል Getty Images/AFP/J. Vaughan

[No title]


ጥቃቱ የተፈፀመው የአሸባብ ተዋጊ አንድ የኢትዮጵያ ወታደር ከገደለ በኋላ በተወሰደው የአፀፋ እርምጃ መሆኑን መቅዲሾ

የሚገኝ ጋዜጠኛ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ለዶቼቬለ ተናግሯል ። «አሚሶም» ባወጣው መግለጫ ስለ ጥቃቱ የሚካሄደው ምርመራ እንደተጠናቀቀ ውጤቱ ይፋ እንደሚሆን አስታውቋል ። ጥቃቱ የደረሰው ደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ውስጥ ከባይዶዋ ከተማ 30 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዋርዲሌ በተባለችው መንደር ነው ። መቅዲሾ የሚገኘው ጋዜጠኛ ሃሰን ኢስቲል እንደተናገረው በአሚሶም ስር ሶማሊያ የዘመቱት የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ መንደሪቱ የሄዱት የሶማሊያን ጦር የሚወጋው አሸባብ በዚያ እንደሚገኝ መረጃ ደርሷቸው ነው ። የአሸባብ ኃይል በመንደሪቱ አቅራቢያ ባለው የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ለመጣል እዚያ መግባቱ የተነገረው የአፍሪቃ ኅብረት ኃይል ወደ መንደሪቱ ከሄደ በኋላ ምን እንደገጠመው ጋዜጠኛ ሃሰን ያስረዳል ።
«የአፍሪቃ ኅብረት ኃይል አንዳንድ የአሸባብ ኃይሎች ሃይማኖታዊ ስርዓት በሚካሄድበት በዚህ ስፍራ እንዳሉ መረጃ ደርሶት ወደዚያ እንደሄደ አምኗል ። ሆኖም ነዋሪዎች አሸባብን ስለሚፈሩ አሸባብ የት እንዳለ የሚጠቁም መረጃ አይሰጡም ። እናም የአፍሪቃ ኅብረት ኃይል አካባቢውን ለቆ በመውጣት ላይ እያለ አንድ የአሸባብ አባል በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ተኩሶ አንድ ወታደር ከገደለ በኋላ የኢትዮጵያ ወታደሮች በአፀፋው በከፈቱት ተኩስ በመንደሪቱ የነበሩ 14 ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል ። በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚካሄድ ተነግሯል ። »
የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አንድ የምክር ቤት አባል ጠቅሶ እንደዘገበው ዋርዲሌ ውስጥ የአሸባብ ተዋጊዎች እና የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች እና የአፍሪቃ ኅብረት ኃይሎች ባካሄዱት ውጊያ ከተገደሉት 14 ሰዎች መካከል አዛውንቶች እና ሰላማዊ ሰዎች ይገኙበታል ።የምክር ቤት አባሉ የአሸባብ ተዋጊ በአፍሪቃ ኅብረት ጦር ላይ ተኩስ በከፈተበት ወቅት ሰዎቹ ተሰብስበው ፀሎት በማድረስ ላይ ነበሩ ብለዋል ። ሌሎች ሰዎች ደግሞ የተለየ መረጃ ነው የሰጡት ።ዜና አገልግሎቱ ያነነጋገራቸው ብዙ የዓይን እማኞች የኢትዮጵያ ወታደሮች ጥቃት የከፈቱት ትንኮሳ ሳይደርስባቸው መሆኑን ገልፀዋል ። አንድ በእማኛነት የተጠቀሱ ሰው ፣የኢትዮጵያ ወታደሮች ዋርዲሌ ሲደርሱ የቁርዓን መምህራን እና ሌሎች ሰላማዊ ሰዎች የተሰበሰቡበትን ቤት ዒላማ ማድረጋቸውን በወቅቱም ለአንድ ታማሚ እየተፀለየ እንደነበር መናገራቸው ተዘግቧል ። የመቅዲሾው ጋዜጠኛ ሃሰን እንደተናገረው አንድ የሶማሊያ ምክር ቤት አባል እና ሁለት ሚኒስትሮች እንዲሁም የጎሳ መሪዎች ጥቃቱ የደረሰበትን ስፍራ ትናንት ከጎበኙ በኋላ መግለጫ ሰጥተው ነበር ።
«የፓርላማው አባል የአዛውንቶችን ጨምሮ የ14 ሰዎችን አስከሬኖች መቁጠራቸውን ተናግረዋል። ሰዎቹ የተገደሉት የአሸባብ ኃይሎች በአካባቢው በነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ካደረሱ እና አንድ ወታደር ከገደሉ በኋላ ነው ። ከዚያም የኢትዮጵያ ወታደሮች በነሲብ መተኮስ ከጀመሩ በኋላ 14 ሰላማዊ ሰዎች ተገደሉ ።ሆኖም እስካሁን ድረስ ከሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ያገኘነው መግለጫ የለም ።»
ሶማሊያ የዘመተው የአፍሪቃ ኅብረት ኃይል «አሚሶም» ዛሬ ባወጣው መግለጫ እሁድ ማታ በኢትዮጵያ ወታደሮች ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት ማጣራት መጀመሩን አስታውቋል ።ምርመራው እንደተጠናቀቀም ውጤቱን ለህዝብ እንደሚያሳውቅም ገልጿል ። የአፍሪቃ ኅብረት ኃይል ሶማሊያ መጀመሪያ የዘመተው በጎርጎሮሳዊው 2007 ዓም ነው ።በአሁኑ ጊዜም በተልዕኮው ስር ሶማሊያ የሚገኙት ወታደሮቹ ቁጥር 22ሺህ ይደርሳል ።

Somalia Kämpfer der al-Shabaab in Mogadischu
ምስል M:Abdiwahab/AFP/Getty Image
Äthiopien Soldaten
ምስል John Moore/Getty Images

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ